“ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ጥቅሟን የሚያስነካ ውል አልፈረመችም፤ ወደፊትም አትፈርምም፤ መፈረምም የለባትም፡፡” ዶክተር ይልማ ስለሺ

“ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ እስካሁን ድረሰ ጥቅሟን የሚያስነካ ውል አልፈረመችም፤ ወደፊትም አትፈርምም፤ መፈረምም የለባትም፡፡” ዶክተር ይልማ ስለሺ ( የውኃ መሐንዲስና በዓባይ ጉዳይ የተደራዳሪዎች ቡድን አባል )
(አብመድ) የግብጽ ፈጣሪና አሳዳጊ ዓባይ መውጫ ጎጆውን እንዲጠቅም በታሰበ ቁጥር ግብጽ አሻፈረኝ ትላለች፡፡ ኢትዮጵያ ዓባይን በግብጽ ደረጃ ስላልተጠቀመችበት ግብጽ “ዓባይ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ግብጻዊ ነው” እስከማለት ደርሳለች፡፡ ይህ ሐሳብ ደግሞ በተለይም ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ “ልጠቀም ነው” ካለችበት ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ውዝግብ እንዲጎላ አድርጎታል፡፡ በተለይም ደግሞ በቅርብ ጊዜያት በዓባይ ውኃ የወደፊት አጠቃቀም ዙሪያ ለውይይት የተቀመጡት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በከፊሉ ተስማምተው በከፊሉ ሳይስማሙ መለያየታቸው ይታወሳል፡፡ የሦስቱ ሀገራት አለመስማማት ደግሞ የቀጣናው ብሎ የዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኗል፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትም ስለነበረው የውይይት ሂደትና ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች፣ ወደ ፊትም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የመፍትሔ ርምጃዎች ከዘርፉ ምሁር ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ የውኃ መሐንዲስና በዓባይ ጉዳይ የተደራዳሪዎች ቡድን አባል ዶክተር ይልማ ስለሺ ድርድሩ ስምምነት ሳይደረስበት የቀረው መሠረታዊ ነገሩ የሦስቱ ሀገራት በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ያላቸው ሐሳብና ግብ የተለያየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “የግብጽና የሱዳን ተቀራራቢ ቢሆንም የኢትዮጵያ የተለየ መሆን ነው ድርድሩ ያለ ስምምነት እንዲቋጭ ያደረገው፤ ኢትዮጵያ ‘ውኃውን በፍትሐዊነት እንጠቀም’ የሚል ሐሳብ ነው ያቀረበችው፤ እነርሱ ግን በፊት ለፊት አይምጡ እንጂ ‘ውኃውን የመጠቀም ውል አለን፤ ውኃውን አትንኩ፤ የእኛ ነው’ የሚል መንፈስ ያለው ድርድር ነው ያላቸው” ብለዋል፡፡
እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ኢትዮጵያ የግድቡን የውኃ ሙሌት በተመለከተ አቋሟን አሳውቃለች፡፡ ሙሉ ለሙሉ መሙላት ቢቻልም ከፍትሐዊነት አንጻር ኢትዮጵያ ሌሎቹን ላለመጉዳት ቀስ በቀስ ለመሙላት ነው ያሰበችው፡፡ ሱዳናውያን “የግድቡን አሞላል ደኅንነት ጉዳይ እንይ” የሚል አቋም እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ የውኃውን መሙያ ጥናት፣ እንዴትና ማን እንደሚገነባው እንዳዩና ኢትዮጵያ በዚሁ የአገዳደብ አቋሟ እንድትቀጥል ተስማምተው ሄደው አንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት በመፈራረም የግድቡ ደኅንነት ጉዳይ ኢትዮጵያ በያዘችው መንገድ ትጨርሰው የሚል ስምምነት ላይ እንደደረሱም ተናግረዋል፡፡
የአጀማመሩ ሁኔታ ምክንያታዊ መሆኑንም ዶክተር ይልማ ገልጸዋል፡፡ በድርድሩ ሂደት ግን የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያሳጣ አንቀጽ ይዘው በመምጣታቸው ኢትዮጵያ ከድርድሩ ራሷን እንዳገለለች ተናግረዋል፡፡ ግብጽ እና ሱዳን ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ጥቅም ከግምት ውስጥ ያላስገባ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ ውል ብትይዝና በኋላ “ተሳስቻለሁ ይታረም” ብትል ለጦርነት ሕጋዊ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልና አሁን ግን ለጦርነት የሚያበቃ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ምክንያት በመካከላቸው እንደሌለም ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ እስካሁን ድረሰ ጥቅሟን የሚያስነካ ውል አልፈረመችም፤ ወደፊትም አትፈርምም፤ መፈረምም የለባትም” ብለዋል ምሁሩ፡፡ የኢትዮጵያ ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ውኃውን መገደብ ሳይሆን የድርሻዋን መጠቀም ብቻ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አማራጭም ሕዝቡ አንድነቱን አጠናክሮ ለመብቱ ከመታገል ውጭ ሌላ መንገድ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ “በዚህ ድርድር ውስጥ ጥንቃቄ ካላደረግን ብዙ ነገር እናጣለን፤ በውክቢያና በድርድር ጉድለት ቀይ ባሕርና ጅቡቲን አጥተናል፤ አሁንም የድርድር ጉድለት ካጋጠመን የዓባይን ውኃም እናጣለን፤ የመብቱን ጉዳይ በጥንቃቄ ካልተሄደበት ሌላ ችግር ነው ይዞ የሚመጣውም፤ ውኃውን ለማግኘት መንገድ ቢቀይሩም ኢትዮጵያ ደግሞ ‘አይሆንም ሉዓላዊነታችን አትጋፉ’ እያለች ነው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ግብጽ የምታነሳው የመከራከሪያ ሐሳብ ምክንያታዊ እንዳልሆነ የገለጹት ዶክተር ይልማ ስለሺ የግብጽ ጥያቄ ውስብስብ እና የብዙ ሀገራት ግፊት ያለበት እንደሆነም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ትኩረት ማድረግ ያለባት ውኃውን እንዳታጣና መብቷ እንዳይነካ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ከሦስቱ ሀገራት ውጭ ሦስተኛ አካል አለማስገባት ተመራጩ ጉዳይ እንደሆነም መክረዋል፡፡
እንደምሁሩ ማብራሪያ ኢትዮጵያም ሦስተኛ ወገን መግባት ተፅዕኖ እንደሚኖረው አስቀድማ በማወቋ አሜሪካንና የዓለም ባንክን በታዛቢነት ብቻ እንዲሳተፉ አድርጋለች፡፡ በኋላ ግን ራሳቸውን ወደ አደራዳሪነት ሲለውጡ ኢትዮጵያ ውይይቱን አቋርጣለች፡፡ የሦስተኛ ሀገራት መግባት እና የአንዱን ሀገር ዓላማ ብቻ ማሳካት ከሆነ ወደማይፈቱት ችግር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ አንዲህ ዓይነቱን ነገር ሦስተኛ ወገን ሊሠራውም ሊፈታውም እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡
ሱዳን በውይይቱ ላይ እየወሰደች ያለውን አቋም በተመለከተም “ሱዳን የዐረብ ሊግን ሐሳብ ‘አልቀበልም’ ማለቷ እውነት ነው ወይ? የሚለውን ማጤን መቻል አለብን፤ ሱዳን ስለደገፈችን ጉዳይን የምንተወው ስለነቀፈችን መልሰን የምንይዘው ነገር መኖር መቻል የለበትም፤ የእኛ ትኩረት መብታችን ላይ ነው፡፡ ሱዳን ግብጽን ወይም ኢትዮጵያን የመምረጥ የራሷ ፈንታ ነው፤ ኢትዮጵያ ግን ጠንካራ ሆና መገኘት መቻል አለባት” ብለዋል፡፡ “በግብጽ ሐሳብ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ለመስማማት መዘጋጀት ለወደፊቱ ትውልድ ላይ ስቃይ ማስቀመጥ ነው” ብለዋል ምሁሩ፡፡
ሱዳን ከዚህ በፊት ከግብጽ ጋር ስምምነት እንዳላት የተናገሩት ዶክተር ይልማ የተፈራረመችውን ብትጥስ ግብጽ ምን ልታደርጋት ትችላለች የሚለውን ማየት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የድርድርና የውይይት ጉዳይ በጥንቃቄ የተሞላና መብትን የማያሳጣ መሆን መቻል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

 መረጃ ቲቪን በተሻለ ጥራት እና ፍጥነት እንድናቀርብ እገዛችሁን እንሻለን።
መረጃ ቲቪን ለማገዝ ይህን ሊንክ በመጫን አባል ይህኑ - JOIN Mereja TV