" /> ቫይረሱን ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ካልቻልን የሚመጣውን ጫና መሸከም እንችልም – ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

ቫይረሱን ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ካልቻልን የሚመጣውን ጫና መሸከም እንችልም – ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

«ቫይረሱን ለመከላከል ቅድመ – ዝግጅት ማድረግ ካልቻልን የሚመጣውን ጫና መሸከም አንችልም፡፡»
የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)
Imageየኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በራስ ሆቴል «ሙሉ ኃይላችንን የኮሮና ቫይረስ (COVID – 19)ን ጫና ለመቋቋም እናውለው!» በሚል መሪ ቃል ለመንግሥትና ለግል ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኢዜማ ጋዜጣዊ መግለጫ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ በመከፋፈል ሀገሪቱ ሊያጋጥማት የሚችለው ተግዳሮቶች በቀጣይ በሀገሪቱ ሊደረግ የሚገባውን ቅድመ ጥንቃቄ ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡
ኢዜማ በመግለጫው በምዕራብ ኦሮሚያ የተዘጋው የስልክ እና የበይነ መረብ ግንኙነት በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች እራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል የሚረዳቸውን መረጃ ለማድረስ እና ከአካባቢው ወረርሺኙን በሚመለከት መረጃ ለመሰብሰብ ተግዳሮት ስለሚሆን የስልክ እባ የበይነ መረብ ግንኙነቱ ወደሥራ እንዲመለስ ጠይቋል።
Imageመንግሥት የቫይረሱ ወረርሺኝ በንግድ እንቅስቃሴ እና በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቋቋም እንዲቻል የግል ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ 27% በመመሪያ እንዲገዙ ተገደው ከነበረው የብሔራዊ ባንክ ቦንድ ውስጥ ጊዜያቸው የደረሰውን እና ሊደርስ የተቃረበውን ቦንድ ገንዘብ እንዲከፈላቸው እና ያጋጠማቸውን የገንዘብ እጥረት ቀርፈው የንግዱን እንቅስቃሴ እንዲደግፉ እንዲደረግ ኢዜማ ጠይቋል። ወረርሺኙ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድርባቸው ዘርፎችን በመለየት የግብር ቅነሳ እና የሚሰበሰብበትን ጊዜ ማራዘም እንዲሁም ከባንክ የተበደሩትን ገንዘብ የሚመልሱበትን ጊዜ በማራዘም የግል ዘርፉ ወደሠራተኛ ቅነሳ እና ሥራቸውን ወደማቆም እንዳይሄድ ድጋፍ እንዲደረግም በመግለጫው ተጠይቋል።
የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) «በአሜሪካ ከሳምንት በፊት በኮሮና ቫይረስ የተጠቁት በመቶዎች የሚቆጠሩ ብቻ ነበሩ አሁን ግን የኮሮና ተጠቂዎች 42 ሺህ ደርሰዋል።… ብዙዎቹ ሀገሮች ለዚህ የተዳረጉበት ዋነኛ ምክንያት ቅድመ ዝግጅት ባለማድረጋቸው ነው፡፡ ቫይረሱን ለመከላከል ቅድመ – ዝግጅት ካላደረግን የሚመጣውን ጫና መሸከም አንችልም፡፡ የሚያስፈልገውን ጥንቃቄ ከአሁኑ ከምር ወስደን መተግበር ካልቻልን በፍፁም ልንወጣው የማንችለው ችግር ውስጥ ነው የምንገባው። ማንኛውም ሰው አስፈላጊ ካልሆነ በቀር በተቻለ መጠን እራሱን በቤቱ ብቻ እንዲወስን ማድረግ ናቸው አደጋውን ለመቋቋም የሚረዱን» ሲሉ አስጠንቅቀዋል። «አሁን በኮሮና የተያዙ 12 ሰዎች የተገኙት የተመረመሩት ብቻ ናቸው፡፡ ቁጥሩም ይሄ ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡» ብለዋል፡፡
የኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ የቀጣዩን ሀገር አቀፍ ምርጫና የምርጫ ቦርድን ሰሌዳ በተመለከተ «ምርጫም ፖለቲካም የሚኖረው ሰው ሲኖር ነው፡፡ እኛ ቅድሚያ ሕዝቡን ከኮሮና እንዴት ማዳን እንችላለን የሚለው ነው የሚያሳስበን፤ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ቀርቶ ያደጉ ሀገራትም መቋቋም አቅቷቸዋል፡፡ …አሁን መንግሥት ሥርጭቱን ለመግታት ለ15 ቀን የጣላቸው ዕቀባዎች የምርጫ ቦርድ ብዙ ሥራዎች ተስተጓጉለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ምርጫ ቦርድ በያዘው እቅድ መሠረት መሄድ እንደማይችል ፓርቲዎችን ሰብስቦ ባናገረበት ወቅት ገልጿል» ብለዋል።

 


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV