ማህሌት ፋንታሁንና ጌታቸው ሽፈራው የ2011 የአመቱ ሰዎች #ግርማ_ካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በቅድሚያ እንኳን ለአዲሱ አመት በሰላምና በጤና አደረሳሽሁ እላለሁ። 2011 ዓ.ም ልዩ አመት ናት። ድንቅ አመት። ኢትዮጵያዉያን ፣ ኤርትራዉያንንም ጨምሮ የሳቅንበት፣ የተደሰትንበት አመት። የታሰሩ ተፈተዋል፤ የተሰደዱ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፤ የጦርነት አዉድማዎች የሰላም ቀጠና ሆነዋል። ይሄን ሁሉ ላደረገ ለእግዚአብሄር ክብር ምስጋና ይድረሰው።

አዲሱን አመት ስንጀምር ብዙ ወገኖች የአመቱ ሰው ብለው የሚወዱትን፣ የሚያደንቁትን ኢትዮጵያዊና .ኢትዮጵያዉት ይጠቅሳሉ። ዶ/ር አብይ አህመድ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፥ እንዲሁም ብዙዎች በብዙ ወገኖች ዘንድ አድናቆትን አትርፈዋል።

እኔም ሁለት ኢትዮጵያውያንን የአመቱ ሰዎች ብዮ መርጫቸዋለሁ። አንዲት እህትና አንድ ወንድም። ሁለቱም ኢትዮጵያዊ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። ሁለቱም ወህኒ ወርደው የተሰቃዩና ቶርቸር የተደረጉ ናቸው። ሁለቱም ተመሳሳይ ስራ ነው የሰሩት፣ እየሰሩ ያሉት። ሁለቱም ጸሃፊዎች ናቸው። ጦማሪያን። የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁንና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ናቸው።

ማህሌትን ያወኳት የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ተብላ ከታሰረች በኋላ ነበር። ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን እስር ቤት ሆና ስለደረሰባት ግፍስትናገር «ሙሉ ልብሴን እንዳወልቅ ተገድጄ ራቄቴን በወንድ መርማሪዎች ፊት ስፓርት አንድሰራ እገደድ ነበር ፡ ሴትነትሽ አንዲህ ከሚዋረድ አመጽ እንዳነሳሳሽ እመኚ ተብያሁ» ነበር ያለችው። እህቶቻችን ሞራላዊ፣ መንፈሳዊና የሴትነት ክብራቸውን በመድፈር ፣ ራቁታቸውን ሆነው በአረመኔ የሕወሃት ወንድ ምናምንቴዎች ፊት ስፖርት እንዲሰሩ መገደዳቸው ምን ያህል እንደ አገር ዘቅጠን እንደነበረ የሚያሳይ ነው። በርግጥ ማህሌት ብቻ ሳትሆን ሕወሃቶች ከ40 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን የአገራችንን እናቶችና እህቶች ነበር የደፈሩት።

ማህሌት ፋንታሁን ኢሰብአዊ ቶርቸር በወህኒ ቢፈጸምባትም አንገቷን አልደፋችም። መረረኝ ብላ ዝምታን አልመረጠችም። እኔ ላይ በወህኒ የተሰራው በሌሎች ላይ መድረስ የለበትም በሚል፣ እርሷ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ግፊት ብትፈታም፣ ሌሎች የታሰሩ እንዲፈቱ ግፊት ማድረጓን፣ ስለሌሎች መጦመሯን አላቆመችም።

ጌታቸው ሽፈራውም በወህኒ ወርዶ ፍዳዉን አይቷል። ጌታቸውን የማወቀው ከመከሰሱ በፊት ነው። በተለይም የታሰሩ እስረኞችን ጉዳይ የልብ ትረታው ነበር። ከሶስት አመታት በፊት በውስጥ መስመር “ ችግር ያለባቸውን እስረኞች ወይንም የእስረኛ ቤተሰቦች በዝርዝር ለማቅረብ እየሞከርኩ ነው፡፡ ምን አልባትም በአንተ አነሳሽነት ዳያስፖራው እንዲረዳ ካደረክ እኔ ሌሎች ጓደኞቼ ጋር በመሆን የድርሻዬ እወጣለሁ፡፡ ዛሬ ልነግርህ የምፈልገው ስለአንዲት እማዋይሽ የምትባል እስረኛ ነው፡፡ በእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ ክስ ተከሳ የታሰረች ነች” ብሎ ስለ ወይዘሮ እማዋይሽ አጫወተኝ። ሌሎች ከጌታቸው ጋር እላላካቸው የነበሩ መልእክቶች ሁሉ አብዛኞቹ እስረኞችን በተመለከተ ነበር። ከነ ጌታቸው ሽፈራው በተገኘ መረጃ በካናዳና በአሜሪካ ያሉ ያሉ የቀድሞ አንድነት ደጋፊዎች፣ ወ/ሮ እማዋየሽን ጨምሮ ከሃያ ስድስት በላይ የእስረኛ ቤተስቦች ወደ ሁለት አመት ገደማ ድጋፍ ያደርጉ ነበር።

ጌታቸው ሽፍራው ብዙም አልቆየም ሽብርተኛ ብለው አሰሩት። አንዱ የቀረበበትም ክስ ፣ ከኔ ጋር እስረኞችን በተመለከተ ሐሳብ መለዋወጡ ነበር። “ተከሳሽ በሚጠቀምበት ማሀበራዊ ድህረ ገጽ በተለይም ፌስ ቡክ አድራሻዉን ተጠቅሞ በዉጭ አገር ከሚገኝ የሽብር ቡድኑ ግንቦት ሰባት አመራር እና አባል የሆነው ግርማ ካሳ ተብሎ የሚጠራ ግንኙነት በመፍጠር በሽብር ቡድኑ የተሰጠዉን ተልእኮ በማስፈጸም በቀን 27/2/2007 ዓ/ም፣ በ28/2/2007 ዓ/ም፣ በ10/6/2007 ዓ/ም፣ በ11/06/2007 ዓ/ም፣ በ18/06/2007 ዓ/ም፣ በ01/07/2007 ዓ/ም እየተገናኙ ስለ ግንቦት ሰባት እና አሸባሪ ተብለው የተከሰሱትን ቤተሰቦቻቸው እንዴት ሊደገፉ እንደሚችሉ የሚገልጽ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መረጃዎች የተለዋወጡ በመሆኑ በዝርዝር ያደረጉት ንግግር በክሳችን በተጠቀሰው ማስረጃ የቀረበ በመሆኑ…” ይል ነበር አንዱ ክስ ፣ በሚያስቅ ሁኔታ ግንቦት ሰባት ከተመሰረተ ጊዜ ጀመሮ በግንቦት ሰባት አካሄድ ችግር እንዳለኝ በይፋና በአደባባይ እጽፍ የነበርኩትን፣ የግንቦት ሰባት አመራር አድርገውኝ።

ጌታቸው በወህኒ በጣም አሰቃይተዉታል።ሞራሉንና መንፈሱን ለመስበር ብዙ ሞክረዋል። እንደደረሰበት መከራና ስቃይ በቃኝ ብሎ አርፎ መቀመጥ ነበረበት። ግን አላደረገዉም።ብዙዎች ስለ ኮሎኔል ደመቀ፣ ስለ አቶ በቀለ ገርባ፣ ስለ ወንድም አንዱዋለም አራጌ፣ ስለ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ስለ ጋዜጠኛ እስክንድር …ነበር የሚጽፉትና የሚናገሩት። ግን ያልተዘመረላቸው፣ ሰው የማያውቃቸውን፣ የተረሱትን እያስታወሰ፣ የፍርድ ቤት ክሳቸውን እየተከታተለ ሕዝብ እንዲያውቃቸው ያደረገ ፣ አሁንም እያደረገ ያለ የእስረኞች ተቆርቋሪና ተሟጋች ወጣት ነው።

ማህሌት ፋንታሁንና ጌታቸው ሽፈራው ፣ ሁሉን እርግፍ አድርገው በመተው ዝም ብለው መቀመጥ ይችሉ ነበር። ቀላሉም ነገር እርሱ ነበር። ግን ቀላሉን አልመረጡም። የሌሎች ሕመም ሕመማቸው ስለሆነ በየፍርድ ቤቱ እየሄዱ ማንም የማያስታወሳቸውን እስረኞች ሁኔታ ዘር፣ ፓርቲ ሳይለዩ ለሕዝብ ያሳወቁ ነበር፡ እያሳወቁም ነው። ያንን በማድረጋቸው የሚያገኙት ልዩ ጥቅም አልነበረም። ያንን በማደጋቸው ደሞዝ አይከፈላቸውም። ግን ያንን ያደርጉ የነበሩት ትልቅ ሰው ስለሆኑ ነው። ትልቅ ሰው የሌላው ሕመም፣ የሌላው ስቃይ አያስተኛዉምና።

እንደ እህት ማህሌት ፋንታሁንና ወንድም ጌታቸው ሽፈራው፣ ወረድ ብለው የወደቁትን የሚያነሱ፣ የተረሱትን የሚያስታዉስ ዜጎችን እግዚአብሄር ያብዛልን።
መልካም አዲስ አመት