ጌዴኦ ተፈናቀለ፣ አሁን ደግሞ እየተቆመረበት ነው፣ ማን ለጌዴኦ ይጩህ ? #ግርማካሳ

(ከዚህ በታች ያሉት አሓዞች የተገኙት ከህዝብ ቆጠራ ሪፖርትና ከተባበሩት መንግስታት ነው፡)

ከ13 አመት በፊት በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ 729955 ጌዴኦዎች እንዳሉ ተገልጿል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 731871 ወይም 74.8 % በደቡብ ክልል፣
729955 ወይም 73% በጌዴኦ ዞን ውስጥ ይኖራሉ፡፡ 19% የሚሆኑት ደግሞ፣ በኦሮሞ ክልል የጊዴኦ ዞንን በሚያዋስኑ፣ በገለና፣ በአባያ፣ በቡሌ ሆራ፣ በቀርቻ፣ በሃምቤላ ዋሜናና በኡራጋ ወረዳዎች ተካተዋል፡፡

በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ጌዴኦዎች በተለይም ኦህዴድ አራት ኪሎን ከተቆናጠጠ በኋላ፣ በኦሮሞ ጽንፈኞች ትልቅ ችግርና ሰቆቃ እንደደረሰባቸው በስፋት አለም የሚያወቀው ጉዳይ ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞችን ጉዳይ ባወጣው መረጃ፣ በሁለት የስደተኞች ካምፕ ከ600 በላይ አብዛኞቹ ጌዴኦዎች መፈናቀላቸውን ይገልጻል፡፡ ከቀርጫ ወረዳ 202819፣ ከከቡሌ ሆራ፣ ገለናና አባያ ወረዳዎች 252427 ፣ ከሃምቤላ ዋሜናና ኡራጋ ወርዳዎች 1505275፣ በአጠቃላይ 620747 ዜጎች፡፡

ከጌዴኦ ዞን በስተ ምእራብና ደቡብ ያሉት የቡሌ ሆራ፣ ገላናና አባያ ወረዳዎችን ብንወስድ፣ ባለፈው የሕዝብ ቆጠራ መሰረት 438394 ዜጎችን ይኖሩባቸው ነበር፡፡ ቁጥራቸው በ36% አድጓል ብለን ብንወስድ አሁን የሕዝብ ብዛታቸው 596216 ይደርሳል ብለን ልንገምት እንችላለን፡፡ እንግዲህ ከነዚህ ወረዳዎች 252427 ወይንም 42% ተፈናቅለው ነበር፡፡

ከጌዴኦ ዞን በስተ ምስራቅ ያለው የቀርቻ ወረዳን ብንወስድ በሕዝብ ቆጠራው 227198 ነዋሪ የነበረው ሲሆን በ36% አድርጓል ብንል አሁን የሕዝቡ ቁጥር 308989 ይደርሳል፡፡ ከዚህ ወረዳ 202819 ወይንም 66% ተፈናቅለው ነበር፡፡

ከቀርቻ ወረዳ ወደ ሰሜን ስንሄድ፣ አሁን ከጊዴኦ ዞን በስተ ምስራቅ ያሉትን የሃምቤላ ዋሜናና ኡራጋ ወርዳዎችን ብንወስድ በሕዝብ ቆጠራው 281036 ነዋሪዎች የነበራቸው ሲሆን በ36% ቁጥሩ ጨምሯል ብንል አሁን የሕዝብ ብዛታቸው 382209 ይደርሳል፡፡ ከነዚህ መካክል 150524 ወይንም 39% የሚሆኑት ተፈናቅለዋል፡፡

እንግዲህ የተፈናቀሉት አብዛኞቹ ጊዴኦዎች ከነበሩ ከዚህ የምንረዳው ከላይ በተጠቀሱት ወረዳዎች ብቻ ከ605770 በላይ ጌዲኦዎች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ በነዚህ ወረዳዎች በድምሩ ከሚኖረው 1287414 ሕዝብ 48% ወይንም ግማሾቹ ጌዴኦዎች ናቸው ማለት ነው፡፡

አሁን ባለው አከላለልም የምናየው አንዱ ትልቅ ኢፍትሃዊነት ይሄ ሁሉ የጊዴኦ ማህበረሰብ ለኦሮሞ ፣ በኦሮሞ፣ ከኦሮሞ በሆነ ፣ አፓርታይዳዊ፣ ኦሮሞ ያልሆኑትን ሁለተኛ ዜጋ ያደረገ፣ ከኦሮሞኛ ውጭ በሌሎች ቋንቋዎች አገልግሎት የማይሰጥበት፣ ኦሮሞ ብቻ ተመራጭ የሚሆነበት ክልል ውስጥ ያለፍቃቸው እንዲካተቱ መደረጉ ነው፡፡

ያም አልበቃ ብሎ ጌዴኦዎች ኦሮሞ ስላልሆኑ ብቻ፣ ለዘመናት የኖሩበት መሬት ኦሮሞ ክልል ውስጥ በመካተቱ፣ አገራችሁ አይደለም ተብለው የጥቃት፣ የመፈናቀልና የዘር ማጽዳት ወንጀል ሰለባ ሆነዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት በሁለት ጣቢያዎች ተዝገበው የነበሩትን 600 መቶ እንደሚደርሱ ገለጸ እንጂ በተለያዩ ሌሎች ቦታዎች የተጠለሉትን በመጨመር የጊዴኦ ተፈናቃዮች ወደ 800 ሺህ ይደርሱ ነበር፡፡ እንግዲህ ያ ሁሉ ፣ ያዉም በተወሰነ ወረዳዎችን ብቻ የሚኖር ሕዝብ ነው፣ አሁን ባለው የዘዉግ ሕገ መንግስትና አወቃቀር አገር አልባ እንዲሆን የተደረገው፡፡

በነገራችን ላይ ይሄ ሁሉ ጌዴኦ በሕዝብ ቆጠራው ላይ የት ነበር ? ይሄ ሁሉ ጊዴኦስ ለምን በኦሮሞ ክልል እንዲካተት ተደረገ ? የሚሉት ጥያቄዎች ብዙዎች የሚያነሱት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ለዚህም በጣም ቀላል መልሶች አሉ፡፡

አሁን ያለው ሕገ መንግስትና አወቃቀር በዋናነት የተጻፈው በኦነግ ና ሕወህት ነው፡፡ በኦሮሞና የትግራይ ብሄረተኛ ልሂቃኖችንና ፖለቲካኖች፡፡ በአንድ ወረዳ ወይንም በአንድ አካባቢው ኦሮሞዎች ማይኖሪቲ ቢሆኑም ፣ የሚኖሩበት መሬት አብዛኛው ማለት ይችላል ወደ ኦሮሞ ክልል ነው የተጠቃለሉት፡፡ የኦሮሞ መሬት ተብሎ፡፡  እነ ከሚሴን ወደ ኦሮሞ ክልል ለማጠቃለልም ተፈልጎ በመሐል ሌሎች በብዛት ስለሚኖሩ ነው አማራጭ አጥተው በአማራ ክልል ውስጥ እንዲቀጥሉ የተደረገው፡፡ እንደዚያም ሆኖ በዞን ደረጃ የኦሮሞ ዞን በሚል ኦሮሞዎች የዞኑ ባለቤቶች ተደርገዋል፡፡ በአማራ ክልል ሆኖ፣ በከሚሴ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ልክ እንደ አቦምሳና አሳሳ ፣ እንደ አምቦና ሻምቦ፣ እንደ ያቤሎና ደምቢዶሎ ነው ሁለተኛ ዜጎች ነው የሚቆጠሩት፡፡

ያ ብቻ አይደለም ፣ የኦሮሞ ክልል አፓርታይዳዊ ዘረኛ ክልል ነው፡፡ አንድ ሰው ኦሮሞ ነኝ ካላለ ወይንም ኦሮምኛ የማይናገር ካልሆነ በኦሮሞ ክልል የማደግ፣ የመሻሻል፣ ሃብት የማፍራት እድሉ የመነመነ ነው፡፡ በክልሉ ኦሮሞ ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆን በመደረጉ፣  ከኦሮሞና ከጉራጌ፣ ከኦሮሞና ከአማራ፣ ከኦሮሞና ከሶማሌ፣ ከኦሮሞና ከጊዴኦ ….ወላጆች የተወለደ ራሱን ኦሮሞ ብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ሳይወድ በግዱ፡፡ ለምን ? መታወቂያው ላይ ኦሮሞ የሚል ከሌለ በኦሮሞ ክልል እንደ ውጭ አገር ዜጋ ስለሚቆጠር፡፡ እነዚህ በግማሽ ጎን ኦሮሞ የሆኑት ብቻ ሳይሆን፣  ኦሮሞም ያልሆኑ ለመኖር ሲሉ ኦሮሞ ነን ያሉም ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በርካታ ጌዴኦዎችና ከጌዴኦና ኦሮሞ የተወለዱ ሕብረ ብሄር ዜጎች ለመኖር ሲሉ ኦሮሞ ነን ያሉበት ፣ በሕዝብ ቆጠራው ኦሮሞ ተብለው የተቆጠሩት ሁኔታ እንዳለ ነው በግልጽ የምናየው፡፡

ሆኖም ግን ኦሮሞ መባል በራሱ በኦሮሞ ክልል ዋስትና አይሰጥም፡፡ “አባትህ ኦሮሞ አይደለም፣ እናትህ ኦሮሞ አይደለም” በሚል ትልቅ ልዩነቶች በኦሮሞ ክልል አሉ፡፡ “ንጹህ ኦሮሞ አይደላችሁም”፣”ዲቃላዎች” ናችሁ የሚል አባባል በስፋት አለ፡፡ በቅርቡ በባሌና አርሲ በርካታ የሸዋ ኦሮሞዎች ከሌሎች ጋር ተደምረው በግፍና በጭካኔ የታረዱት “ኦሮሞ አይደላችሁም፣ ዲቃላ ናችሁ” ተብለው ነው፡፡ በመሆኑም ዘር ተኮር ጥቃት ሲፈጸም ግማሽ ኦሮሞ የሆነውም ሰለባ መሆኑ አልቀረም፡፡ በጌዴኦም የሆነው ይሄ ነው፡፡ በእናት ወይም በአባት ጌዴኦ የሆኑ፣ ጌዴኦ ሆነው ኦሮሞ ነን ያሉትም በጅምላ ነው ጌዲኦ ተብለው መፈናቀል የተፈጸመባቸው፡፡ ለዚህም ነው በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ጊዴኦዎች በሕዝብ ቆጠራው መሰረት ትንሽ ቢሆኑም፣ የተፈናቀሉ ጊዜ ቁጥራቸው የበዛው፡፡

በዶር አብይ የሚመራው መስተዳደር ከብዙ ጩከትና ተቃውሞ በኋላ የተፈናቀሉ ጊዴኦዎች ወደ ቅያቸው እንዲመለሱ ማድረጉን ይናገራል፡፡ በዚያን ወቅት በተደረጉ ውይይቶች የኦሮሞ አባ ገዳዎች ጌዲኦዎች እንዲመለሱ አንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠውላቸው እንደነበረ በስፋት ሲነገር ነበር፡፡ እርሱም “ኦሮሞ ነን “ በሉ የሚል፡፡

ይሄም የሚያሳየው በኦሮሞ ፖለቲከኞችና አባ ገዳዎች ነን በሚሉት ዘንድ የመጠቅለል፣ ሌሎችን ኦሮሞ አድርጎ በኦሮሞነት ስር የማድረግና የመጨፍለቅ አላማና አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ነው፡፡ በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ በኦሮሞ ክልል ያሉ ጌዴኦዎች መጨፍለቅ ብቻ ሳይሆን በደቡብ ክልል የጌዴኦ ዞን ያሉትን የመጨፍለቅ ፍላጎት እንዳለም አንዳንድ ምልክቶች እያየን ነው፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በአሁኑ ወቅት የፊዴራል መንግስትንና ተቋማትን የሚቆጣጠሩ እንደመሆናቸው የኦሮሞ የመስፋፋት አጀንዳቸውን አጠናክረው እየገፉበት ነው፡፡ የጌዲኦ ጉዳይም አንዱ ማሳየ ነው፡፡ የኦሮሞ ብሄረተኞች ፖለቲካ የእኩልነትና የፍትህ ሳይሆን የበላይነትና ሌላው የመጨፍለቅ ፖለቲካ ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡

ይህ አካሄድ በዋናነት የኦሮሞ ማህበረሰብን በማያባራ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚከተው ብቻ ሳይሆን በቶሎ ካልተቀጨ ትልቅ ጥፋት የሚያመጣ ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፣ “የኔ ጎሳ የበላይ ነው፣ ከኔ ቋንቋ ውጭ ሌላ ቋንቋ አትናገሩ፣ ይሄ መሬት የኔ ነው ፣ አንተ መጤ ነህ .።” የሚሉ አነጋገሮች አደገኞች ናቸው፡፡

የሚያሳዝነው በንግግር ኢትዮጵያዊነት እንደሚያስቀድሙ የሚናገሩት የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በዚህ ወቅት ጌዴኦዎች ለኦሮሞ ተስፋፊዎች የእሳት እራት እንዲሆኑ በማድረግ የዚህ ጥፋት ተባባሪ ብቻ ሳይሆን ዋና አንቀሳቃሽ መሆናቸው ነው። የደቡብ ክልል እንደፈለጉ በመሸንሸን ፣ የጉዴኦ ዞን ከደቡብ ክልል ተነጥሎ ለጊዜው ልዩ ዞን ሆኖ በሂደት ግን ክሌሎቾ ክልሎች ጋር እንዲዋሃድ ወስነዉበታል።  ለጊዜው ልዩ ዞን ቢሉም የጊዴኦ ዞንን ወደ ኦሮሞ ክልል ለመጠቅለል አላማ እንዳልቸው መገመት አያስቸግርም፡፡ (በነገራችን ላይ የጌዴኦ ዞን ብቻ አይደለም፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሃረር፣ ሶማሌ ክልል ያሉ እንደ ሜኤሶ፣ ጉርሱም ባቢሌ፣ ሊባን ፣ ዳዋ ያሉ ወረዳዎች፣ የሞያሌን ከተማ፣ አሶሳና ዙሪያ ያሉ  በርካታ የቤኒሻንጉል ግዛቶችን ሁሉ በኦሮሞ ክልል  ውስጥ መጠቅለል ነው የሚያስቡት፡፡)