የኢትዮጵያን ታሪክ ሲነሳ ትግራይ የሌበት ታሪክ እና ትግራይ የሌለበት ኢትዮጵያዊነት የለም – አቶ አንዱዓለም አራጌ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“የኢትዮጵያ ዕዳ የሆኑት የኢሕአዴግ ክፍልፋዮች ናቸው” – አቶ አንዱዓለም አራጌ
ሲራራ– በትግራይ ክልል መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያለው ውጥረት እና መካረር ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ይህ በሁለቱ አካላት መሀከል የሚታየው መካረር ወደ ግጭት እንዳያመራ ምን ቢደረግ ይሻላል ይላሉ?
አቶ አንዱዓለም፡- ኢሕአዴግ ለኢትዮጵያ በዘመኗ የገጠማት ትልቅ መርገምት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ገና አልተላቀቃትም፡፡ የኢሕአዴግ መበስበስ እና የውስጥ ክፍፍል ነው አሁን የምናየው ምስቅልቅል ውስጥ እየከተተን ያለው፡፡ በውስጣቸው ከሶሻሊዝም ጋር አብሮ ተጣብቆ የመጣ አንበረክካለሁ አልንበረከክም የሚል ዕብሪት የሞላበት እንቅስቃሴ አለ፡፡ አሁን ያለው መናናቅ በሚተዋወቁ ሰዎች መሀከል መሆኑ ፀቡን የድመት ፀብ አድርጎታል፡፡
መፍትሔው መወያየት እና መወያየት ብቻ ነው፡፡ ከውይይትና ድርድር ውጪ ምንም ዓይነት መፍትሔ የለም፡፡ ሁለት በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት በየፊናቸው ሕዝቡን በስሜት እየኮረኮሩ ቅስቅሰው እያደራጁ ወደ ጦርነት ሊማግዱት እና በኢትዮጵያ ልጆች ላይ ሊጫዎቱ አይገባም፡፡ ከውይይት የተሻለ ምንም ዓይነት መፍትሔ የለም፡፡ እውነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስቡ ከሆነ ለሰላም የማይሻገሩት ድልድይ የለም፡፡ አሁን ያለው ችግር በአመዛኙ ከግል ዝና ጋር እና መናናቅ ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ አንድ ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተጭኖ ስለ ግል ክብሩ የሚጨነቀው እሱ ማን ስለሆነ ነው? በግለሰቦች ብስጭት ሕዝብ እንደ ሳር እና ቅጠል የሚረግፍበት ምክንያቱ ምንድን ነው? አሁን ላይ ለሕዝብ ለአገር ሲባል ዝቅ የሚባልበት ጊዜ ነው፡፡ ዛሬ ዝቅ ማለቱ ለነገ ወደተሻለ ከፍታ መስፈንጠሪያ ሆኖ ነው የሚያገለግለው፡፡ ብዙ ፖለቲከኞች ራሳቸው ከአገር እና ከሕዝብ በታች ራሳቸውን አድረገው አገርን ክፍ ማድረግ ነው ያቃታቸው፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው እነዚህ ዛሬ ለጠብ የሚፈላለጉ ሰዎች ለበርካታ ዓመታት በአንድ ላይ ሆነው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲበድሉ ነው የኖሩት፡፡ አሁን ተለያይተው ደግሞ ዳግም ሕዝብ ሊበድሉ እያሴሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እምቢ ማለቱ አይቀርም፡፡ አንዱ በሌላው ወንድሙ ላይ ጦርነት ሰብቆ የራሱን ስጋ ሊያጠቃ አይችልም፤ አይገባምም፡፡ የጦርነትን አውዳሚነትና አስቀያሚነት በደንብ እናውቀዋለን፡፡ የራበን ሰላም፣ ልማት እና ዴሞክራሲ ነው፡፡ በቀላሉ ማሳካት ስንችል በገዥዎች እምቢተኝነት ምክንያት ያጣነው ፍትሕና እኩልነት የሰፈነበት ሥርዓት ነው፡፡
ሲራራ– በፌዴራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መንግሥት መሀከል የሚታየውን መካረር መነሻ በማድረግ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ትግራይ ልትገነጠል ትችላለች የሚል ስጋት ይስተዋላል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ አንዱዓለም፡- እኔ ፈጽሞ አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲነሳ ትግራይ የሌበት ታሪክ እና ትግራይ የሌለበት ኢትዮጵያዊነት የለም፡፡ የኢትዮጵያዊነት እምብርቱ ማን ሆነና? እንገንጠል ቢሉ እንኳን ትግራይ ከሚሉ ኢትዮጵያ ብለው ቢገነጠሉ ነው የሚሻላቸው፡፡ ለአገር የተደረገው ተጋድሎ፣ አድዋን የመሰለ አንፀባራቂ ድል፣ አክሱምን የመሰለ ታሪክ የተሠራው ትግራይ በሚል ስም አይደለም፤ ኢትዮጵያ በሚል ስም ነው፡፡ የትግራይ ምድር ቢቆፈር ኢትዮጵያዊነትን ነው የሚያበቅለው፡፡ የሚወጣው ታሪክ የኢትዮጵያዊነት ታሪክ ነው፡፡ ትግራይን ከኢትዮጵያ እቅፍ ውስጥ ፈልቅቆ የሚያወጣ የሕዝብ ለሕዝብ ችግር የለም፡፡ ግጭቱ ያለው በኢሕአዴግ ክፍልፋዮች መሀከል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዕዳ የሆኑት የኢሕአዴግ ክፍልፋዮች ናቸው፡፡ እነሱ ደግሞ ያልፋሉ፤ ሕዝብ ነው የማያልፈው፡፡ ለሚያልፍ ችግር ሕዝብ አይለያይም፡፡ የመገንጠል ታሪክ የከፍታ ዘመን ሳይሆን የዝቅታ እና የውድቀት ታሪክ ማሳያ ነው፡፡
በጥቅሉ ማለት የሚቻለው የሥልጣን ቁንጮውን እኔ ልያዘው እኔ ልያዘው በሚሉ ፖለቲከኞችና ጽንፈኛ ልኂቃን መሀከል እንጅ በኢትዮጵያ ሕዝብ መሀከል ግጭት የለም፤ ኖሮም አያውቅም፡፡ የትግራይ ሰፊ ሕዝብም ለዘመናት ሲጨቆን የኖረ ሕዝብ ነው፡፡በፍፁም በክፉውም በደጉም አብሮት ከኖረው ሌላው ወንድሙና እህቱ ተነጥሎ አይሄድም፡፡