ከሚደርስብን ጥቃት ቀድሞ ደርሶ ሊታደገን የሚችል አካል አላገኘንም – ሆሮ ጉድሩ ወለጋ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የጸጥታ ችግር እንዳለና በስጋት ውስጥ መሆናቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች ለአሚኮ ተናግረዋል። ባሳለፍነው እሁድም በተፈጸመ የተደራጀ ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን፣ በሀብትና በንብረት ላይ ዝርፊያና ውድመት መድረሱን ነግረውናል፡፡ ግድያው ማንነትን መሠረት ያደረገ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች እንዳሉት ከስምንት ቀናት በፊት ጀምሮ በአካባቢው ውጥረት ነበር፡፡ ችግሩን ለጸጥታ አካላት ቢያሳውቁም በወቅቱ የደረሰ አካል ባለመኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለተደራጀ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ገልጸውልናል፡፡

ከነፍስወከፍ እስከ ቡድን መሣሪያ የታጠቁ አካላት ምንም የፖለቲካ እውቀትና አመለካከት በሌላቸው ንጹኃን አርሶ አደሮች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ህጻናት እና ሴቶች ላይ ጭምር ግድያ እንደፈጸሙ ነው የተናገሩት፡፡

የጸጥታ ኃይል ወደ ስፍራው የገባው ሰዎች ከሞቱ፣ የእምነት ተቋምና የሰዎች መኖሪያ ቤት ከተቃጠለና ሀብት ከወደመ በኋላ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት ወደ ቦታው ከገቡ በኋላ ተኩሱ ቢቆምም ነዋሪዎች በደኅንነት ስጋት አካባቢያቸውን ለቅቀው በአቅራቢያ ወደምትገኘው ቱሉጋና ከተማ እየሸሹ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ በዕምነት ተቋማት የተጠለሉ ቢሆንም አሁንም ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፤ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍም እንዲደረግላቸው መንግሥትን ጠይቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንም ግድያ መፈጸሙን አረጋግጧል፡፡ ኦነግ ሸኔ ንጹኃንን በመግደልና በማፈናቀል የብሔር መልክ ለማስያዝ እየጣረ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ኢታና በሆሮ ጉድሩ ወለጋ አቤ ደንጎሮ ወረዳ የተፈጸመው ጥቃት ብሔር ተኮር አደለም ባይ ናቸው፤ የኦሮሞ ተወላጆችም ጭምር እየተገደሉ መሆኑን በማሳያነት በማንሳት፡፡

ይሁን እንጂ ኦነግ ሸኔ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብን ለማጋጨት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ከኦነግ ሸኔ ውጪ በክልሉ ተንቀሳቅሶ የሽብር ሥራ የሚሠራ ተላላኪ ቡድን የለም›› ብለዋል፡፡ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች በጥፋት ቡድኑ ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም አመላክተዋል።

ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ ጥቃት የተፈጸመባቸውን አካባቢዎች ለማረጋጋትም ከፌዴራል የጸጥታ አካላትና ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹የጥፋት ቡድኑን› ለማጥፋት ሁሉም በጋራ መሥራት እንደሚገባውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡