የጦርነት ቀጠና በሆኑ የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች የዓለም ምግብ ፕሮግራም ድጋፍ ማቅረብ መጀመሩ ተገልጿል።

የጦርነት ቀጠና በሆኑ የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) በራሱ አርማ መለያ ድጋፍ ማቅረብ መጀመሩ ተገልጿል።

በትግራይ ክልል ድጋፍ ሲያቀርቡ የነበሩ አጋር አካላት ከዛሬ ጀምሮ ተመሳሳይ እርዳታ ወደአማራ ክልል ለማቅረብ ከመንግስት ጋር ውል መፈፀማቸው ተነግሯል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ ለሸገር ኤፍ ኤም 102.1 በሰጡት ቃል ፥ WFP በራሱ አርማና መለያ ተሽከርካሪዎችን ማስገባት እና ማከፋፈል ስለሚችል ድርጅቱ ይህን እንዲሰራ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከአጋር አካላት ጋር በተደረገ ስብሰባ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውል ገብተው እስከሰሩ ድረስ ወደአካባቢው የግድ መግባት አለባቸው በሚል እነሱም በተቻላቸው አቅም ተጨማሪ ሃብት ከሌሎች ፕሮግራሞች ወደዚህ በማምጣት ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

አቶ ደበበ ፥ “ከዛሬ ጀምሮ በእያንዳንዱ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል ICP አቋቁመናል፤ ሰዎች እዛ ሁሉ እንዲመድቡ ስምምነት ተደርሷል ፤ ስለዚህ እነሱ ከሚቀርባቸው ዋና መስሪያ ቤት ጋር በመገናኘት እንዲሰሩ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል” ብለዋል።

በሌላ በኩል የብሄራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ለደቡብ እና ሰሜን ወሎ አጎራባች ከሆኑ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎች 270,318 መሆናቸውን ጠቁሞ ተፈናቃዮቹ ደሴ እንደሚገኙ አመልክቷል።

ለተፈናቃዮቹ በመንግስት እና አጋር አካላት በኩል ድጋፍ እየተደረገ ነው ብሏል ፥ ድጋፍ ከሚደረግላቸው መካከል 118,000 በመንግስት በኩል 60 ሺ ደግሞ Joint Emergancy Operation (JEOP) በሚባል አጋር አካል የሚሰጥ መሆኑን ኮሚሽኑ ለሬድዮ ጣቢያው ገልጿል።

Credit : Sheger FM