ሰሜን ወሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በረሃብ ምክንያት ከሞት ጋር መጋፈጣቸው ተሰምቷል።

ሕወሓት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ እየፈፀመ ባለው ግፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በረሃብ ምክንያት ከሞት ጋር መጋፈጣቸው ተሰምቷል።  ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን ቡድኑ በከፈተው ወረራና ጦርነት በዞኑ የተፈናቀሉ እናቶች፣ ህፃናትና አዛውንቶች ለሞት የሚያደርስ ረሃብ ውስጥ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡
አልጀዚራ፣ ሮይተርስ፣ አጃንስፍራንስ ፕረስ፣ ቢቢሲ፣ ፎክስ ኒውስና አሶሼትድ ፕሬስ ሚሊዮኖች ለህይወታቸው በሚያሰጋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ ይህንኑ መልዕክትና ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ እይታውን ሊያስተካከል እንደሚገባው እንዲሁም የረድኤት ተቋማት በሰብኣዊ አቅርቦት መንግሥትን እንዲያግዙ የሚጠይቁ የቲውተር ዘመቻዎችም እንደቀጠሉ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሐሙስ ጳጉሜ 4/2013 በሰጠው መግለጫ በአካባቢው በሽብር ቡድኑ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብኣዊ አቅርቦትን ከተባባሪ የረድኤት ተቋማት ጋር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ለሽብር ቡድኑ ሕወሓት ወገንተኛ ዘገባን የሚዘግቡ ተቋማትና በሰብኣዊ አቅርቦት ሽፋን የሽብር ቡድኑን ለመደገፍ የሚሰሩ አካላት ሰብኣዊነት ካሳሰባቸው በሁሉም አካባቢ ላሉና በሽብር ቡድኑ ምክንያት ችግር ውስጥ ለገቡ ድምፅ ሊሆኑ እንደሚገባ በመግለፅ ከኢትዮጵያዊያን ውግዘት እየደረሰባቸው ነው፡፡