" /> ሞዛምቢክ የጭነት መኪና ውስጥ ህይወታቸው አልፎ የተገኙት 64 ኢትዮጵያዊያን ቀብር ተፈጸመ። | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

ሞዛምቢክ የጭነት መኪና ውስጥ ህይወታቸው አልፎ የተገኙት 64 ኢትዮጵያዊያን ቀብር ተፈጸመ።

BBC Amharic : ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ሲጓዝ በነበረበት የጭነት መኪና ውስጥ ህይወታቸው አልፎ የተገኙት 64 ኢትዮጵያዊያን ቀብር ተፈጸመ።

ቴቴ ግዛት ውስጥ ያለ ድልድይየሞዛምቢክ ባለስልጣናት እንዳሉት በኮንቴነር ውስጥ ሞተው የተገኙትን ኢትዮጵያዊያን የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ እዚያው ሞዛምቢክ ውስጥ ፈጽሟል።

ማክሰኞ ዕለት አስክሬናቸው የተገኘው ኢትዮጵያዊያን በአየር እጥረት ታፍነው ሳይሞቱ እንደማይቀር በስፋት ተገምቷል።

በሞዛምቢክ ምዕራባዊ ግዛት ቴቴ በተባለችው ክፍለ አገር ውስጥ ተሽከርካሪ ላይ ኮንቴነር ውስጥ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 14 ሰዎች በህይወት መገኘታቸው ይታወሳል።

“የሞዛምቢክ የኢሚግሬሽን አገልግሎት ሰራተኞች የጭነት መኪናውን አስቁመው ሲፈትሹ ነው ሟቾቹን ያገኙት” ሲሉ የአካባቢው ባለስልጣን ተናግረው ነበር።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ከሁለት ቀናት በፊት ለቢቢሲ ሲናገሩ “ከማላዊ ወደ ሞዛምቢክ ጉዞ እያደረጉ ሳለ ነው ይህ አሳዛኝ ነገር የተፈጠው” ብለው ነበር።

አምባሳደሩ ከ78 ተጓዞች የ64ቱ ሕይወት ማለፉን አረጋግጠውም ነበር።

የሞዛምቢክ ባለስልጣናት ኢትዮጵያዊያኑ መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ ያደረጉ ስደተኞች ናቸው ብለዋል።

በህይወት የተረፉት 14ቱ ኢትዮጵያዊያን በሞዛምቢክ የኮሮናቫይረስ ምረመራ እንደተደረገላቸው ተነግሯል። ምንም እንኳ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ቢረጋገጥም ስደተኞቹ ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ሙቀት አላቸው መባሉን ተከትሎ ወደ ለይቶ ማቆያ መወሰዳቸው ተገልጿል።

የሞዛምቢክ ብሔራዊ የስደተኞች አግልግሎት ቃል አቀባይ የሆኑት አሜሊዓ ዲሬኢቶ አንዳሉት “የ64ቱን ስደተኞች እስክሬን ለመለየት እንዲያመች ቁጥር ተሰጥቶት ቀብር ተፈጽሟል። የኢትዮጵያ ኤምባሲም ከግዛቱ የስደተኞች አገልግሎት ጋር ተገናኝቷል” ብለዋል።

በህይወት የተረፉ ኢትዮጵያዊንን በሚመለከት ደግሞ “ከኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ጋር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው” ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሁለት የሞዛምቢክ ዜጎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV