የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመናገር ነፃነትን ለመገደብ እየተጠቀመበት ነው

Ethiopia: Free Speech at Risk Amid Covid-19

New Emergency Law Raises Concerns of Further Arrests, Prosecutions

The Ethiopian government has been using Covid-19 restrictions and a recently declared state of emergency as a pretext to restrict free speech.

የኢትዮጵያ መንግሥት የኮቪድ-19ን ለመከላከል ያስተላለፋቸው ገደቦችና ለአምስት ወራት የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመናገር ነፃነትን ለመገደብ እየተጠቀመበት ነው ሲል የሂይመን ራይትስ ዎች ወነጀለ።

ድርጅቱ በመግለጫው ባለፈው ወር ጠበቃ ኤልሳቤጥ ከበደና ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ አስተያየት በመስጠታቸው መታሰራቸውን ጠቀሷል።

ሪፖርቱ እንዳለው ኮሮናቫይረስ በአገሪቱ እንዳይስፋፋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጠኞችንና መንግሥትን የሚተቹትን ለማሰር እየዋለ ነው።

“ስለቫይረሱ የሚሰራጩ የተሳሳተ መረጃዎች ስጋት ቢሆኑም የመናገር ነፃነትን ለመገደብ ግን ሰበብ ሊሆኑ አይገባም” ያሉት የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላይቲቲያ ባደር፣ መንግሥት ያየሰው ሽመልስ ላይ የከፈተውን ክስ ውድቅ ማድረግ፣ ኤልሳቤጥ ከበደንም ከእስር መልቀቅ አለበት እንዲሁም ሰዎች በሰላማዊ መንገድ ሃሳባቸውን ስለገለፁ ብቻ ማሰር ማቆም ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮቪድ-19 ተያዘ ሰው ከተገኘ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል ይረዳል ያሉትን እርምጃ ያስተላለፉ ሲሆን በወቅቱ መገናኛ ብዙኀንም “ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ” እንዲያደርሱ አሳስበው ነበር።

ከዚህ በኋላም በትግራይ ቴሌቪዥን ጣብያ ፖለቲካዊ ፕሮግራሞች የሚያቀርበው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በግል የፌስ ቡክ ገፁ ላይ መንግጅት በኮቪድ-19 ምክንያት ለሚሞቱ ሰዎች 200 ሺህ ጉድጓዶች እንዲቆፈሩ አዝዟል ሲል ጽፏል።

በወቅቱ መንግሥት መረጃው ስህተት ነው ሲል አስተባብሏል።

በሚቀጥለው ቀን ጋዜጠኛው ለገጣፎ አካባቢ ከሚገኘው ቤቱ በፖሊስና በደህንነት ሰዎች ተይዞ መታሰሩ ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት በሚል ካሰረው በኋላ ለሶስት ሳምንት ክስ ሳይመሰርት እንዳቆየው የገለፀው መግለጫው፣ በኋላም በቂ ማስረጃ ባለመቅረቡ በዋስ እንዲለቀቅ ቢወሰንም የፌደራል ፖሊስ በመካከል ጣልቃ ገብቶ ይግባኝ በማለት ማሻሻያ የተደረገበትን የፀረ ሽብር ሕግ በመጣስ ከስሶታል ብሏል።

ለሁለተኛ ጊዜ የፌደራል ፍርድ ቤት ለጋዜጠኛ ያየሰው የዋስትና መብቱን አስጠብቆለት ሊለቀቅ መቻሉን መግለጫው አክሎ አስፍሯል።

የሂይውመን ራይትስ ዎች እንዳለው ከሆነ ያየሰው የተከሰሰው በአዲሱ የጥላቻና ሐሰተኛ መረጃ ሕግ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በጎ ፈቃደኛ ጠበቃ የሆነችው ኤልሳቤጥ በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት በቁጥጥር ስር መዋሏን ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል።

ድርጅቱ ከምትሰራበት ተቋም አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ኤልሳቤጥ እስካሁን ድረስ ክስ ያልተመሰረተባት ሲሆን ነገር ግን ” ግጭት የሚያነሳሳ” ሀሰተኛ መረጃ በፌስ ቡክ በማሰራጨት ተወንጅላለች ብሏል።(BBC Amharic)

https://www.hrw.org/news/2020/05/06/ethiopia-free-speech-risk-amid-covid-19