ጎንደር ከነገ ጀምሮ ማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አይኖርም

DW : በጎንደር ከተማ ማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከነገ ጀምሮ አይኖርም
ከሌሎች አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሚያስገቡና ከከተማዋ የሚስወጡ የህዝብ ተከርካሪዎች መውጫና መግቢያ በሮቿን ደግሞ ከትናንት ጀምሮ ዘግታለች፡፡
የተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የኮሮና ተሐዋሲን ለመከላከል የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰዱ ነው፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደርም ከትናንት ጀምሮ የተለያዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሸመ አግማስ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ (DW) በስልክ እንደተናገሩት ከነገ መጋቢት 26 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ርምጃ በከተማ ውስጥ በሚገኙ መዝናኛ ቦታዎችና የከተማ ውስጥ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ወሴኔ ተላልፏል፡፡
ምክትል ከንቲባው እንዳሉት መዝናኛ ስፍራዎች፣ አዝማሪ ቤቶች፣ መሸታ ቤቶች፣ ጫት ቤቶችና ሌሎች ሰዎች በርከት ብለው የሚገለገሉባቸው ቦታዎች ከነገ ጀምሮ ለ14 ተከታታይ ቀናት አገልግሎት አይሰጡም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በከተማው ውስጥ ጋሪዎችንና ሞተር ብስክሌቶችን ጨምሮ ማነኛውም የህዘብ አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪ በእገዳው እንደተካተተ ምክትል ከንቲባው አቶ ተሸመ አብራርተዋል፡፡
ምግብ ቤቶች ወንበራቸውን በግማሸቀንሰው አንዲያስተናግዱ ወፍጮ ቤቶችና ክሊኒክና ፋርማሲዎች ሳይዘጉ በጥንቃቄ ህቡን የሚያገለግሉ እንደሚሆኑም ምከትል ከንቲባው አመልክተዋል፡፡
አቶ ተሸመ አያይዘውም የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከየትኛውም አቅጣጫ ወደ ከተማዋ የሚገባንና ከከተማዋ የሚወጣን የህዝብ ትራንስፖርት ማገዱንና ተግባራዊ መደረጉን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
ምክትል ከንቲባው አቶ ተሸመ አግማስ እንደተናገሩት ከአጎራባች ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በመመካከር ከየትኛውም አቅጣጫ ወደ ጎንደር ከተማ የሚገባና ከጎንደር ከተማ የሚወጣ የህዝብ ትራንስፖርት ከትናንት መጋቢት 24 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
አንዳንድ በስልክ ያነጋገርናቸው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ወሳኔው ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በተለይ ወደ ከተማዋ በሚወጡና በሚገቡ የህዝብ ተሸከርካሪዎች ላይ የተሰጠው የማስጠንቀቂያ ጊዜ በቂ አይደም ውሳኔውም ከእጅ ወደ አፍ የሚተዳደረውን ህብረተስብ የሚጎዳ በመሆኑ በመውጫና መግቢያ በሮች ላይ መመርመሪያ መሣሪያ ገጥሞ መመረመሩ ተመራጭ ይሆን ነበር ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ፣ አዲስ ቅዳም፣ ቲሊሊና በክልሉ ማዕከል ባሕር ዳር ተመሳሳይ እርምጃዎች መወሰዳቸው ይታወሳል፡፡