መቃብሩ ባዶ ሆነ ምድርም በብርሃን ተመላች


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


እውነተኛ አምላክ፣ የእውነት መምህር፣ የማይመረመር፣ የማይሸነፍ፣ ሁሉን የሚያደርግ፣ ሁሉን የሚገዛ፣ በምድርም በሰማይም ያለ እርሱ ምንም ምንም የሆነ ነገር የሌለ ነው፡፡ ጌታ የጠፋውን የሰው ልጅ ሊያድን ወደ ምድር መጣ፡፡ አስቀድማ በተመረጠች ንጽሂት እመቤት በምትሆን አደረ፡፡ በእርሷም ተወለደ፡፡ ልደቱን ዘር አልቀደመውም፡፡ ከሐጢያት በቀር ሁሉን እያደረገ እንደ ሰው አደገ፡፡ ከመወለዱ አስቀድሞ ነብያት የተነበዩት እየተፈጸመ አደገ፡፡ ከድንግል ማርያም እንደሚወለድ አስቀድመው ተናገሩ – ተወለደም፡፡ በዮርዳኖስም እንደሚጠመቅ ተናገሩ -ተጠመቀ፡፡ በዕለተ አርብ እንደሚሰቀልም ተናገሩ – ያም ሆነ፡፡

No photo description available.በምድር ታማራትን አደረገ፡፡ ድውያተ ስጋን በታምራት፣ ድውያተ ነብስን በትምህርት ፈወሰ፡፡ ይህም መልካም ሥራው አልተወደደለትም፡፡ ቃሉን የሚፈፅመበት ቀን ቀረበ፡፡ በሐሰተኞች እጅ ተያዘ፡፡ ራሱንም አሳልፎ ሰጠ፡፡ በሐሰተኞች ጭፍራ ተይዞ ተንገላታ፡፡ መራራ አጠጡት፣ ገፉት፣ አዳፉት፣ ገረፉት፡፡ ሄሮድስ ጌታን አቃለለው፡፡ በውሸታሞች ገበያ ውስጥ የእውነት ድምፅ አይሰማም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በበደለኞች ፊት ነበርና እውነቱን የተመለከተው አልነበረም፡፡ ከእርሱ ይልቅ በርባን ይፈታ ክርስቶስ ይሰቀል ተባለ፡፡ ፍርዱ የሐሰተኞች ነውና፡፡

የመሰቀያው ጊዜ ደረሰ፡፡ ወደ ቀራንዮም ይዘውት ወጡ፡፡ የክርስቶስን ስቃይና መከራ ያዩ የኢየሩሳሌም ሴቶች ደረታቸውን እየደቁ፣ ወደመሬት እየወደቁ፣ ያለቅሱ ነበር፡፡ እርሱ ግን ʺ እናንት የኢየሩሳሌም ሴቶች ለእኔ አታልቅሱ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ፤ መካን የሆነች ያልወለደችም ማሕፀን፣ ያላጠቡም ጡቶች ንዑዳን ክቡራን ናቸው የሚባልበት ዘመን ይመጣል ” አለ፡፡ መከራ አበዙበት፣ ሰውን ወዷልና፡፡ ለፍፁም ፍቅር ሲል ታገሰ፡፡

መስቀሉን እንደያዘ ወደ ምድር ተደፋ፡፡ መጨነቅ አበዙበት፣ ተሰቃዬ፣ መልካም አምላክ፣ ሁሉን አድራጊ ሆኖ ሳለ እንደሚታረድ ጠቦት ወደ መታረጃው ተነዳ፡፡ እስከ መሰቀያውም እየመቱ እየገፉና እያዳፉ ወሰዱት፡፡ ቀራንዮም ደረሰ፡፡ ከመስቀሉ ላይ አስተኙት፡፡ ዝም አለ፡፡ ደረቱን በችንካር ከነቸሩት፡፡ በደረቱ የከነቸሩት ክንቻርም በጀርባው ዘልቆ ወጣ፡፡ ደም ፈሰሰው፡፡ ደሙም እርሱን ያመኑት ሁሉ የዘላለም ሕይወት ነውና መላእክት በእሳት ፅዋ ደሙን ተቀበሉ፡፡ እጆቹንም ቸነከሯቸው፤ ደምም ፈሰሰው፡፡ እግሮቹንም ቸነከሯቸው፣ ደምም ፈሰሰው፡፡ መላእክትም የሚፈሰው ደሙን በእሳት ፅዋ ተቀበሉት፡፡

መከራው ፀና፣ ዓለም ተረበሸች፣ የምትሆነውን አጣች፣ ፍርሃት መጣ፣ ስጋት አንዣበበ፣ እውነተኛና ሐሰተኛ የሚፈተንበት ጊዜ ደረሰ፡፡ በችንካር መትተው ሰቀሉት፡፡ ሁሉን አድራጊ ሆኖ ሳለ እንደ በደለኛ ተቆጠረ፡፡ የሚሰድቡት በረከቱ፡፡ የእርሱ ሕመም አሟቸው የሚያለቅሱትም ሐዘናቸው በዛ፡፡

እናቱ ማርያም አምርራ አለቀሰች፤ አዘነች፣ የተወደደ ልጇን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስታዬው ተጨነቀች፡፡ ሰባቱ የመላእክት አለቆችም ወደ እርሷ መጡ፡፡ አጽናኗትም፡፡ እርሷ ግን የልጇን ስቃይ እያዬች ማልቀስን አላቆመችም፡፡ ዳዊትም በእሳታዊ ፈረስ መጣ፡፡ አይዞሽም አላት፡፡ የእናት አንጄት እንቢ ቢላት ከማልቀስ አላቆመችም፡፡ የእናት አንጀቷ ተላወሰ፡፡ በተባረከው ስጋዋ እንባዋ እንደ ቦይ ፈሰሰ፡፡ ክርስቶስም ከመስቀሉ ግርጌ ሆና የምታለቅሰውን እናቱን ተመለከተ፡፡ ከሀዘኗ ትረጋጋ ዘንድም የሚወደውን ደቀ መዝሙር ዮሐንስን እነኾት ልጅሽ አላት፡፡ ለደቀመዝሙሩ ዮሐንስም ከሀዘን የምታረጋጋ፣ የመዳን ተስፋ የሆነች እናት ሰጠው፡፡ እነዃት እናትህ አለው፡፡
እርሷ ግን አብዝታ አለቀሰች፡፡ የማንስ ልብ ይጨክናል ልጁ በመስቀል ላይ ተሰቅሉ እያዬ፡፡ ከመስቀሉ ግርጌ እንባዋ አብዝቶ ፈሰሰ፡፡ ጸሐይ ብርሃኗን ከለከለች፣ ምድር ተናወጸች፣ ኢየሩሳሌምን ጨለማ ወረሳት፡፡ ሰዎች ሁሉ ተጨነቁ፡፡ ጨረቃ ደም ለበሰች፡፡ አለቶች ተሰነጣጠቁ፤ መጋረጃው ተከፈለ፡፡ ከዋክብት ረገፉ፤ ዓለም ድብልቅልቋ ወጣ፡፡ ትንቢት ተፈፀመ፡፡ ʺሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” እንዳለ ቃሉን ሊፈፅም የመጣው አምላክ ሳያጓድል ፈፅሟልና ʺተፈፀመ” አለ፡፡ ነብሱን ከስጋው ለዬ፡፡ የሞትም የድኅነትም አምላክ ሆኖ ሳለ ሞትን ይሽረው ዘንድ የማይሞተው ሞተ፡፡ ሞቶም ያዝዛል፤ ሞቶም ይገዛል፤ ሁሉም በእርሱ ነውና ያለ እርሱ የሆነች አንዳችም ነገር አልነበረችም፡፡ በነብስ የሞተውን የሰውን ልጅ በስጋው ሞቶ ለማዳን ሞተ፡፡

ማርያምም እስከ ሶስት ቀን ድረስ ምንም ሳትቀምስ ልቧ በሀዘን ተመልቶ ቆዬች፡፡ ክርስቶስን የሰቀሉት ሁሉ ስለ ጀብዶቻቸው ያወራሉ፡፡ ዮሴፍና ኒቆዲሞስም የክርስቶስን ስጋ አውርደው ይቀብሩት ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፡፡ ጲላጦስም ይሁንታውን ሰጠ፡፡ ከመስቀሉም አወረዱት፡፡ ʺሞትን ድል የምትነሳ ጌታ ሆይ ተኛህን”? ሞትስ በአንተ ላይ እንደምን ሰለጠነ? ” እያሉ አለቀሱ፡፡ ምድር አዘነች፡፡ ፍጥረታት በፈጣሪያቸው መሞት አዘኑ፤ ደነገጡም፡፡

ዮሴፍና ኒቆዲሞስም ክርስቶስ እንደነገራቸው ʺቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት፤ ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ ኦግዚኦ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት፤ ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ፣ ወተሰቅለ ዲበ እጸ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት፤ ዘተንሥኣ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት ዐረገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽእ በስብሐት ይኮንን ሕያዋነ ወሙታነ ተሣሃለነ እግዚኦ፤ ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን” እያሉ ገነዙት፡፡ በፈቃድ ሞተ በፈቃድ ተገዘነ፡፡ ክርስቶስ ተቀበረ፡፡ መቃብሩንም በድንጋይ ዘጉት፡፡

የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ተሰባስበው ደቀመዛሙርቱ ክርስቶስ ተነስቷል እያሉ ሕዝቡን እንዳያውኩ መቃብሩ እንዲጠበቅ ለጲላጦስ ነገሩ፡፡ መቃብሩም በጭፍሮች ተጠበቀ፡፡ እነርሱን የሚጠብቃቸውን አምላክ በመቃብር ውስጥ ሊያስቀሩ ጠበቁት፡፡ ጠባቂዎችም እስከ ሦሥት ቀን ጠበቁ፡፡ የመነሳት ጊዜ ደረሰ፡፡ የረገፉት ከዋክብት ሰማያትን ያደምቁ ጀመሩ፡፡ ጨረቃ ፊቷን ገለጠች፡፡ ያዘነው ልብ ሊረጋጋ ቀረበ፡፡ ጎለጎታ በአስፈሪ ድምፅ ተጨነቀች፡፡ ብርሃናት መሉ፡፡ የብርሃን አለቃ ሁሉ በእርሱ የሆነ ጌታ በስልጣኑ ተነሳ፡፡ ሞት በእርሱ ስልጣን የለውም፡፡ ሞትን በራሱ ፈቃድ የሻረና የገደለ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ መቃብር የሚጠብቁ ጭፍሮች አላዩትም፡፡ በጎለጎታ ግን ክርስቶስ የለም፡፡ ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷልና፡፡ የሲኦል ነብሳት ተስፋቸው ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎላቸዋልና በደስታ ዘለሉ፡፡ ወደ አባታቸው እቅፍ ሮጡ፡፡ በክርስቶስ መሰቀልና መሞት አዝነው የነበሩት ደስታቸው ወሰን አጣ፡፡ ሞት በሞት ተሽሯልና፡፡ የገነት ደጆች ተከፈቱ የሲኦል ደጆችም ተዘጉ፡፡ ዲያቢሎስ አፈረ፣ ተሸነፈም፡፡ ክርስቶስ መግነዙን ትቶ ልብሰ መንግሥቱን ለበሰ፡፡ የሰማይ መላእክት ነጫጭ እየለበሱ የተነሳውን ጌታቸውን አመሰገኑት፡፡

ʺከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም፡፡ እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ እነሆ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። የሰው ልጅ በሐጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ።

ቃሎቹንም አሰቡ፡፡ ከመቃብሩም ተመልሰው ይህን ሁሉ ለአሥራ አንዱና ለሌሎች ሁሉ ነገሩአቸው። ይህንም ለሐዋርያት የነገሩአቸው መቅደላዊት ማርያምና ዮሐና የያዕቆብም እናት ማርያም ከእነርሱም ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ። ይህም ቃል ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም። ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት የተልባ እግር ልብስን ብቻ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ” እንዳለ መጽሐፍ፡፡
ሊቃውንት ʺኢየሱስ በተወለደም ጊዜ የእናቱን ማሕጸን እንዳለወጠ ሁሉ በትንሳኤውም መገነዝ ፍቱልኝ፤ መቃብርም ክፈቱልኝ ሳይል ተነሳ ” ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዲሳት መምህርና በማሕበረ ቅዱሳን የአብነት ትምህርት ቤቶች ስልጠና ባለሙያ መምህር እንዳልካቸው ንዋይ የትንሣኤ በዓል እስከ ዘመነ ዲምጥሮስ ድረስ እሁድን ሳይጠብቅ ይከበር ነበር፡፡ ዲምጥሮስ ከተነሳ በኋላ ግን ሱባኤ ገብቶ ጥንተ እለቱን እንዳይለቅ አደረገ፡፡ ይህም ስቅለቱም አርብ ትንሣኤውም እሁድ እንዲሆን አዘጋጄው ነው ያሉት፡፡ የክርስቶስን ትንሣኤም ማክበር የጀመሩም ሐዋርያት ናቸው፡፡

ክርስቶስ ለክርስቲያኖች መመኪያ አለኝታ ነው፡፡ ሞትን ሞት አድርጎ የተነሳ ነውና፡፡ በደሙም ሃይማኖታቸውን አነፀ፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ የተበታተኑትን ይሰበስባል፣ የተራራቁትን ያቀራርባል፣ የተሰበሩትን ይጠግናል፣ ያዘኑትን ያረጋጋል፤ ተስፋ ለቆረጡት ተስፋ ይሆናል፡፡ ሰላም ለእናንተ ይሁን እንዳለ ትንሣኤውን በመልካም ልብ ለሚያከበሩ ሁሉ ሳለም ይመጣል ይላሉ አበው፡፡ ክርስቲያኖች ድል ያደረገው የክርስቶስ ልጆች ናቸውና ትንሣኤውን ሲያከብሩ ነጭ ለብሰው ያከብራሉ፡፡ ለምን ካሉ የድል ዘመን ደርሷልና፤ መላእክት በትንሣኤው ነጭ ለብሰዋልና፣ እርሱም የሚያበራና የሚያስፈራ ብርሃን አሳይቷልና፡፡ ትንሣኤ የበዓላት ሁሉ አክሊል ነውም ይላሉ አበው፡፡ በምድር መካከል መዳን አደረገ እንዳለ በቃራንዮ መዳንን አደረገ፡፡

ክርስቶስ ተነሳ፡፡ ምድርም በብርሃን ተመላች፡፡ ያዘኑት ሁሉ ተጽናኑ፡፡ የጨለመው ዓለም በብርሃን ተለወጠ፡፡ የፍዳ ዘመን አበቃ፡፡ የምህረት ዘመን መጣ፡፡ እነሆ ይህች ቀን ለክርስቲያኖች ኃያል ቀን ናት፡፡ እነርሱም በፍፁም ፍቅር፣ በታላቅ ክብር፣ በታላቅ ደስታ ያከብሩታል፡፡ ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ ተነስቷልና እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ መልካም በዓል፡፡

ምንጭ፡–  በታርቆ ክንዴ – (አሚኮ)