ኦነግ የተገፉ እና በግል ምክንያት የለቀቁ የቀድሞ የድርጅቱን አባላት በማሰባሰብ ለስሙ የሚመጥኑ አመራሮችን በመምረጥ ራሱን እንደሚያጠናክር አስታወቀ

  • ኦነግ ለስሙ የሚመጥኑ አመራሮችን በመምረጥ ራሱን እንደሚያጠናክር አስታወቀ
(ኢፕድ) የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር /ኦነግ/ ከምስረታው ጀምሮ ደርጅቱን ደግፈው ሲታገሉ የነበሩ፤ ነገር ግን የተገፉ እና በግል የወጡ የቀድሞ የድርጅቱን አባላት በማሰባሰብ እና ለስሙ የሚመጥኑ አመራሮችን በመምረጥ ራሱን እንደሚያጠናክር አስታወቀ። ድርጅቱን በተለያየ ምክንያት ለለቀቁ ነባር አመራሮች ጥሪ አቀረበ ።
የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ ትናንት በግንባሩ ፅህፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከምስረታው ጀምሮ ደርጅቱን ደግፈው ሲታገሉ የነበሩ የተገፉ እና በግል ምክንያት የለቀቁ የቀድሞ የድርጅቱን አባላት በማሰባሰብ ለስሙ የሚመጥኑ አመራሮችን በመምረጥ ራሱን የማጠናከር ስራ እየሰራ ነው ።
ግንባሩ በዓላማ ተመሳሳይ ከሆኑ ሌሎች የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ያስታወቁት ቃል አቀባዩ ፣ድርጅቱ በተግባር የግለሰብ ሳይሆን የህዝብ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል። ድርጅቱ የተመሰረተው መላውን የኦሮሞ ህዝብ ታሳቢ አድርጎ መሆኑን ጠቁመው፣ ከእንግዲህ ይህንኑ የተመሰረተበትን አላማ ታሳቢ አድርጎ ይንቀሳቀሳል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በብሔር በመደራጀት ግንባር ቀደም የሆነው ኦነግ በኦሮሞ ማህበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍ እና ተቀባይነት እንዳለው አመልክተው፣ በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ምክንያት ህዝቡንም ድርጅቱንም በሚጎዳ መልኩ ሲከፋፈል መቆየቱን ተናግረዋል። ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ብቻ ቢያንስ ሶስት ጊዜ የመከፋፈል አደጋ እንዳጋጠመው ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ቶሌራ ገለጻ ድርጅቱ በየአራት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ቢኖርበትም ላለፉት 21 ዓመታት በተገቢው መልኩ ጉባኤው ለማካሄድ ሳይችል ቀርቷል። በእነዚህ ዓመታት እ.አ.አ በ2004 እና በኋላም ከ13 ዓመት በኋላ እ.አ.አ በ2017 ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። በእነዚህ ዓመታት ድርጅቱን በሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ዳውድ ኢብሳ ጉባኤዎች እንዳይካሄዱ በመፈለጋቸው የተለያዩ እንቅፋቶች ሲፈጥሩ ቆይተዋል።
በኢትዮጵያ ለውጥ መመዝገቡን ተከትሎ ድርጅቱ ከመንግስት ጋር በመነጋገር የትጥቅ ትግሉን ቀይሮ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገርቤት መግባቱን ቃል አቀባሩ አስታውሰው ወደ አገር ቤት ከገባ በኋላም የድርጅቱ ነባር አባላት እና አመራሮች አንድ ወጥ አቋም ማራመድ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል። የተወሰኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ድርጅቱ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስኖ ወደ አገር ቤት የተመለሰበትን የትግል ስትራቴጂ በመቀየር የትጥቅ ትግል የማድረግ ዝንባሌ እየታየባቸው መምጣቱን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ ቶሌራ ገለፃ፤ አገር ቤት ከተገባ በኋላ በአመራር መሃል ክፍተት ተፈጥሯል ይህን ተከትሎ የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ‹‹ስብሰባ ይካሄድ›› የሚል ጥያቄ በቃል ሳይሆን በፅሁፍም ጭምር ለድርጅቱ የወቅቱ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ቀርቦ ነበር። በሳቸውም በኩል ጥያቄው ተቃውሞ አልገጠመውም።
የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ ሊካሄድ አንድ ቀን ሲቀረው በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ‹‹ስብሰባውን አላውቀውም ኦነግን ለህዝቡ ሰጥቻለሁ። ህዝቡ ይጠብቀው›› በማለት ሁሉንም ግር ያሰኘ መግለጫ መስጠታቸውን ቃል አቀባዩ አስታውሰዋል ።
ይህንን የመሳሰሉ ውዥንብሮች መኖራቸውም ድርጅቱ በጥርጣሬ እንዲታይ ያደረገው መሆኑን ያስረዱት አቶ ቶሌራ ከቃል አልፎ በፅህፈት ቤቱም ስብሰባው እንዳይካሄድ በወጣቶች ረብሻ ለማስነሳት ሙከራ ተደርጓ እንደነበር ጠቁመዋል።
ማዕከላዊ ኮሚቴው ችግሩን በብልሃት እና በታጋሽነት በማለፍ ለሁለት ቀን ስብሰባውን በማካሄድ ከሃጫሉ ሁንዴሳ ጋር ተያይዞ የኦነግ ስም መነሳቱን በሚመለከት እንዲሁም ኦነግ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ፈጥሯል በሚል የሚናፈሰውን ወሬ እና ለኦነግ የሚመጥን አመራር በመምረጥ ዙሪያ በግልፅ መወያየትን ዓላማ አድርጓ ስብሰባው ተካሂዷል ብለዋል።
ኦነግ ለጋራ አመራር እንጂ ለግለሰብ አመራር ቦታ የለውም። የኦነግ መተዳደሪያ ደንቡም ይህንኑ ያረጋግጣል። ይሁን እንጂ አቶ ዳዉድ ኢብሳ ከ8 የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች 2ቱ የታሰሩ ሲሆን፣ የድርጅቱን ህገ ደንብም ሆነ አሰራር በመጣስ 5ቱን አባላት ‹‹ከስራ አባርሪያለሁ›› በማለት የግል ፍላጎታቸውን ማራመድ ቀጥለዋል ያሉት አቶ ቶሌራ፣ የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ግን ህግ እና ደንቡን ተከትሎ ሊቀመንበሩን አግዶ፤ ለጠቅላላ ጉባኤው የማቅረብ መብቱን በመጠቀም በዚህ መልኩ በጋራ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አስታውቀዋል። ጠቅላላ ጉባኤውም በመጪው ታህሳስ 2013 ዓ.ም ይካሄዳል የሚል ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል።
መግለጫውን ተከትሎ አቶ ቶሌራ የአቶ ዳውድን መታገድ ተከትሎ ከእርሳቸው ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ በእርሳቸው የሚታዘዙ ‹‹የኦነግ ታጣቂዎችን›› አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ‹‹የኦነግ ታጣቂዎች የተወሰኑ ቢኖሩም፣ ብዙዎቹ በመንግስት ሰልጥነው ወደ መደበኛ ህይወታቸው ተመልሰዋል። ሌሎቹም ወደ ግል ሥራ ሄደዋል ብለዋል።
ከእነርሱ ውጪ ‹‹አሁንም አማራጬ የትጥቅ ትግል ነው›› የሚል አካል ካለ ኦነግ የትግል አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ሰላማዊ ትግል በመዞሩ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስታውቀዋል። ኦነግ ከአሁን በኋላ ተዋጊ ሰራዊት የለኝም ብሎ ያወጀው ገና ኢትዮጵያሳይገባ ለውጡን ተከትሎ በኤርትራ እያለ መሆኑን አብራርተዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በተለያየ መልኩ በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ እና ሌሎችም በኦሮሚያ ለኦሮሞ ህዝብ የቆሙ ፓርቲዎች አሉ።
ኦነግ ከነዚህ ሃይሎች ጋር የዓላማ ልዩነት የሌለው በመሆኑ ከእነርሱ ጋር አብሮ መስራት እንደሚፈልግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው መግባባት ላይ ደርሶ በአብላጫ ድምፅ ቢወሰንም የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረግ እያለባቸው እንዳይፈፀም አድርገዋል። ይህ ከዴሞክራሲያዊ አሰራር የወጣ የአንድ ግለሰብ አምባገነንነት መስፈኑን ያመላከተ ሲሆን፣ ከአሁን በኋላ ኦነግ በዓላማ ከሚመሳሰሉት ጋር ይሰራል።
የተወናበዱ የድርጅቱ ደጋፊዎች ግር እንዳይሰኙ የድርጅቱ ትግል መቀጠሉን፤ ከአንድ ግለሰብ ከስራ መታገድ ውጪ ሥራዎች በትክክል እየተካሄዱ መሆናቸውን አቶ ቀጄላ አመልክተው፤ ከድርጅቱ የለቀቁ ነባር አባላት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል። ድርጅቱ ከውስጥና ከውጭ የገጠሙትን ችግሮች በማቃለል፤ ያለበትን ድክመት በማረም በሰላማዊ መንገድ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።