የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ማሻሻያ ሃሳቦችና አምስት አማራጭ ፌዴራል አወቃቀሮች – ግርማ ካሳ

ጥር 19 ቀን 2010 ዓ.ም

ከ105 የሕገ መንግስቱ አንቀጾች 77ቱ አንቀጾች መሻሻል አያስፈልጋቸውም። እንዳለ ይቀጥላሉ። 25 አንቀጾች በከፊል ወይም እንዳለ የተሻሻሉ ሲሆን፣ 3 አንቀጾች ( አንቀጽ  82፣ 83 እና 84) ተሰረዝዋል። ይህ አማራጭ የሕገ መንስግቱ ሰነድ በዋናነት ማሻሻያ ያደረገባቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡

  • የኢትዮጵያ በለቤትነትን ለ”ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች” ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሰጣል።
  • “ብሄር ብሄረሰብና ሕዝብ” በሚለው ምትክ ብሄረሰብ የሚለዉን አባባል ተጠቅሟል።
  • የብሄረሰቦችን ሆነ ማናቸዉንም የቡድን መብቶች ፣ የግለሰብ መብቶችን ባልደፈረ መልኩ ሙሉ ለሙሉ ያረጋግጣል። ከግለሰብ መብቶች ጋር የሚጋጩ ከሆነ ቅድሚያ ለግለሰብ መብት ይሰጣል።
  • “ክልል” የሚለው ቃል ክፍለ ሃገር በሚለው ይተካል።
  • የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመራረጥና የሥራ ሃላፊነት በተሻለ መልኩ ተለዉጧል። ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ሃላፊነት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ወደ ዳኞች ተወስዷል።
  • ፕሬዘዳንቱ ተጨማሪ ስልጣኖች እንዲያገኙ ተደርጓል።
  • መሬት መሸጥና መለወጥ እንደሚያስፈልግ የሚደነግጉ አንቀጾች ተቀምጠዋል።
  • ፌዴራሊዝም ስልጣን ከማእከላዊ መንግስት ወደ ህዝብ የሚያወርድና ለአገሪቷ ጠቃሚነቱን ታሳቢ በማረግ በኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ይቀጥላል። ሆኖም አሁን ያለውን “ፌዴራል” የሚባለው ግን ፌዴራል ያልሆነ አወቃቀር በመጠኑም ሆነ ስር ነቀል በሆነ መልኩ መሻሻያ የሚያደርጉ አምስት የፌዴራል አወቃቀር አማራጮች ቀርበዋል።

በአማራጭ 1 ፣ ሶስቱ ትላልቅ ክልሎች (አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ) ከቋንቋ በተጨማሪ ሌሎች መስፈርቶችን በማካተት፣ አነስ ወዳሉ በርካታ ክፍለ ሃገሮች ተሸንሽነዋል። የሃረሪ ክልል፣ የድሬደዋን አስተዳደር፣ ጅቡቲን የሚያዋስነው የሶማሌ ክልልን  ጨምሮ ሰፋ ያለች ክፍለ ሃገር ትሆናለች። የቤኔሻንጉል ክልል አይኖርም። ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ወደ በጌምድር ክፍለ ሃገር ይጠቃለላሉ።

በአማራጭ 2 ፣ በአጼ ሃይለስላሴ ጊዜና በኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማሪያም አስተዳደር መጀመሪያ አመታት ወቅት የነበሩ ከፍለ ሃገራትን ያካተተ ፌዴራል አወቃቀር ነው።

በአማራጭ 3፣ በክሎኔል መንግስቱ ሃይለማሪያም አስተዳደር ወቅት የነበሩትን የአስተዳደር መዋቅሮች እንዳለ ወስዶ፣ የኦጋዴን ክልል ከድሬደዋ/ሽንሌ ጋር ያገናኘዋል።

በአማራጭ 4 ፣ አገሪቷን ለአምስት ተመጣጣኝ ክፍለ ሃገራት የሸነሸነ የፌዴራል አወቃቀር ነው።

በአማራጭ 5፣ ከሞላ ጎደል ለአዲስ አበባባ ለድሬዳዋ ከተሞች ዘላቂ መፍትሄ በሰጠ መልኩ አሁን ያለው የፌዴራል አወቃቀር ያስቀጥላል። የወልቃይት ጥያቄ በትግራይ አማርኛም የስራ ቋንቋ በማድረግና ትግራይ አሁን ባለው አሰራር የተጋሩዎች ብቻ ሳትሆን የሁሉም ዜጎች የሆነች ክፍለ ሃገር ከተደረገች ሊፈታ ይችላል በሚል ታሳቢ ያደረገ አማራጭ ነው።

በአምስቱም አማራጮች አማርኛ የሁሉም ክፍለሃገራት የስራ ቋንቋ ሲሆን፣ በሁሉም ክፍለሃገራት ዜጎች የመኖር፣ የመስራት፣ የመነገድ፣ የመመረጥ፣ የመመረጥ፣ የመግባት፣ የመዉጣት . .መብታቸውን ያለምንም መሸራረፍ የሚያስከበር ነው።

ይህ አማራጭ ሰነድ የተዘጋጀው ኢትዮጵያዉያን በዚህ ጉዳይ እንዲነጋገሩበት ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ  ኢሕአዴግ ሆነ ተቃዋሚዎች ጠቃሚ መስሎ ካገኙትም ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

መግቢያ

በሕግ መንግስቱ መግቢያው ላይ የተቀመጠው በሙሉ በሚከተለው ተለዉጧል፡

“ኢትዮጵያ ሀገራችን የየራሳቸው አኩሪ ባሕል ያላችው፣ የየራሳቸው መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበራቸውና ያላቸው፣  ብሄረሰቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረው አብረው የኖሩባትና  የሚኖሩባት ሀገር በመሆንዋ፤ የብሄረሰቦቿ ልዩነት ዉበቷ ፣ትስስራቸውና አንድነታንቸው ደግሞ ጥንካሬው ሆኖ፣ በተለያዩ ዘመናት የተቃጣባትን የውጭ ወራር መክታ የቆየች አገር ናት።

ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች መጪው የጋራ እድላችውን በመመስረት ፣ በታሪካችን የነበሩ ድክመቶችን በማረም፣ የጋራ ጥቅማቸዉን በማሳደግ ፣ ሁሉም ዜጎች በቋንቋ፣ በባህል በሃይማኖት በጾታ ፣ በእድሜና  በመደብ ልዩነት ሳይደረግባቸው በሰላምና በፍቅፍ፣ በብልጽግና የሚኖሩባት አንዲት ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን የሚያረጋግጥ ሕግ መንግስት ነው።”

አንቀጽ 3

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ

ንዑስ አንቀጽ 2

«ከሰንደቅ ዓላማዉ ላይ የሚቀመጠው ብሄራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ኃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል።» የሚለው ይሰረዛል። ሰንደቅ ዓላማዉ አርማ አይኖረዉም።

አንቀጽ  4

የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር

«የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግስቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያን ሕዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንጸባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል።» የሚለው «የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግስቱን ዓላማዎችና ዜጎች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንጸባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል።» በሚለው ይተካል።

አንቀጽ 5

ስለ ቋንቋ

ንዑስ አንቀጽ 2

«አማርኛ የፌዴራሉ መንግስት የሥራ ቋንቋ ይሆናል» የሚለው  «አማርኛ  የፌዴራል መንግስትና የክልሎች ሁሉ የስራ ቋንቋ ይሆናል” በሚለው ይተካል።

ንዑስ አንቀጽ 3

«የፌዴሬሽኑ አባላት የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ በሕግ ይወስናሉ» የሚለው «የፌዴሬሽኑ አባላት ከአማርኛ በተጨማሪ የየራሳቸው ሌላ የሥራ ቋንቋ በሕግ ሊደነግጉ ይችላሉ። በሚለው ይቀየራል።

አንቀጽ 8

የሕዝቡ ሉዓላዊነት

ንዑስ አንቀጽ 8

«የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ስልጣን ባለቤቶች ናቸው።» የሚለው «የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ነው» በሚለው ይተካል።

አንቀጽ 33

የዜግነት መብቶች

ንዑስ አንቀጽ 3

«ማንኛዉም ዜጋ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን የመለወጥ መብት አለው» የሚለው «ማንም ዜጋ ከኢትዮጵያዊነት ዜግነት በተጨማሪ የሌሎች አገሮች ድርብ ዜግነት መያዝ ይችላል» በሚል ይሻሻላል።

አንቀጽ 34

የጋብቻ፣ የግልና የቤተሰብ መብቶች

«ጋብቻ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል ብቻ የሚደረግ  ይሆናል» የሚል አምስተኛ ንዑስ አንቀጽ ያጨመራል።

አንቀጽ 39

‹የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት» የሚለው “የብሄረሰብ መብት” በሚለው ይተካል።

«ማንኛዉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብ፣ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው»   የሚለው ንዑስ አንቀጽ 1 ይሰረዛል።

«የብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ከሥራ ላይ የሚዉለው»  ብሎ የሚጀመረው ንኡስ አንቀጽ 4 ይሰረዛል።

« የብሄረሰብ መብቶች ከግለሰብ መብቶች ጋር የሚጋጩ ከሆነ ቅድሚያ ለግለሰብ መብት  ይሰጣል» የሚል አንቀጽ ይጨመራል።

አንቀጽ 40

የንብረት መብት

ንዑስ አንቀጽ  3 ፣ 4፣ 5፣ 6፣ 7፣ 8   የዜጎችን የመሬት ባለቤትነት መብት በጠበቀ መልኩ በሚከተሉትን አንቀጾች ይለወጣሉ

ንኡስ  አንቀጽ 3

በገጠርም ሆነ በከተማ በጋራ ወይም በማህበር ባለቤትነት የሚያዝ መሬት ሊኖር ይችላል

ንኡስ  አንቀጽ 4

አርሶ አደሮች በያዙት የእርሻ መሬት ላይ ባለቤትነታቸው በሕግ ተረጋግጦ በፍላጎታቸው የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማከራየት፣ የማውረስ፣ የማስተላለፍ መብታቸው የተጠበቀ ነው።

ንኡስ  አንቀጽ 5

አርብቶ አደሩ ሕብረተሰብ ኑሮው በሂደት ወደ ቋሚ ሰፋሪነት እስኪቀየር ድረስ የሰፈረበት መሬት በመንግስት ይዞታነት ተይዞ እንዲቆይ ይደረጋል።

ንኡስ  አንቀጽ 6

አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ያልሰፈሩበት የአገሪቷ መሬት ለጊዜው በክልል መንግስታት ባለቤትነት ተይዞ ይቆያል። በሂደት በተለያዩ የሕዝብ አገልግሎቶች፣ ለኢንቨስትመንትና መሬት ለሌላቸው አርሶ አደሮች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲከፋፈል ይደረጋል።

ንኡስ  አንቀጽ 7

የእርሻ መሬት የግል ንብረት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሰፋፊና ዘመናዊ እርሻዎችን ፣ እርባታዎችና የመሳሰሉትን የግብርና ተግባራት ለማካሄድ ለሚሹ፣ በግል፣ በሽርክናና በማህበር ለተደራጁ ዜጎች የክልል መንግስታት መሬት በኪራይ ይሰጣሉ።

ንኡስ  አንቀጽ 8

ማንኛዉም የገጠርና የከተማ መሬት ለሕብረተሰቡ የጋራ ጥቅም በክልል፣ ሆነ በፌዴራል መንግስት ሲፈለግ፣ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ካሳ ተከፍሎት ወይም በምትኩ ተሰጦት እንዲለቀቅ የሚያስችል ፖሊሲ ሥራ ላይ እንዲወል ይደረጋል።

አንቀጽ 46

የፌዴራል ክልሎች የሚለው የፌዴራል ክፍለ ሃገራት በሚለው ይተካል።

ንዑስ አንቀጽ 1

«ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝቡ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ የማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት ነው» የሚለው «ክፍለ ሃገራት  የሚዋቀሩት በሕዝቡ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ የመልከዓ ምድር አቀማመጥ፣ ኢኮኖሚ፣ የአስተዳደር አመችነት፣ የሕዝቡን ፍላጎት ባህልና ታሪካን ከግምት በማስገባት ነው» በሚለው ይለወጣል።

አንቀጽ 47

የፌደራል መንግስት አባላት

ንዑስ አንቀጽ 1

አማራጭ 1.

አሁን ያለው የዘጠኝ ክልሎች ዝርዝር  ከታች በተዘረዘሩት  የ 12  ክፍለ ሃገራት  ዝርዝር ይተካል። ይህ አማራጭ አሁን ያለው የፌዴራል አወቃቀር በከፊል እንዲቀጥል አድርጎ ሕብረብሄራዊ የሆኑ የማህበረሰባችን ክፍሎ የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች ሕብረብሄራዊ በሆኑ ክፍለሃገራት ስር እንዲሆኑ ያደርጋል። ለአስተዳደር እንዲያመችም ትላልቅ ክልሎች አሳንሷል።

  1. የሸዋ ክፍለ ሃገር  (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ አዳማ)
  2. የትግራይ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና ትግሪኛ፣ ዋና ከተማ መቀሌ)
  3. የአፋር ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና አፋርኛ፣ ዋና ከተማ አሳይታ)
  4. የቤጌምደር ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ጎንደር)
  5. የጎጃም ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ደብረማርቆስ)
  6. የወሎ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ደሴ)
  7. የምስራቅ ኦሮሚያ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ አሰላ)
  8. የምእራብ ኦሮሚያ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ነቀምቴ)
  9. የሐረርጌ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ኦሮምኛና ሶማሌኛ፣ ዋና ከተማ ድረዳዋ)
  10. የኦጋዴን ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና ሶማሌኛ፣ ዋና ከተማ ጂጂጋ)
  11. የከፋ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ጂማ)
  12. የደቡብ ክፍል ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛ ዋና ከተማ አዋሳ)

የኦሞ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አርባ ምንጭ)

አማራጭ 2

በአጼ ሃይለስላሴ ጊዜና በኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማሪያም አስተዳደር መጀመሪያ አመታት ወቅት የነበሩ ከፍለ ሃገራትን ያካተተ ፌዴራል አወቃቀር ነው።

  1. የሸዋ ክፍለ ሃገር  (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ አዳማ)
  2. የትግራይ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና ትግሪኛ፣ ዋና ከተማ መቀሌ)
  3. የቤጌምደር ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ጎንደር)
  4. የጎጃም ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ደብረማርቆስ)
  5. የወሎ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ደሴ)
  6. የኢሊባቡር ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ መቱ)
  7. የወለጋ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ነቀምቴ)
  8. የአርሲ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ኦሮምኛና ዋና ከተማ አሰላ)
  9. የሃርርጌ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ኦሮምኛና ሶማሌኛ፣ ዋና ከተማ ሃረር)
  10. የባሌ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ጎባ)
  11. የከፋ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ጂማ)
  12. የጋሞጎዳ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ ዋና ከተማ አርባ ምንጭ)
  13. የሲዳሞ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አዋሳ)

አማራጭ 3

አሁን ያለው የዘጠኝ ክልሎች ዝርዝር  ከታች በተዘረዘሩት  የ 29  ክፍለ ሃገራት  ዝርዝር ይተካል። ኢሕአዴግ ስልጣን ከመያዙ በፊት በኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማሪያም አስተዳደር ወቅት የነበሩ፣ ኤርትራን ያልጨመረ፣  የአስተዳደር ግዛቶችን እንደ ፌዴራል ክፍለ ሃገራት የወሰደ አማራጭ ነው። የምስራቅ ሃረርጌና የኦጋዴ ግዛቶች ማሻሻያ ተደረጎባቸዋል። ክፍለ ሃገራት አነስ ባሉ ቁጥር ለአስተዳደር አመች ከመሆኑም በተጨማሪ ሕዝብ አገልግሎት ለማግነት ረጅም ረቀት መጓዝና መጓላላት አይኖርበትም።

  1. አዲስ አበባ  (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አዲስ አበባ)
  2. የሰሜን ሸዋ ክፍለ ሃገር  (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ደብረብርሃን)
  3. የምስራቅ ሸዋ ክፍለ ሃገር  (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ወሊሶ)
  4. የምእራብ  ሸዋ ክፍለ ሃገር  (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ አምቦ)
  5. የደቡብ ሸዋ ክፍለ ሃገር  (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ አዳማ)
  6. የትግራይ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ትግሪኛ፣ ዋና ከተማ መቀሌ)
  7. የሰሜን ጎንደር  ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ጎንደር)
  8. የደቡብ ጎንደር  ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ  ደብረታቦር)
  9. የሰሜን ወሎ  ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ወልዲያ)
  10. የደቡብ ወሎ  ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ደሴ)
  11. የምስራቅ ጎጃም  ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ባህር ዳር)
  12. የምእራብ ጎጃም  ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ደብረማርቆስ)
  13. የመተክል ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ፓዊ)
  14. የአሳሳ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አሶሳ)
  15. የወለጋ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ነቀምቴ)
  16. የጋምቤላ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ጋምቤላ)
  17. የኢሊባቡር ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ መቱ)
  18. የከፋ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣  ዋና ከተማ ጂማ)
  19. የሰሜን ኦሞ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አርባ ምንጭ)
  20. የደቡብ ኦሞ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ጂንካ)
  21. የሲዳሞ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አዋሳ)
  22. የቦረና ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ ዋና ከተማ ጋምቤላ)
  23. የአርሲ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ አሰላ)
  24. የባሌ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ጎባ)
  25. የምስራቅ ሃረርጌ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ሃረር)
  26. የምእራብ ሃረርጌ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ ጭሮ/አሰበ ተፈሪ)
  27. የድሬዳዋ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ሶማሌኛ፣ ዋና ከተማ ድሬዳዋ)
  28. የኦጋዴን ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ሶማሌኛ፣ ዋና ከተማ ጂጂጋ)
  29. የአፋር ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና አፋርኛ፣ ዋና ከተማ አሳይታ)

አማራጭ 4

አሁን ያለው የዘጠኝ ክልሎች ዝርዝር  ከታች በተዘረዘሩት  የ5   ክፍለ ሃገራት  ዝርዝር ይተካል። ክፍለ አገራቱ በስፋት፣ በሕዥብ ብዛትና በኢኮኖሚ ተመጣጣኝ እንዲሆኑ የሚረዳ፣ ቀለል ያለ የፌዴራል አወቅቀር አማራጭ ነው።

  1. የመካከለኛ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ አዳማ)
  2. የምስራቅ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ሶማሌኛና አፋርኛ ዋና ከተማ ድሬዳዋ)
  3. የሰሜን ክፍለ ሃገር ((የስራ ቋንቋ አማርኛና ትግሪኛ ዋና ከተማ ደብረታቦር)
  4. የደቡብ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አዋሳ)
  5. የምእራብ ክፍለሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ፣ ነቀምቴ)

አማራጭ 5

አሁን ያለው የዘጠኝ ክልሎች ዝርዝር  ከታች በተዘረዘሩት  የ10  ክፍለ ሃገራት  ዝርዝር ይተካል። በኢሕአዴግ መንግስት የተዘረጋዉን አወቃቅር ከሞላ ጎደል የሚያስቀጥል አማራጭ ነው። የአዲስ አበባ ጉዳይን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትና የአዲስ አበባን ህዝብ መብት ለማክስከበር፣ አዲስ አበባ እንደ አንድ የፌዴራል መንግስት አባል ትቆጠራለች። ያልተፈታውን የድሬዳዋን ችግር እልባት ከመስጠት፣ድሬዳዋንም ከሃረሬ ክልልና በድረዳዋና ከሃረር ከተማ መካከል ያሉትን አካባቢዎች ፣ እንዲሁም የሶማሌ ክልል የሽንሌን ዞን በመጨመር፣ የሃረርጌ ክፍለ ሃገር ይኖራል።

በሁሉ ክፍለ ሃገራት አማርኛ የስራ ቋንቋ ስለሚሆን በኦሮሚያም ሆነ በትግራይ የሚኖሩ ኦሮምኛ ወይም ትግሪኛ የማይናገሩ ማህበረሰባት መብት የሚከበርነት ሁኔታ ይኖራል።፡

ይህ አማራጭ ለዘለቂታ ጠቃሚ አማራጭ ባይሆንም በጊዜያዊነት ግን ሊያገለግል የሚችል አማራጭ ነው።

  1. የአዲስ አበባ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አዲስ አበባ)
  2. የሃረርጌ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ኦሮምኛና ሶማሌኛ ዋና ከተማ ድሬዳዋ)
  3. የትግራይ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ትግሪኛ፣ ዋና ከተማ መቀሌ)
  4. የአፋር ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦፋርኛ፣ ዋና ከተማ አዳማ)
  5. የአማራ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ባህር ዳር)
  6. የኦሮሚያ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛና ኦሮምኛ፣ ዋና ከተማ አዳማ)
  7. የደቡብ ክፍለ ሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አዋሳ)
  8. የጋምቤላ ክፍለ ሃገር((የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ ጋምቤላ)
  9. የሶማሌ ክፍለ ሃገር(የስራ ቋንቋ አማርኛና ሶማሌኛ፣ ዋና ከተማ ጂጂጋ)
  10. የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክፍለሃገር (የስራ ቋንቋ አማርኛ፣ ዋና ከተማ አሶሳ)

ንዑስ አንቀጽ 2 ፣ 3 ይሰረዛሉ።

አንቀጽ 49

አዲስ አበባ በሸዋ ወይም መካከለኛ ክፍለ ሃገር ስር ወይንም ራሷን የቻለች ክፍለ ሃገር ስለምትሆን  ንዑስ አንቀጽ 2፣ 3 እና 4 ይሰረዛሉ።

አንቀጽ 50

ስለ ስልጣኝ አካላት አወቃቀር

ንዑስ አንቀጽ 3

«የፌዴራሉ መንግስት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌደራሉ መንግስት የሕዝብ ተወክዮች ምክር ቤት ነው። ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ ነው። የክልሉ ከፍተኛ የስልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው።፡ተጠሪነቱም ለወከለው ክልል ሐዝብ ነው» የሚለው «የፌዴራሉ መንግስት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌደራሉ የሕዝብ ተወክዮች እና የፈዴሬሽን ምክር ቤቶች ነው ። ተጠሪነታቸዉም ለሀገሪቱ ሕዝብ ነው። የክፍለ ሃገራቱ  ከፍተኛ የስልጣን አካል የክፍለ ሃገራቱ  ምክር ቤት ነው። ተጠሪነቱም ለወከለው ክፍለ ሃገር  ሕዝብ ነው»

አንቀጽ 61

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት

ንዑስ አንቀጽ 1

«የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራል መንግስት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የሚልኩዋቸው አባላት የሚወክሉት ምክር ቤት ነው» የሚለው «የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራል መንግስት የክፍለ ሃገራት  ሕዝቦች በቀጥታ በመረጧቸዉ አባላት የሚወክሉት ምክር ቤት ነው» በሚለው ይተካል።

ንዑስ አንቀጽ 2

«እያንዳንዱ ብሄር ፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል። በተጨማሪም የብሔር ወይም ብሔረሰቡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ወኪል ይኖረዋል» የሚለው «እያንዳንዱ ክፍለ ሃገር  ሁለት ተወካዮች ይኖሩታል» በሚለው የቀየራል።

ንዑስ አንቀጽ 3  ይሰረዛል።

አንቀጽ 62

የፌዴረሽኑ ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር

ንዑስ አንቀጾች 1፣ 2፣ 3፣ 4፣ 5፣ 6፣ 7፣ ፣ 8፣ 9፣ 10፣ 11   ይሰረዛሉ።

«የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡት ሚኒስትሮችን ያጸድቃል» የሚል ንዑስ አንቀጽ ይጨመራል።

«በፕሬዘዳንቱ የቀረቡ የጠቅላይ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዳኞችን ያጸድቃል» የሚል ንዑስ አንቀጽ ይጨመራል።

«በፕሬዘዳንቱ የቀረቡ የምርጫ ቦርድና የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን አባላትን እና ዋና ኦዲተሩን ያጸድቃል።» የሚል ንዑስ አንቀጽ ይጨመራል።

አንቀጽ 70      

የፕሬዘዳንቱ አሰያየም

ንዑስ አንቀጽ 1

«ለፕሬዚዳንትን እጩ የማቅረብ ስልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው» የሚለው «ለፕሬዚዳንትና እጩ የማቅረብ ስልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው» በሚለው ይተካል።

አንቀጽ 71

የፕሬዘዳንቱ ሥልጣንና ተግባር

«የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሌሎች ዳኞችን ፣የምርጫ ቦርድ አባላት፣ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽነሮችን እና የዋና ኦዲተርን ሾሞ፣ ለፈዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል።» የሚል ንዑስ አንቀጽ ይጨመራል።

«ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክር ቤት የሚቀርብለትን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል» የሚል ንዑስ አንቀጽ ይጨመራል።

አንቀጽ 74

የጠቅላይ ሚኒስተሩ ሥልጣንና ተግባር

ንዑስ አንቀጽ 7

«ኮሚሽነሮችን፣ የማእከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት፣ ምክትል ፕሬዘዳንትና እና ዋና ኦዲተርን መርጦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን ያጸድቃል»  የሚለው ይሰረዛል።

አንቀጽ 75

ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሩ

ንኡስ አንቀጽ 1/ለ  «ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለረጅም ጊዜ በሕመም ወይንም ሌሎች ምክንያቶች መስራትና መወሰን በማይችሉበት ጊዜ፣  ወይንም በሞት ከዚህ አለም ሲለዩ፣ ፓርላማው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስተር እስሚከርጥ ድረስ፣ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነ፣ ሙሉ የጠቅላይ ሚኒስተርነት ሃላፊነትና ስልጣን ተቀብሎ ይሰራል» በሚለው ተሻሽሎ ይቀርባል።

«ከአንድ በላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር አይኖርም» የሚል ሌላ ንኡስ አንቀጽ ይገባል።

አንቀጽ 78

ስለ ነጻ የዳኝነት አካል

ንዑስ አንቀጽ 2

«የፈዴራል መንግስት ከፍተኛ የዳኝኘት አካል የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሆናል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሆነ የመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት በሀገሪትይ በሙሉ ወይም በከፉል እንዲደራጅ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ሊወስን ይችላል። ጉዳዩ በዚህ አኳኋን ካልተወሰነ የፌዴራል ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ለክልል ፍርድ ቤቶች ተሰጥቷል» የሚለው «የፈዴራል መንግስት ከፍተኛ የዳኝኘት አካል የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሆናል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሆነ የመጀመሪያው ደረጃ ፍርድ ቤት በሀገሪቱ በሙሉ ወይም በከፉል እንዲደራጅ በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ሊወስን ይችላል። ጉዳዩ በዚህ አኳኋን ካልተወሰነ የፌዴራል ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ለክፍለ ሃገር ፍርድ ቤቶች ተሰጥቷል» በሚለው ይተካል።

ንዑስ አንቀጽ 5

«የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልሎች ምክር ቤቶች በአንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 5 መሰረት የኃይማኖትና የባሕል ፍርድ ቤቶችን ሊያቋቍሙ ወይም እውቅና ሊሰጡ ይችላሉ። ይህ ሕግ መንግስት ከመጽደቁ በፊት በመንግስት እውቅና አግኝተው ሲሰራባቸው የነበሩ ኃይማኖቶችና የባሕል ፍርድ ቤቶች በዚህ ሕገ መንግስት መሰረት እውቅና አግኝተው ይደራጃሉ» የሚለው «የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የክፍለ ሃገር ምክር  ቤቶች በአንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 5 መሰረት የኃይማኖትና የባሕል ፍርድ ቤቶችን ሊያቋቍሙ ወይም እውቅና ሊሰጡ ይችላሉ። ይህ ሕግ መንግስት ከመጽደቁ በፊት በመንግስት እውቅና አግኝተው ሲሰራባቸው የነበሩ ኃይማኖቶችና የባሕል ፍርድ ቤቶች በዚህ ሕገ መንግስት መሰረት እውቅና አግኝተው ይደራጃሉ» በሚለው ይተካል።

«የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንቱን ጨምሮ የሚኖሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ቁጥራቸው ሰባት ይሆናል።» የሚል ንዑስ አንቀጽ ይጨመራል።

«ሰባቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ያካታተና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ የሚመራ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክር  ቤት ይኖራል» የሚል ንዑስ አንቀጽ ይጨምራል።

«የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክር ቤት፣  የዳኞች አስተዳደር ጽ/ቤትን  ያቋቁማል። የዳኞች አስተዳደር ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክር ቤት ሆኖ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን፣  እንዲሁም ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችን አስተዳደራዊ ሥራ ያከናወናል።» የሚል ንዑስ አንቀጽ ይጨመራል።

አንቀጽ 79

የዳኝነት ሥልጣን

ንዑስ አንቀጽ 4/ሐ  «የጉባዔው ዉሳኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በክልል ምክር ቤቶች ከግማሽ በላይ ድምጽ ሲጸድቅ»  የሚለው  ««የጉባዔው ዉሳኔ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም በክፍለ ሃገራት ምክር ቤቶች ከሁለት ሶስተኛ በላይ ድምጽ ሲጸድቅ» በሚለው ይሻሻላል።

አንቀጽ 81

ስለዳኞች አሿሿም

ንዑስ አንቀጽ 1

«የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንት በፌዴራል መንግስት ጠቅላይ ሚኒስተር አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ» የሚለው «የፈዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ ጨምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞ በአገሪቷ ፕሬዘዳንት አቅራቢነት፣  በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሾማሉ። » በሚል ይሻሻላል።

ንኡስ አንቀጽ 2

«ሌሎች የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን በተመለከተ በፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የቀረበለትን እጩዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያሾማል» የሚለው «የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን በተመለከተ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የቀረበለትን እጩዎች የአገሪቷ ፕሬዘዳንት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ ያሾማል» በሚለው ይሻሻላል።

አንቀጽ 82

ይሰረዛል

አንቀጽ 83

ይሰረዛል

አንቀጽ 84

ይሰረዛል

አንቀጽ 101

ዋናዉ ኦዲተር

ንዑስ አንቀጽ 1

«ዋናዉ ኦዲተር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል» የሚለው «ዋናዉ ኦዲተር በፕሬዘዳንቱ አቅራቢነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሾማል በሚለው ይሻሻላል።

አንቀጽ 102

የምርጫ ቦርድ

ንዑስ አንቀጽ 2

«የቦርዱ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ።» የሚለው «በፕሬዘዳንቱ አቅራቢነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሾማሉ» በሚለው ይሻሻላል።

አንቀጽ 103

የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን

ንዑስ አንቀጽ 2

«የኮሚሽኑ አባላት በጠቅላይ ሚኒስተሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ»> የሚለው «የኮሚሽኑ አባላት በፕሬዘዳንቱ አቅራቢነት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሾማሉ» በሚለው ይሻሻላል።

ንዑስ አንቀጽ 6

«የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ስለ ሥራዉ አፈጻጸም በየጊዜ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል» የሚለው «የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለፈዴሬሽን ምክር ቤት ነው። ስለ ሥራዉ አፈጻጸም በየጊዜዉ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል» በሚለው ይሻሻላል።

አንቀጽ 105

ንዑስ አንቀጽ 1     ይሰረዛል

ንዑስ አንቀጽ 2

«በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ከተዘረዘሩት ዉጭ ያሉት የሕጘ መንግስቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳኋን ብቻ ይሆናል» የሚለው «የዚህ መንግስቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳኋን ብቻ ይሆናል» በሚለው ይሻሻላል።

በፒ.ዴ.ኤፍ ለማንበብ