" /> መከራ ሲመጣ የማንሞትለትን ሕዝብ ለሞት አናመቻቸው – ዲያቆን ዳንኤል ክብረት | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

መከራ ሲመጣ የማንሞትለትን ሕዝብ ለሞት አናመቻቸው – ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

መታዘዝን የገፋ አገልግሎት – ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
ትናንት ቅዱስ ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስን ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ በየአጥቢያው ያሉ ካህናትና ምእመናን ግን እንደ ዘመነ መሳፍንት በራሳቸው ሐሳብ ብቻ ነው የሚጓዙት፡፡ ማዕጠንትን በተመለከተ በቁጥር 9 ላይ የተቀመጠው ሕግ ‹ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ፣ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምሕረትና በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ ዕጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ› ይላል፡፡
በዚህ አንቀጽ ላይ ማን ማድረግ፣ የት መደረግ፣ ምን መደረግ፣ እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ጸሎተ ዕጣን እየተጸለየ ማዕጠንት እንዲፈጸም ታዝዟል፡፡ ይሄን መፈጸም ያለባቸው ‹ካህናት ብቻ› መሆናቸው ተገልጧል፡፡ መደረግ ያለበትም ‹በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምሕረትና በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ› መሆኑን ይገልጣል፡፡ ዛሬ ጠዋት በየአጥቢያው እየታየ ያለው ነገር ግን አሳዛኝ ነው፡፡ ትናንት በዋዜማው ምእመናን በ11 ሰዓት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማዕጠንት እንዲመጡ በመኪና እየተዞረ ጥሪ ሲደረግ ነበር፡፡ ይህ ከልክ በላይ ሰዎች በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰባሰቡ ያደርጋል፡፡ በአዲስ አበባ ቅዱስ ሩፋኤል ዛሬ የታየው ይሄ ነው፡፡ ቅጽረ ግቢው ሞልቶ መንገዱ ሰው በሰው ሆኖ ነበር፡፡ ሕዝቡ እንደ አምስቱ ገበያ ሕዝብ እርስ በርሱ ይጋፋ ነበር፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ካህናቱ በየመንደሩ እየዞሩ እያጠኑ ነው፡፡ ይህ ሲደረግም በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ተጠጋግተው እየጠከተሏቸው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ይህን አልፈቀደችም፡፡ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምሕረትና በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ነው ያዘዘችው፡፡ በአንዳንድ አጥቢያዎች ደግሞ ‹ከ11 ሰዓት ጀምሮ በራችሁን ከፍታችሁ ጠብቁ› የሚል ዐዋጅ በመኪና ላይ በተገጠሙ ስፒከሮች ሲታወጅ ነበር፡፡ ይህም ስሕተት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አላለችም፡፡ ከዚያም በላይ በአንዳንድ ቦታዎች አድራሻቸው የማይታወቅ፣ የአጥቢያ ካህናት ያልሆኑ፣ የመነኮሳትን ልብስ የለበሱ ‹ካህናት› በቤታቸው መጥተው እንደነበር ምእመናኑ እየተናገሩ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ክህነትንና ቤተ ክርስቲያንን የሚያሳጣ ነው፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የንግሥ በዓላትን ለጊዜው ያሻገረው በሕዝብ መጨናነቅ እንዳይፈጠርና ምእመናን ለአደጋ እንዳይጋለጡ ነው፡፡ አጥቢያዎቹ ግን የተከለከለውን የንግሥ በዓል እንደገና እያመጡት ነው፡፡
አሁን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ክትትል ሊያደርግ ይገባል
1. የንግሥ በዓል በሚመስል መልኩ እየተከናወነ ያለው የማዕጠንት ጉዳይ ከትእዛዙ ውጭ ነውና እንዲታረም ይደረግ፤
2. አንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች የቅዱ ሲኖዶስን መመሪያ እንደማይቀበሉ በአደባባይ መናገር ጀምረዋልና ክትትል ተደርጎ ማረሚያ ይሰጥ፤
3. በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እንዲፈጸሙ የታዘዙ ነገሮች እየተፈጸሙ መሆናቸውን የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ክትትል ያድርጉ፤
‹መታዘዝ ከመሥዋዕትነት ይበልጣል› የሚለውን ቃል ስንሰማው እንዳልኖርን፣ መታዘዝን የገፋ አገልግሎት ውስጥ መግባት ድህነት እንጂ ድኅነት አይሆነንም፡፡
ተዉ፤ መከራ ሲመጣ የማንሞትለትን ሕዝብ ለሞት አናመቻቸው፡፡

የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV