የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 26.1 ሚሊዮን ደረሰ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሶማሌ እና አፋር ክልሎች ውጪ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሁለት ሳምንት ያራዘመው የመራጮች ምዝገባ የሚጠናቀቀው ከሁለት ቀናት በኋላ በመጪው አርብ ሚያዝያ 29፤ 2013 ነው።

እስካለፈው ሳምንት ሐሙስ ሚያዝያ 21 ድረስ፤ የተመዘገቡ አጠቃላይ መራጮች ብዛት 26.1 ሚሊዮን መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

ከተመዘገቡት መራጮች መካከል 1.4 ሚሊዮን ያህል የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

ምርጫ ቦርድ ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው መረጃ እስከ ሚያዝያ 14 ባለው ጊዜ 18,427,239 መራጮች መመዝገባቸውን ይፋ አድርጎ ነበር። ይህ መረጃ ከተለቀቀበት ጊዜ አንስቶ ባለው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመምረጥ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ወደ ስምንት ሚሊዮን ይጠጋል።  ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ባልተጀመረባቸው የምርጫ ክልሎችን የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን ለማከናወን የጸጥታ ችግሮች እንቅፋት በሆነባቸው አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 – ግንቦት 13 ቀን 2013 ድረስ በልዩ ሁኔታ እንዲራዘም ወስኗል።

በዚህም መሰረት ፣ በምእራብ ወለጋ ዞን ከ ቤጊ እና ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል ውጪ ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን (ከአያና እና ገሊላ ምርጫ ክልል ውጪ) ፣በቄለም ወለጋ ዞን እና በሆሮ ጉድሩ ዞን (ከአሊቦ፣ ጊዳም እና ኮምቦልቻ ምርጫ ክልል ውጪ) ከሚገኙት 31 ምርጫ ክልሎች መካከል በ24ቱ ላይ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በከማሽ ዞን ከሚገኙት አምስት የምርጫ ክልሎች በአራቱ የመራጮች ምዝገባ (ከሴዳል ምርጫ ክልል ውጪ)የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 – ግንቦት 13 ቀን 2013 ድረስ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን ወስኗል።

ከዚህም በተጨማሪ የመራጮች ምዝገባ በጸጥታ ችግር የተነሳ ሳይከናወንበት የነበረው የአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔር ልዪ ዞን የሚገኙት ዳዋ ጨፌ፣ ጨፋ ሮቢት እና ባቲ ምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 – ግንቦት 13 ቀን 2013 ድረስ ይከናወናል።