በገበያ የሚታየው የዋጋ ንረት በሰበብ አስባቡ ጠዋት እና ከሰዓት በኋላ የዋጋ ልዩነት ማሳየት ጀምሯል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት እና በኑሮ ውድነቱ የተማረሩት የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሁሌም ለሸቀጦች ዋጋ መጨመር ነጋዴው ምክንያት የሚሰጣቸው የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና የዶላር ምንዛሬ ዋጋ መናርን እንደሆነ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

BBC Amharic : “ፈሳሹ ዘይት ተፈልጎ አይገኘም” የሚሉት እኚህ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ ከዚህ ቀደም አንድ እንጀራ በ10 ብር ይገዙ እንደነበር አስታውሰው 12 ብር መግባቱን በምሬት ይናገራሉ።

በእጃቸው ጤፍ የያዙ እናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኑሮ ውድነቱ ግን አዲስ አበባን መኖሪያቸው ያደረጉትን ብቻ አይደለም የተጫነው፣ በሐረር ከተማ የሚኖሩት ወ/ሮ ሽርካ አሕመድ ዘንድሮ የገጠማቸው የዕቃዎች ዋጋ መጨመር ከዚህም በፊት ከነበረው ሁሉ የተለየ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ኑሮ እጅግ ተወዶብናል። ለምሳሌ አንድ ኪሎ ቲማቲም 12 ብር የነበረው በአሁኑ ሰዓት 25 ብር ገብቷል። ከጥቂት ቀናት በፊት በ265 ብር ይገዛ የነበረው ዘይት 430 ገብቷል። ከሶስት ወራት ወዲህ ያልጨመረ አንድም ነገር የለም። ከአቅማችን በላይ ሆኗል” ሲሉ ተስፋ በመቁረጥ ይናገራሉ።።

ወ/ሮ ሽርካ በሁሉም እቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ‘ዶላር ስለጨመረ ነው’ ሲባል ከመስማት ውጪ ምክንያቱ ይህ ነው ብሎ ያስረዳቸው የለም።።

በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩት የአጋሮ ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ እመቤት ከድር በበኩላቸው፣ በገበያ የሚታየው የዋጋ ንረት “ጠዋትና እና ከሰዓት በኋላ የዋጋ ልዩነት ማሳየት ጀምሯል” ይላሉ።

“እኔ የችርቻሮ ነጋዴ ነኝ፤ ከኅብረተሰቡ ጋር በቀጥታ እገናኛለሁ፤ እኛ ደግሞ ከጅምላ አከፋፋዮች እንገዛለን። እኛ እነርሱን ስንጠይቅ፣ የጨመረው ከላይ ነው ይሉናል፤ ግልጽ የሆነ ምክንያት የለም። እኔ አሁን ይህንን የሕዝብ ምሬት መስማት አቅቶኝ ሥራዬን እያቆምኩ ነው” ይላሉ ወ/ሮ እመቤት።

አክለውም “አንድም ዋጋው አልጨመረም የምንለው ነገር የለም። አንተ ጠዋት አንድ እቃ ከሸጥክ፣ ከሰዓት በኋላ ዋጋው ጨምሯል። እቃው ግን ያው ጠዋት የነበረው ነው። ተገቢ ቁጥጥር መደረግ አለበት” ሲሉ ለመፍትሄው የመንግሥትን እጅ ይማፀናሉ።

የዶላር ኖቶች

የነዳጅ ዘይት እንደ ሰበብ

በዚህ ወር ውስጥ ዋጋቸው ከጨመረ ነገሮች መካከል የነዳጅ ዘይት አንዱ ነው። በዚህም ምከንያት የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ማስተካከያ ተደርጓል።

ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባው የነዳጅ ዘይት በሁለት አቅጣጫዎች፣ በሱዳን እና ጅቡቲ በኩል የነበረ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሱዳን በኩል የሚገባው መቋረጡን የቢሮው ኃላፊዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አለማየሁ ፀጋዬ በሱዳን በኩል የሚገባው ነዳጅ ቢቋረጥም፣ አገሪቷ ከውጪ በምታስመጣው ነዳጅ ላይ ግን የታየ ለውጥ የለም ይላሉ።

“በነዳጅ አቅርቦት ላይ ከዚህ በፊት በነበረው ላይ ልዩነት የለም። በሱዳን በኩል ይገባ የነበረው ቤንዚን ብቻ ነው። እንደውም በጥገና ምክንያት ይገባ ከነበረው የቀነሰ እና ለተወሰኑት ከተሞች ብቻ ሲቀርብ የነበረ ነው። በኮሮናቫይረስ ምክንያት ደግሞ ይገባ የነበረው ራሱ ተቋርጦ ነው የቆየው” መሆኑን ገልፀዋል።

በሱዳን በኩል ይቀርብ የነበረው ነዳጅ፣ ቀድሞ የተቋረጠ እና በሁለቱ አገራት መካከል ካለው የድንበር ውዝግብ ጋር የማይገናኝ መሆኑንም ጨምረው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ነዳጅን ከመካከለኛው ምስራቅ፣ በጅቡቲ በኩል እያስገባች መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የሚናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው፣ በሱዳን በኩል የነበረው አቅርቦት ከተቋረጠ ወዲህም የአቅርቦት እጥረት አልተፈጠረም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከሰላሳ በላይ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች ከውጪ የሚገባውን ይህንን ነዳጅ ለተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያቀርባሉ።

በነዳጅ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪም ከዓለም ገበያ ዋጋ ጋር የተያያዘ እንጂ በአቅርቦት መቀነስ ምክንያት እንዳልሆነ ኀብረተሰቡ ሊረዳ ይገባል ሲሉ አቶ አለማየሁ ፀጋዬ ያስረዳሉ።

የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋን የሚወስነው የንግድ ሚኒስቴር በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ምርቶች ዋጋ የጨመረበትን ምክንያት ለማጣራት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በሐረር ገበያ ውስጥ ያሉ ነጋዴ

ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ የማይታየው የኑሮ ውድነት

የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ጉቱ ቴሶ አሁን በኢትዮጵያ ለገጠመው የኑሮ ውድነት ምክንያቶቹ በርካታ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

ቀዳሚዎቹ ግን ከዓመት ዓመት መጨመር እንጂ መቀነስ የማያሳየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አንዱ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ይህ በየዓመቱ መጨመር ብቻ የሚያሳየው የዋጋ ግሽበት መንስዔው መሠረታዊ የሆኑ የምጣኔ ኃብት መዋቅሮች አለመስተካከል ጋር ተያይዞ መሆኑን ገልፀዋል።

ቀሪዎቹ ደግሞ ወቅታዊ የሆኑ እና የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት ፈተና ውስጥ የሚጥሉ ክስተቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፥።

ዶ/ር ጉቱ የምርት አቅርቦት እየቀነሰ መምጣት፤ የሰላም መታጣት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ መፈናቀሎች ለገበያው ዋጋ መናር ምክንያቶች መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ።

በአገሪቱ ውስጥ የተካሄዱ ሕዝባዊ አመጾች፣ የተደረጉ ተከታታይ የገበያ እቀባዎች፣ የንግድ ሰንሰለቱን በተጋጋሚ መሰበራቸውን፣ በተለይ ደግሞ ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎች በሰላም እጦት ምክንያት ተደራራቢ ጫና መፍጠሩን ያስረዳሉ።

ገበሬው በሰላም እጦት ምክንያት ቢያርስ እንኳ አልጎለጎለም የሚሉት ባለሙያው፣ የጎለጎለው መዝራት ሳይችል ሲቀር፣ የዘራ ደግሞ መሰብሰብ አለመቻሉ የእርሻ ምርቶች አቅርቦት እየቀነሰ እንዲመጣ ማድረጉን ይገልጻሉ።

የምጣኔ ኃብት ባለሙያው አክለውም በርካታ ኢንደስትሪዎችም ከውጪ አገር ግብዓት ስላላገኙ ወይንም በሰላም እጦት ፍራቻ ምክንያት ምርት መቀነሳቸው ወይንም ማቆማቸው ሌላው ለኑሮ ውድነቱ አስተዋጽኦ ካደረጉ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

እነዚህ ማምረት የሚያቆሙ ኩባንያዎች በበዙ ቁጥር ለኑሮ ውድነቱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የሚገልጹት ዶ/ር ጉቱ፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ተደራርበው የኑሮ ውድነትን ማክበዳቸውን ይገልጻሉ።

“ከ2017 እስከ 2021 (እኤአ) የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም በ54 በመቶ ወርዷል፤ በአጠቃላይ ሲታይ በአስር ዓመታት ውስጥ የኢትዮጰያ ብር የመግዛት አቅም በመቶ እጅ ወድቋል” የሚሉት ዶ/ር ጉቱ፣ የምግብ አቅርቦትና ሌሎች የዕለት ፍጆታ የሆኑ ምርቶች የብር የመግዛት አቅም በወደቀበት በዚህ ጊዜ ከውጪ ሲገቡ የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብሱ ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ምርት የሚያመርቱ አብዛኞቹ ኢንደስትሪዎች ከውጪ በሚገባው ግብዓት ላይ የተንጠለጠሉ በመሆናቸው ይህንን ችግር ለመፍታት ያላቸውን ሚና ማሳነሱንም ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ ከቀጠለ አገሪቷን ውስብስብ ወደ ሆነ ችግር ሊመራት እንደሚችል ባለሙያው ይመለክታሉ።

“ሰው በኢኮኖሚ ሲዳከም ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ይሰደዳል። እንደዚህ ዓይነት ስደት ደግሞ በከተሞች ላይ ማህበራዊ ቀውስን ያስከትላል። የሚበላው ያጣ ሕብረተሰብ ደግሞ ወደ ተቃውሞ እና ሽብር ይሄዳል። ይህ ደግሞ አሁንም ምልክቱ እየታየ ነው” ብለዋል።

የሥራ ማጣት፣ የኑሮ ውድነት እና ሌሎች ምክንያቶች ችግሮች፣ መጀመሪያውኑ አሁን ካለንበት አዙሪት ውስጥ እንዳንወጣ ያደርጉናል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጨምረው ይናገራሉ።

በማዳበሪያ የተቀመጡ እህሎች

መፍትሔው ምንድን ነው?

የኑሮ ውድነትን ጨምሮ ለበርካታ የአገሪቱ ችግሮች መነሻ የሆነው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የመጀመሪያው ምርጫ መሆን እንዳለበት ዶ/ር ጉቱ ያመለክታሉ።

“ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንት የለም፣ ወደ ውጪ መላክ የለም፣ ምርትን አጓጉዞ ማከፋፈል የለም። ሰላም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መኖር ያለበት ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥትና ሌሎች ድርጅቶች አብረው ሆነው መወያየት አለባቸው። ግጭት ከሁሉም ወገን መቆም አለበት” ሲሉ ይመክራሉ።

የውጪ ምንዛሬ ላይ በፍጥነት ማስተካከያ መደረግ አለበት የሚሉት የምጣኔ ኃብት ባለሙያው፣ በዚህ ሁኔታ አገሪቱ ከቀጠለች አስቸጋሪ የምጣኔ ኃብት ቅርቃር ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ገልፀዋል።

ብር የመግዛት አቅሙ ከቀን ወደ ቀን መቀነሱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም እንዳለበትም ይመክራሉ።

አሁን ያለው የውጪ ምንዛሬ ከዚህም ባነሰ በ30 እጅ ወደ ኋላ መመለስ አለበት ይላሉ። አሁን የብርን ዋጋ እንዲወርድ ማድረግ በኢንቨስትመንትም ሆነ በውጪ ንግድ አንጻር ለኢትዮጵያ የሚያመጣው ፋይዳ የለውም ብለዋል።

የአገሪቷን ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግ፣ የባህልና ማህበረሰባዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ አለበትም የሚሉት ዶ/ር ጉቱ፣ የህዝቦች የሥራ ባህልም ላይ መሻሻል መደረግ አለበት በማለት ሃሳባቸውን ያጠናቅቃሉ።