ተማሪዎችን የያዙ የመጀመሪያ 10 አውቶብሶች የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ለመረከብ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ወደ ትግራይ ተመልሰዋል – መቐለ ዩኒቨርሲቲ

ዛሬ ከሰዓት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ በወቅታዊ የተማሪዎች ጉዳይ መግለጫ አውጥቷል።

ይህ መግለጫ በዩኒቨርሲቲው ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ በኩል ነው የተሰራጨው።

ዩኒቨርሲቲው ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ፣ መቐለ እና አዲስ አበባ ከሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤቶች እና “ከትግራይ ክልል መንግስት” ጋር በመነጋገር 4 ሺህ 896 ከትግራይ ክልል ውጭ የመጡ ተማሪዎችን በአብዓላ (አፋር ክልል) በኩል እሁድ ሐምሌ11/2013 ዓ.ም ለመሸኘት ዝግጅት አድርጎ መንቀሳቀሱን ገልጿል።

ይህን እንቅስቃሴ ሲያደርግም ምንም አይነት ገንዘብ ማንቀሳቀስ በማይችልበት፣ ስልክም ሆነ ሌላ ምንም የግንኙነት መንገድ በሌለበት እና በከተማው ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ባለበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበር ብሏል።

እሁድ ጥዋት ተማሪዎችን የያዙ የመጀመሪያ 10 አውቶብሶች አባዓላ ከደረሱ በኋላ የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ወደኋላ እንዲመለሱ ትዕዛዝ እንዳስተላለፉ፤ ተማሪዎቹን አጅበው የሄዱት የተባበሩት መንግስታት ወኪሎችም ሁኔታውን ለማስረዳት ቢሞክሩም እንዳልተሳካ አሳውቋል።

አብዓላ ድረስ ተማሪዎቹን ርክክብ ይፈፅማሉ የተባሉ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተወካይም በሰዓቱ ስልክ ሲደወልላቸው “አሁን ሰመራ ነው የምገኘው” የሚል ምላሽ እንደሰጡ እና ተማሪዎቹን ተቀብለው ወደመሃል ሀገር የሚያጓጉዙት አውቶብሶችም በቦታው እንደሌሉ ተወካዩ ማሳወቃቸውን ዩኒቨርሲቲው በመግለጫው ጠቅሷል።

በዚህ ምክንያት ጉዞው አጅበው የተንቀሳቀሱ የድርጅቱ ሰዎች ባላሰቡት መልኩ አውቶብሶቹ እንዲመለሱ እና መርሃግብሩ እንዲሰረዝ ተደርጓል ሲል አሳውቋል።

ዩኒቨርሲቲው አሁን ፦

– በባንክ የነበረውን ገንዘብ እንዳያንቀሳቅስ የታገደበት

– የሰኔ 2013 በጀት ባልተላከበት

– የ2014 በጀት ባልተለቀቀበት ሁኔታ ይገኛል ሲልም አስረድቷል።

በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ከ10 ሺህ በላይ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ያሉት በመሆኑ፣ የምግብ አቅርቦት ግዢ ለመፈፀም ገንዘብ ስለማያንቀሳቅስ እና በግምጃ ቤት የነበረ የምግብ ክምችት ስላለቀ በከፍተኛ ውጥረት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ያለውን ችግር ለማቃለል ከዓዲግራት እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ የተደረገለት መሆኑን የገለፀው መቐለ ዩኒቨርሲቲ የምግብ አቅርቦት ድጋፉ ከሐምሌ 20 በኋላ ሊዘልቅልኝ አይችልም ብሏል።

በሌላ በኩል የዪኒቨርሲቲው የባንክ አካውንት በመታገዱ እና በጀት ስላልተላከለት ከ7 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የሰኔ ወር ደመወዝ መክፈል እንዳልተቻለም አሳውቋል።

መቐለ ዩኒቨርሲቲ ከላይ የተዘረዘሩ ተግዳሮቶች ባሉበት ሁኔታ ተማሪዎችን ማቆየትም ሆነ ወደመጡበት ለመሸኘት ከማይችልበት ደረጃ መድረሱን አሳስቧል።

ዩኒቨርሲቲው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ እንዲያመቻች አልያም መቐለ ድረስ አውቶቡስ በመላክ ተማሪዎቹን እንዲያጓጉዝ በፅሁፍ መጠየቁን በመግለጫው ላይ ገልጿል።

ተማሪዎቹን ለማጓጓዝ መቐለ ድረስ ለሚመጡ አውቶቡሶች እና ሹፌሮቻቸው ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የ “ትግራይ ክልል መንግስት” ዋስትና እንዲሰጥ የማረጋገጥ ስራ እና የተባበሩት መንግስታት በታዛቢነት ጉዞውን እንዲያጅብ የማስተባበር ኃላፊነት መቐለ ዩኒቨርሲቲ እንደሚወጣ ለሚኒስቴሩ ማሳወቁን ገልጿል።

ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ተማሪዎቹ በአስቸኳይ ወደቤተሰቦቻቸው የመሸኘት ስራ ካልተፈፀመ ወይም ዩኒቨርሲቲው ገንዘብ የሚያገኘበት መንገድ ካልተፈጠረ ከሐምሌ 20 ጀምሮ ተማሪዎቹ ለሚያጋጥማቸው ከምግብ እጦት ጋር የተያያዘ ችግር ዩኒቨርሲቲው ኃላፊነት አልወስድም ብሏል።

** መቐለ ዪኒቨርሲቲ ካወጣው መግለጫ ጋር በተገናኘ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው።