የመንግሥት የፀጥታ ኀይል እንዲደርስላቸው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን የኪራሙ ወረዳ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

(አሚኮ) በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ የሽብርተኛው ሸኔ ቡድን ዘርን መሰረት በማድረግ በአማራዎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በስልክ ተናግረዋል፡፡
ከመስከረም 30//2014 ዓ.ም ጀምሮ መፈጸም የጀመረው ጥቃት እስከ ዛሬ ቀጥሏል ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡ በጥቃቱም ንጹሃን ተግድለዋል፤ ተፈናቅለዋል፤ ሃብት ንብረት ተዘርፏል፣ ወድሟል ነው ያሉት፡፡
ለአካባቢው አሥተዳደር ጥቃቱን እንዲያስቆም ቢያመለክቱም ምላሽ ማገኘት አለመቻላቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ በአፋጣኝ የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኀይል በማስገባት ሕይወታቸውን ሊታደግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሽብርተኛው ሸኔ ዓላማ አማራን ማጥፋት ነው ያሉት ነዋሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ሽብርተኛው የሸኔ ቡድን ከበባ በመፈጸም ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን ምላሽ እንዳገኘን ይዘን እንቀርባለን።