መተከል ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ዉስጥ በንጹሐሀን ዜጎች ላይ የሚፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ትኩረት አላገኘም


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ዉስጥ በንጹሐሀን ዜጎች ላይ የሚፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ትኩረት አላገኘም ሲሉ የአካባቢው ነዋሪ አማረሩ።

መንግስት ትኩረቱን በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ስራ ላይ በማድረጉ በክልሉ በሚኖሩ የሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ሊቆም አልቻለም ብለዋል፡፡ ታጣቂዎች መረጃ ቶሎ ስለሚደርሳቸው ካሉበት ቦታ በፍጥነት ወደሌላ ቦታ ይዛወራሉ ያሉት አስተያየት ሰጪው የክልሉ መንግስት በመዋቅሩ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አመራሮችን መፈተሸ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሰሞኑን በመተከል ዞን በሚታየዉ ጥቃት የትራንስፖርት አገልግሎት መቆሙንም ተናግረዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህዝብ ደህንነትና ሰላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ዱጋሳ ለዶይቼ ቬለ በስልክ እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራን ነዉ ብለዋል። እስካሁን 20 ታጣቂዎች ተገድለዋል፣ 11 መማረካቸዉን ተናግረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የዓለም አቀፍና የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተክለማሪያም በበኩላቸው በመተከል በኩል ያለው አሰቃቂ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት በጊዜ በቁጥጥር ስር ካልዋለ በሌሎች አካባቢዎች ከሚታዩ ግጭቶች ጋር ተዳምሮና ሰፍቶ ወደ እርስ በእርስ ግጭት እንዳይወስደን ሲሉ ስጋታቸዉን ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ የባህርዳሩ ወኪላችን ዓለምነዉ መኮንን የአማራ ክልል መንግስትን አስተያየት ለማግኘት ያደረገዉ ሙከራ አልተሳካም፡፡ DW