በእንግሊዝና ደቡብ አፍሪካ የተገኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያን ያሰጋታል ተብሏል።

  • አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ኢትዮጵያንም እንደሚያሰጋ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
  • በእንግሊዝና ደቡብ አፍሪካ የተገኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያን ያሰጋታል ተብሏል።

የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የአስቸኳይ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ 19 ምላሽ ምክትል አስተባባሪ አቶ ዘውዱ አሰፋ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ ራሱን ቀይሮ ሊመጣ እንደሚችል ይጠበቅ ነበር ብለዋል፡፡

ሆኖም ግን አሁን የተገኘው ቫይረስም እንደሌሎች የአለም ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያንም ያሰጋታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቫይረሱ እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ ስለመግባቱ የሚያመላክት መረጃ የለም ያሉት አቶ ዘውዱ ህብረተሰቡ እራሱን ከቫይረሱ መከላከል የሚያስችሉ የመከላከል እርምጃዎችን ማድረጉን እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ለዚህም የቫይረሱ አሁንም ያልታወቁ ባህሪያት መኖርን እንደምክንያት ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም አስቀድሞ ለመከላከል ጤና ሚኒስቴርና ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንዳለ ነግረውናል።

አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ለመጀመርያ ጊዜ በእንግሊዝ የተከሰተ ሲሆን አገሪቱ የቫይረሱ ስርጭት ከአቅሟ በላይ መሆኑን ተከትሎ በርካታ አገራት የጉዞ እገዳ መጣላቸውን ቀጥለዋል።

ይህ አዲስ የቫይረስ ዝርያ እስካሁን ከእንግሊዝ ውጭ በዴንማርክ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ አሜሪካ ፣ አውስትራሊያ እና ሌሎች አገራት መከሰቱን የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል።

አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከቀድሞው በ70 በመቶ የመሰራጨት እድል እንዳለውም ድርጅቱ ገልጿል።