‘አጋንንትን በካራቴ በመጣል’ና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች አነጋጋሪና አወዛጋቢው ነብይና ሃዋርያ ተብለው ከተነሱ ብዙዎች አንዱ እዩ ጩፋ

ደቡብ ውስጥ ነብያትና ሃዋርያት በዝተዋል ይባላል በዚህ ውስጥ ራስህን እንዴት ነው የምታየው?

ነብይ እዩ ጩፋ እውነት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያገለግሉ የብዙ ነብያትና ሃዋርያት መነሻ ደቡብ ነው፤ እኔም ከዚያው ነኝ። ምናልባት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሊኖረው ይችላል። ደቡቡም ሰሜኑም የእግዚአብሔር ነው። ነገር ግን እኔ የተወለድኩበት ወላይታ አካባቢ ብዙ ዋጋ የከፈሉ የወንጌል አባቶች የነበሩበት በመሆኑ ከዚያ ጋርም ሊያያዝ ይችላል ብዬ አምናለሁ።

ሰተኛ ነብያት በብዛት የሚነሱበት ጊዜ እንደሚመጣ በመፅሃፍ ቅዱስም ተፅፏል።እነዚህ ነብያትና ሃዋርያት ሁሉም እውነተኛ ናቸው?

እዩ ጩፋ በዚህ ጊዜ ሐሰተኛም እውነተኛም ነብያት አሉ። የሚታወቁት ደግሞ በሥራቸው፤ በፍሬያቸው ነው። እኔ ግን የእግዚአብሔብርን ወንጌል እያገለገልኩ የምገኝ የእግዚአብሔር ነብይ ነኝ ብዬ አምናለሁ።

ግን አንተም ገንዘብ ከፍሎ ምስክርነት ያሰጣል፤ ወደ ንግድነት ያደላ ይማኖታዊ አካሄድ ይከተላል ትባላለህ?

እዩ ጩፋ እውነት ነው ገንዘብ ከፍሎን ነው የሚል ነገር ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቆ ነበር። ገንዘብ ከፍሎ የሚለው ነገር ፈጽሞ ውሸት እንደሆነ ግልፅ ማድረግ ስለነበረብኝ እኔም አንዴ መልስ ሰጥቼ ነበር። አጋንንት እስራት ውስጥ ያሉትን ነፃ ለማውጣት ነው የተቀባሁት። ከፍዬ አጋንንት ማስጮኸው ለምንድን ነው? ከፍዬ የማስጮህ ከሆነ የቀን ገቢዬ አስር ሚሊዮን እንኳ ቢሆን አያዋጣኝም። ሰው ደግሞ የማያዋጣውን አይሰራም።

ማነው ነብይ ብሎ የሾመህ?

እዩ ጩፋ በዚህ ዓለም ሰው ሰውን የሚሾም ቢሆንም እውነተኛ ሿሚ እግዚአብሔር ነው። በቤተክርስትያን ከእኛ የቀደሙ ሰዎች በእኛ ላይ የተገለፀውን ፀጋ አይተው ወንጌላዊ፣ ዘማሪ ወይም ነብይ ብለው ይሾማሉ። እኔም በጣም በማከብራቸውና በምወዳቸው ቄስ በሊና ነው ሃዋርያ ተብዬ ሹመት የተሰጠኝ። ነገር ግን ከእሳቸው በፊት ቦዲቲ በሚባል ቦታ በማገለግልበት ወቅት ነብይ ሆኜ በቤተክርስትያን ሰዎች ተሹሜአለሁ። እንጂ እራሴን ነብይ ብዬ አልሾምኩም።

አንተ ቤተክርስትያን የሚያመልኩ ባለስልጣናት ወይም ታዋቂ ሰዎች አሉ?

እዩ ጩፋ ስማቸውን መጥራት ባያስፈልግም እስከ ሚኒስትር ደረጃ ያሉ አሉ። ግን ሰው ስለሚበዛ የስልጣን ደረጃቸው ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለው እንዲገቡ የማይፈቅድላቸው አሉ። እነዚህን ሰዎች በተለይ እንደ ሰዉ አጠራር ቪአይፒ አግኝቼ የማገለግልበት ጊዜ አለ።

የእግዚአብሔር ክብር ከእኔ ይበልጣል ብለው ቦታ ተይዞላቸው ከሰው ጋር ተጋፍተው የሚገለገሉም አሉ። ከአገር ውጪም ለትልልቅ ሰዎች ጸልዬ አውቃለሁ። ለምሳሌ ባለፈው ሱዳን ሄጄ ለፕሬዘዳንት ሳልቫኪር ቤተ መንግሥት ገብቼ ጸልያለሁ። ትልልቅ ሰዎችንም ወደ ቤተ ክርስትያን ጋብዤ አውቃለሁ።

ነቢይ እዩ ጩፋ

አጋንንት ማውጣትና ካራቴን ምን አገናኛቸው? ካራቴ ታበዛለህ

እዩ ጩፋካራቴ የተማርኩት አጋንንት ለማውጣት አይደለም። የለየለት ካራቲስትም አደለሁም። እኛ ጋ ከባህልና ከሁኔታዎች ጋር የተለመደ ነገር አለ። ከተለመደው ውጪ ሌላ አቅጣጫ ይዘሽ ስትነሺ ያስገርማል። አዲስ ነገር ነውና ካራቴው ያስገረመው፣ ያደናገረውና ያስደሰተውም አለ። ሁሌ ካራቴ ሁሌ አጋንንትን ጩኸና ውጣ አልልም። መንፈስ እንዳዘዘኝ ነው ማደርገው።

በጌታ በእየሱስ ስም ጩኸና ውጣ ብዬ አዝዤ የወደቀውን መንፈስ አንስተው ሲያመጡ በካራቴ መታሁት፣ በቴስታ መታሁት ምን ጉዳት አለው? በእጅም በእግርም ጥዬ አውቃለሁ ይህን የማደርገው አጋንንት የተመታና የተዋረደ መሆኑን ለማሳየት ካለኝ ፍላጎት የተነሳ ነው።

እግዚአብሔር መላ ሰውነቴን እንደሚጠቀም ማሳያም ነው። እኔ በካራቴ ከእኔ በኋላ ደግሞ በሌላ ስታይል አጋንንትን የሚመቱ ሊነሱ ይችላሉ፤ ይህ የራሴ ስታይል ነው። አንዳንዶች ካራቴውን የሚቃወሙት በቅናት፣ ሌሎች ደግሞ ከመፅሐፍ ቅዱስ ውጪ ነው በማለት ነው። ከካራቴም የተሻለ አሰራር ያላቸው ካሉ ግብዣዬ ነው።

በቀይ ቦኔቶች ተከበህ ስትንቀሳቀስ ይታያል። እንዴት ነው እንዲህ በወታደሮች የምትጠበቀው?

እዩ ጩፋ፡ አንድ ሚሊዮን ሁለት ሚሊዮን ሰዎች በሚገኙበት የሜዳ ላይ መንፈሳዊ ኮንፈረንስ ለህዝብ ደኅንነት ሲባል መንግሥት የጥበቃ ኃይል ያሰማራል። አንዱ ተጠባቂ እኔ ነኝ፤ ከጌታ በታች እኔን ይጠብቃሉ። ብዙ ሰው ግን እኔ ከፍዬ ያመጣኋቸው ይመስለዋል።

ብዙ የፖሊስና የወታደር ልብስ የለበሱን ከኋላህ አሰልፈህ “የእየሱስ ወታደር ነኝ”ን ስታዘምር የሚታይበት ቪዲዮም አለ?

እዩ ጩፋ፡ እሱ እኔ በክልል ባዘጋጀሁት ኮንፈረንስ ከመንግሥት የተቀበሉትን ሃላፊነት ሦስት ቀን በሥራ ላይ በታማኝነት በማሳለፋቸው በመዝጊያው ቀን ኑ ፖሊሶች ብዬ ጠርቼ የፀለይኩበት ነው። ምክንያቱም ለመንግሥት ለአገርም መፀለይ ስላለብን። እነሱም የመንግሥት አንድ አካል ናቸው።

ወደ አገር ጉዳይ ከመጣን፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ ፕሮቴስታንቶች በመንግሥት ከፍተኛ ስልጣን ላይ ናቸው ይባላል። ይህ ላንተ የተለየ ትርጉም አለው?

እዩ ጩፋ በአሁኑ ወቅት በጠላት አይን አገር እየፈረሰ ያለ ይመስላል በእኔ እይታ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከመጣ በኋላ አገር እየተገነባ ነው። ትልቅ ለውጥ መጥቷል። አንደኛው ለውጥ እግዚአብሔርን የሚያውቅና የሚፈራ መሪ ኢትዮጵያ ላይ መምጣቱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት እግዚአብሄር በትንቢታዊ መንገድ የሰጠኝን መልእክት አስተላልፌ ነበር። ዩ ቲውብ ላይ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚመጡ ቀድሞ እግዚአብሄር ተናግሮኝ ተናግሬአለሁ።የፖለቲካ መናጋቱና መናወጡ በየትኛውም ዘመን አለ። ኢትዮጵያ ከመቼውም በላይ ወደ ተነገረላት ከፍታ እየሄደች ያለችበት ጊዜ ላይ ነን።

ስለ ኢትዮጵያ ብልፅግና ካነሳህ የልምላሜ ተስፋ የተጣለበት የህዳሴው ግድብ ተሰርቶ የሚያልቅ፤ እውን የሚሆን ይመስልሃል?

እዩ ጩፋበእምነት የምትናገሪው ነገር አለ። እኔም የእምነት ቃል መስጠት እችላለሁ። በግሌ እንደ ቤተክርስትያን የጀመርናቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች አሉ። ሰው ሲያይ የማያልቅ የሚመስለው እኔ ግን እንደሚያልቅ አምናለሁ። ያልቃል የምለው ገንዘብ ስላለ ወይም በሌላ ምክንያት ሳይሆን አማኝ ሰው ስለሆንኩና እምነት የሁሉ ነገር ተስፋ ስለሆነ ነው። እንደዚሁ በእምነት አባይም ተገድቦ ያልቃል ብዬ አምናለሁ።

ፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑ ባለስልጣናት ስለመብዛታቸው ጠይቄህ ነበር . . . ?

እዩ ጩፋ፡ ፕሮቴስታንት ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚያውቁና የሚፈሩ በሚለው ብናገር ደስ ይለኛል። ከዚህ በፊት የነበሩት ባለስልጣናት እግዚአብሔርን ካለማወቃቸው የተነሳ ስልጣናቸውን ሰዎችን ለመጉዳት ተጠቅመውበታል። አሁን ግን ፕሮቴስታንት ባለስልጣናቱ ጌታን ስለሚፈሩ ጥሩ ሥራ ይሰራሉ ብዬ አምናለሁ እየሰሩም ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ቤተክርስትያንህ ጋብዘሃቸው ታውቃለህ?

እዩ ጩፋ አንድ ጊዜ ጋብዣቸው ነበር ግን በጊዜው ለሥራ ወደ ውጪ ሃገር ሄዱ። ከዚህ በኋላ ግን አንድ ፕሮግራም አለ እዚያ ላይ እንዲገኙ ደግሜ እጋብዛቸዋለሁ፤ እንደሚገኙም ተስፋ አደርጋለሁ።

ከጥቂት መታት በፊት አትታወቅም ነበር።ያጣህ የነጣህ ደሃ ሆነህ ታውቃለህ?

እዩ ጩፋ እዚህ ደረጃ ከመድረሴ በፊት ሰው በሚያልፍበት መንገድ አልፌአለሁ። ከመታወቄ በፊት ስለ እኔ ሰምተው የማያውቁ በሦስት በአራት ዓመት ወደ ስኬት እንደመጣሁ አድርገው ያስባሉ። ነገር ግን እጅግ አስቸጋሪና ዋጋ በሚያስከፍል መንገድ ነው የመጣሁት።

ብዙ ተከታዮች አሉህ ብዙ ሰዎች የተማሩና በኢኮኖሚም ጥሩ ቢሆኑ ይህን ያህል ተከታይ የሚኖርህ ይመስልሃል?

እዩ ጩፋ እንደ አሜሪካ የሰለጠነና የበለፀገ አገር ላይም ቢሆን ተከታይ ይኖረኛል ብዬ ነው ማስበው። በጥረቴም በፍልስፍናም አይደለም ሰው የሚከተለኝ። ህዝቡ እንዲከተለኝ የሚያደርግ የእግዚአብሄር ሞገስ ስላለ እንጂ። ሰዎች ድሃ ስለሆኑና ስላልተማሩ ይከተሉኛል ብዬ አላስብም። ጥግ ድረስ የተማሩና ባለፀጎችም አብረውኝ አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያዘጋጁት “ገበታ ለሸገር” ላይ ጋብዘውህ ነበር?

እዩ ጩፋአልሰማሁም አጋጣሚ አገር ውስጥም አልነበርኩም።

አረቦች ለፈውስ ወደ አንተ እንደመጡ የሚያሳዩ የተለያዩ ቪዲዮዎችን አይቻለሁ። የሶሪያ ስደተኞች ናቸው ወይስ አንተን ብለው የመጡ?

እዩ ጩፋ እስከማውቀ እኔ ጋር እግረ መንገዱን የመጣ የውጭ አገር ሰው የለም። ፕሮግራም አስይዘው ትኬት ቆርጠው ነው የሚመጡት። ከኢራን፣ ኢራቅ፣ ዱባይና ኦማን ፕሮግራም አስተርጉመው የሚሆነውን ተአምራት እያዩና እየሰሙ ይመጣሉ።

ምን ያህል ሃብት አለህ?

እዩ ጩፋሃብቴ የማይመረመር የማይቆጠር ሰማያዊ በረከት ነው። በዓለማዊው የባለጠጋ መለኪያ ራሴን እንዴን እንደምገልጽ ግን እንጃ። አገልጋይ ነን ቤተክርስትያንን የምናንቀሳቅስበት ብር ይመጣል። መባ፣ አስራትና ስጦታ እያገኘን ያንን ደግሞ መልሰን ለአገልግሎት እናውላለን። እንደሚታወቀው በአንድ ጊዜ አስራ አራት ሺህ ሰው የሚያስተናግድ 97 ሚሊዮን ብር የሚያስወጣ የአዳራሽ ግንባታ እያካሄድን ነው። በአንድ ዓመት ውስጥ ያልቃል።

በግል ያለህ ምድራዊ ሃብትስ?

እዩ ጩፋእስካሁን ያለኝ የማሽከረክረው መኪና ነው።

ወንጌልን ከመስበክ ይልቅ ፈውስና ተዓም ላይ ያተኩራል እየተባልክ ትተቻለህ?

እዩ ጩፋቅድሚያ የምሰጠው ለወንጌል ነው። ተዓምራት ወንጌል ከሌለ የለም።

ቃል ለወጣበት ዘይት(የተፀለየበት ዘይት) እስከ ሁለት ሺህ ብር ታስከፍላለህም ይባላል?

እዩ ጩፋ የተፀለየበት ዘይት(አኖይንቲንግ ኦይል) ሰዎች እኔ መድረስ የማልችልባቸው ቦታዎች እየወሰዱ እንዲፈወሱበት ነው ያዘጋጀነው። አሜሪካ፣ አውሮፓና አረብ አገር እየገባ ነው። አገር ውስጥም በየሰው ቤት እየገባ ነው። እኛ ቤተ ክርስትያን የገባ ሁሉ ይውሰድ የሚል መመሪያ ግን የለም። በነፃ ግን አይሰጥም ምክንያቱም ቤተክርስትያናችን የዘይት ፋብሪካ የላትም። ዘይቱ የሚመጣው ከውጭ ተገዝቶ ነው። ዘይቱ የሚታሸግበት ጠርሙስም የሚመጣው ከውጭ ነው። የጠርሙስ ክዳን፣ ጠርሙስ ላይ የሚለጠፍ ስቲከርም ማምረቻ ፋብሪካ የለንም። ይህን ሁሉ በገንዘብ ስለምናገኝ ነው በገንዘብ የምንቀይረው።

የምትጠይቁት ብር የተጋነነ አይደለም ወይ?

እዩ ጩፋ፡ አልተጋነነም እንዲያውም እኛ እንደ ቢዝነስ ሰው ብናስብ፤ ዶላር ስለጨመረ ዘይት ጨምሯል ብለን ዋጋ መጨመር እንችላለን። ለቲቪ በወር እስከ 640 ሺህ ብር እንከፍላለን። የቤተክርስትያን ኪራይ፣ የወንበር ኪራይ፣ የአገልጋዮች ክፍያና የሳውንድ ሲስተም የመሰሉ ወጪዎችም አሉ።

‘ወንጌላይ’ የተሰኘው መዝሙር ክሊፕህ፤ ይህንኑ መዝሙር መድረክ ላይ ስትዘምረውም እንቅስቃሴው የወላይተኛ ጭፈራ ነው። እንዴት ነው እንዲህ ፈጣሪ የሚመሰገነው? የሚሉ ሰዎች አሉ።

እዩ ጩፋ ጨፋሪዎች ናቸው ከእኛ የኮረጁት። የወላይታ ባህል ጭፈራ ምን እንደሆነ ሳላቅ ለእግዚአብሔር ጨፍሬአለሁ። በቤተክርስትያን ሰው የለመደው ሽብሸባ[ተነስቶ እያሸበሸበ] ስለሆነ ነው። ይሄኛው እንቅስቃሴ ለዘፈን፤ ያ ለእግዚአብሄር ተብሎ የተፃፈ ነገር የለም፤ ሁሉም የእግዚአብሔር ነው። ስለዚህ እኛ ወደፊት የዘፋኞችን እንቅስቃሴ ሁሉ ለእግዚአብሔር ገቢ እናደርጋለን።

አለባበስህ ለየት ያለ ነው የልብስ ዲዛይነር አለህ?

እዩ ጩፋ፡ አዎ ዲዛይነሮቼ ግብፃዊያን ናቸው ልብሴ እዚያ ነው የሚሰራው።

Source BBC Amharic