በሁከትና ግርግር እጃቸው ያለበት የገዥውም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።
በሁከትና ግርግር እጃቸው ያለበት የገዥውም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል…. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ
(ኢዜአ) በሁከትና ግርግር እጃቸው ያለበት የገዥውም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
መንግስት የንጹሃን ደም በማፍሰስ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግን ሙከራ እንደማይታገስም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው እለት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በተለይ በሀገራዊ ሰላም ዙሪያ አሉን የሚሏቸውን ሃሳቦች አንስተዋል።
የፓርቲ ተወካዮቹ የሰላም መስፈን የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ አጀንዳ መሆን አንዳለበምት ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያን ሰላም በማደፍረስ ከሚሰሩ የውጭ ሃይሎች በተጓዳኝ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ አካላት ግጭትና ሁከት እንዲፈጠር እየሰሩ እንደሆነ አንስተው፤ ከዚህ አንጻር መንግስት ራሱን እንዲፈትሽ ነው ጥያቄ ያቀረቡት።
በተጫማሪ “መንግስት በቅርቡ የተከሰተውን ሁከትና ግርግር ምክንያት በማድረግ የፓርቲ አመራሮቻችንን እያሰረብን ነው” ሲሉም ቅሬታ አቅርበዋል።
ሂደቱ የሚፈለገውን ሰላም በማስፈን ረገድ እክል እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
ትግራይ ክልልን የሚመራው መንግስት “ምርጫ አካሄዳለሁ” በማለት በህገ መንግስት ለፌዴራል መንግስት የተሰጠውን ስልጣን እየጣሰ ነው፤ መንግስት ለምን እርምጃ አይወስድም የሚል ሃሳብም በመድረኩ ተነስቷል።
መንግስት የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት እንዲሳካ ላበረከተው አስተዋጽኦም እውቅና ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የተቋም ግንባታ በባህሪው ውስብስብና የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረው፤ መንግስት በራሱ መዋቅር ወስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የፖለቲካ ፓርቲዎችም የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰላምና የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረግ ማናቸውም አይነት ሙከራ መንግስት የማይታገሰው ቀይ መስመር መሆኑንም አብራርተዋል።
የደሃ ኢትዮጵያውያንን ልጆች እያጋጩ በአቋራጭ ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚደረግ ሙከራ እንዳለ ጠቅሰው፤ በድርጊቱ እጃቸው ያለበት ግለሰቦችን ለምን ተጠየቁ የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
በሁከትና ግርግር እጃቸው ያለበት የገዥውም ሆነ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላቶችን በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት።
በቅርቡ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከት ጋር በተያያዘ በርካታ የብልጽግና አመራሮች መታሰራቸውን ለአብነት በማንሳት።
ሽማግሌዎችን አደራጅቶ በመላክ በህግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎችን ለማስፈታት የሚደረግ ጥረት መኖሩንም ተናግረዋል።
ህግን እንደፈለጉ የሚጥሱ ሰዎችን በሽምግልና ስም የማስፈታት ስልጣን የለኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሂደቱ በራሱ የዴሞክራሲና የህግ የበላይነት ልምምድን እንደሚያቀጭጭው አብራርተዋል።
ከትግራይ ክልል ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄም “በትግራይ ክልል ተቀምጠው የክልሉን ህዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ለማጋጨት የሚሰሩ አካላት ቢኖሩም መንግስት ከክልሉ ህዝብ ጋር ግጭት የመፍጠር ፍላጎት የለውም” ብለዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ክልሉን እንዲመራ የተቋቋመው መንግስት እስከቀጣዩ ምርጫ ድረስ በስልጣን አንዲቆይ መወሰኑንም አስታውሰዋል።
ከዚህ አንጻር ክልሉ አደርገዋለሁ ያለው ምርጫ ትርጉም እንደሌለው ጠቅሰው፤ “በምርጫው ከህወሃት ውጭ ሌላ ፓርቲ ወደ ስልጣን ቢመጣ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን የሚጥስ በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ወደ አልተፈለገ ግጭትም ያመራል” ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በቀጣይም በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያያት ቀጠሮ ይዘዋል።