የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰባት ሴት ተመራማሪዎች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያዊት

ዶክተር ሰገነት ቀለሙ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅርንጫፍ የሆነው ዩ ኤን ውሜን ሰሞኑን የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰባት ሴት ተመራማሪዎችን ይፋ አድርጓል።

ከእነዚህ ሰባት ስመጥር ተመራማሪዎች መካከል ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ ዶ/ር ሰገነት ቀለሙ ተካትተውበታል። ዶ/ር ሰገነት የሥራና የሕይወት ተሞክሯቸውን ለቢቢሲ ከዚህ ቀደም አካፍለው ነበር።

ተቀማጭነቱ ናይሮቢ – ኬንያ የሆነው የነፍሣት አካላት እና አካባቢ ጥናት ዓለምአቀፍ ማዕከል (ኢሲፔ) ዋና ዳይሬክተር ናት። ከክብር ዶክተሬት ጀምሮ በርካታ አለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘችው ዶክተር ሰገነት ስለህይወትና ሥራዋ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ዶክተር ሰገነት ቀለሙ ተወልዳ ያደገችው ፍኖተ ሰላም ነው። ፍኖተ ሰላም ያኔ በጣም ትንሽ የገጠር መንደር እንደነበረች ታስታውሳለች።

በፍኖተ ሰላም ያኔ መብራት አልነበረም፣ የቧንቧ ውሃ አልነበረም፣ ምንም ነገር አልነበረም፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አልነበረም።

ስለዚህ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለመከታተል የ13 ዓመቷ ሰገነት ደብረ ማርቆስ ሔደች። እንደ ዶ/ር ሰገነት ገለፃ ደብረማርቆስ ያኔ መብራት የነበራት ቢሆንም ሌላው ነገሯ ከፍኖተ ሰላም ጋር ተመሳሳይ ነበር።

ከቤተሰብ ማንም አብሯት አልነበረም “ወላጆቼ በእኔ ላይ እምነት ነበራቸው ። የትም ብሄድ ራሴን ተንከባክቤ እንደማስተዳደር ያውቃሉ” ስትል ቤተሰቦቿ በእርሷ ላይ ያላቸውን መተማመን ትናገራለች።

እንጨት ለቅማ፣ እህል በእጇ ፈጭታ፣ ብቅል አብቅላ፣ ደረቆት ለጠላ አዘጋጅታ ቤተሰቦቿን እያገዘች ነው የተማረችው።

“ያኔ የፊደል ዘር እለያለሁ ብሎ የትምህርት ቤት ደጃፍ የረገጠ ፈተና የሚሆንበት ደብተር፣ እስክሪብቶ፣ እርሳስ ማሟላት ነው። ትምህርት ቤቱም ቢሆን በቁሰቁስ እና በመጻህፍት የተሟላ አይደለም” ትላለች ዶ/ር ሰገነት።

ይህ ልምዷ ዛሬም በቢሮዋ እርሳስና እስክርቢቶ እንድትሰበስብ አድርጓታል።

በልጅነቴ አስቸጋሪ ነበርኩ የምትለው ዶ/ር ሰገነት ዛፍ ላይ መውጣት፣ አህያ መጋለብ፣ ሴት አትሰራውም የተባለውን በሙሉ ለመስራት ትሞክር ነበር።

በልጅነቷ ቤታቸው እህቶቿን ለማጨት ሽማግሌ ሲላክ ለእሷ የመጣ አንድም ጠያቂ ግን አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ ማህበረሰቡ ሴት ልጅ መሆን አለባት ከሚለው ውጭ መሆኗ ነበር።

ስለዚህ እንደሌሎቹ በልጅነቷ ሳትዳር በትምህርቷ ገፋች።

የዶ/ር ሰገነት ቤተሰቦች ማንበብ እና መፃፍ ባይችሉም በትምህርት ያምኑ ነበር። ስለዚህ ልጆቻቸውን ባጠቃላይ አስተምረዋል።

“ሰባት እህት እና ወንድማማቾች ባጠቃላይ ነበርን ሁላችንም ትምህርት ቤት ሄደናል።” በርግጥ እህቶቿ ቀደም ብለው ያገቡ ቢሆንም ተምረዋል።

ዶክተር ሰገነት ቀለሙ

ሕይወት በዩኒቨርስቲ

ዶክተር ሰገነት ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ውጤት ስታመጣ ጎረቤቶቿ ጠላ፣ አረቄ፣ ምግብ እየያዙ መጥተው ቤተሰቦቿን ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ እያሉ ቀኑን ሙሉ እንዳሳለፉ አትረሳውም።

ከአንዲት ገጠር መንደር ወጥታ ሰፊ ወደሆነችው አዲስ አበባ ስትመጣ ግራ ተጋብታ ነበር።

“መፀዳጃ ቤት እኛ ሜዳ ላይ ነው የለመድነው እዛ ሄደክ ቤት ውስጥ ነው፤ እንዴት ውሃ እንደሚለቀቅ አታውቅም። ሻወር ቤት ውስጥ ነው የምትታጠበው፤ …ፍኖተ ሰላም ሆነን ወንዝ ውስጥ ሄደን ነው ገላችንን እንታጠብ ነበረው። ትልቅ ልዩነት ነው” ትላለች ስለነበረው ሁኔታ ስታስረዳ።

ቴሌቪዥን እና ስልክ አጠቃቀምም ሌላ እንግዳ ነገር ነበር።

ዶክተር ሰገነት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካጠናቀቀች በኋላ ለሁለተኛ ዲግሪዋ አሜሪካሄደች። ሁለተኛ ዲግሪዋን ከመጨረሷ በፊት ለሶስተኛ ዲግሪዋ የነፃ ትምህርት እድል አገኘች። ያንን ስትጨርስ ደግሞ ብዙ ቦታ የስራ በር ተከፈተላት። ከሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ኮርኔል ዩኒቨርስቲን መርጣ ሄደች።

አባቴ የህክምና ዶክተር እንድሆን ነበር የሚፈልገው የምትለዋ ዶክተር ሰገነት “አለማያ ልገባ እርሻ ላጠና ስላቸው አንቺ በቃ ይሄ ውንብድናሽ አሁንም አለቀቀሽ ብሎ ‘ገበሬ ለመሆን ዲግሪ ያስፈልግሻል?’ አለኝ” ስትል ታስታውሳለች።

በኋላ ግን ስለስራዋ እና ስኬቷ እየተረዱ ሲመጡ የኩራታቸው ምንጭ ሆነች።

ፈተና

ፈተና የሕይወታችን አንዱ ክፍል ነው ብላ የምታምነው ዶክተር ሰገነት ፈተናዎችን እንዴት እወጠቸዋለሁ ብሎ ማሰብ እንጂ ተስፋ መቁረጥን አስባው አታውቅም።

ደቡብ አሜሪካ ኮሎምቢያ ከፍተኛ ተመራማሪ ሆና ለአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት የምርምር ስራ ለመስራት በአለም ላይ ካሉ ተመራማሪዎች ጋር ተወዳድራ አለፈች።

በኮሎምቢያ ጥቁር ሳይንቲስት እርሷ ብቻ ነበረች፤ እናም ጎብኚዎች ሲያዩዋት የፅዳት ሰራተኛ ወይንም ሌላ ዝቅተኛ ስራ ላይ የተሰማራች ይመስላቸው ነበር። “ዶ/ር ቀለሙን እንፈልጋለን ይላሉ እና ግቡ ካልኳቸው እሷን ጥሪልን ይላሉ።”

ሌላው በኮሎምቢያ የምታስታውሰው ተቀጥራ እንደሄደች የተፈጠረውን ነው።

ስራ ስትጀምር 17 የቤተ-ሙከራው ሰዎች ነጮች ነበሩ። ትልቅ ብር ተመድቦ በርካታ ቁሳቁስ ተሟልቶ ነው ሃላፊነቱ የተሰጣት። ሴት፣ ጥቁር እንዲሁም ቀጫጫ መሆኗ ከተሰጣት ሃላፊነት ጋር ያልተዋጠለት አንድ ሰራተኛ ማስቸገር ጀመረ።

በዛ ላይ ስፓኒሽኛ አለመቻሏ ፈተናውን የበለጠ አከበደው። የሙከራ ጊዜ የተሰጣት ደግሞ ለስድስት ወር ነው።

በስድስት ወር ውስጥ መልክ መያዝ ያለበት ነገር መልክ ይዞ ውጤት ይጠበቃል።

በአንድ እለት በስሯ የነበሩ ሰራተኞችን ሰብስባ በፀሀፊዋ አማካኝነት እያስተረጎመች ስታወያያቸውና የስራ አመራር ስትሰጥ ዳተኛ የሆነ አንድ ባለሙያ ያልተገባ ነገር ተናገራት።

‘ባንሰራ ምን ታደርጊናለሽ?’ በማለት የሀገሪቱን የሰራተኛ ህግ እና የቀድሞ አለቃቸውን ጠቅሶ እንቢተኝነቱን አሳየ።

‘ከየት እንደመጣሽ እናውቃለን እኮ’ ብሎ የኢትዮጵያን ረሃብ አነሳ።

“እኔን አልፎ 80 ሚሊየን ሕዝብ ስለሰደበ ከስራ መባረሩን ነገርኩት።”

“ከዛም ድርጅቱ በርካታ ገንዘብ ከፍሎ አሰናበተው። የእርሱ መሰናበት በመስሪያ ቤቱ ባጠቃለይ ተሰማ። ሌሎች ስራቸውን ሰጥ ለጥ ብለው እንዲሰሩ ምክንያት ሆነ። ያኔ ያንን ጠንካራ ውሳኔ መወሰኔ እኔንም ውጤታማ አደረገኝ” ትላለች።

በእንዲህ አይነት ጉዳዮች ተበሳጭታ እንደማታውቅ የምትናገረው ዶክተር ሰገነት ዋናው የረዳት ነገር በማንነቷ መኩራትን ተምራ ማደጓ እንደሆነ ትገልፃለች።

“በትምህርት ቤትም በቤትም ቆንጆ ነን፤ ጎበዝ ነን፤ ማንም ሰው ሊያሸንፈን አይችልም፤ ቅኝ አልተገዛንም፤ የሚኒልክ ሰዎች ነን፤ እየተባልን መማራችን በማንነቴ እንድኮራ እና በትንንሽ ነገሮች እንዳልናወፅ ጠቅሞኛል።”

ይህ የኢትዮጵያ ረሃብ ጉዳይ በስራ ቦታ ብቻም ሳይሆን በመንገድ ላይም ገጥሟት ያውቃል።

ያኔ ግን ” ኢትዮጵያ ረሃብተኛዋ አገር ሳትሆን ቡናን ለአለም ያስተዋወቀችው ናት እላቸዋለሁ። ኮሎምቢያውያን በቡናቸው ስለሚኮሩ ዝም ይላሉ”

የትም ሃገር ብትሆን የስራን እና የቤተሰብ ሚዛንን መጠበቅ ለሴት ልጅ ከባድ ነው የምትለው ዶ/ር ሰገነት “ለእኔ ጥሩነቱ ጥሩ ባል አለኝ እሱም ሳይንቲስት ነው። የቤቱን ስራ አብረን ነው የምንሰራው። እንደውም ብዙውን ይሰራ ነበረው እሱ ነው” በማለት ስለትዳር አጋሯ ለስኬቷ ስለሚያደርገው አስተዋፅኦ ትመሰክራለች።

ጥናትና ምርምር

በአሁኑ ወቅት ነፍሳት ላይ የምርምር ስራዋን እያካሄደች የምትገኘዋ ዶ/ር ሰገነት በአለም ላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ የነፍሳት ዝርያ እንዳለ ታስረዳለች።

አብዛኞቹ ነፍሳት ሰራተኛ ናቸው የምትለው ዶ/ር ሰገነት እነዚህን ነፍሳት ተጠቅሞ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል እየሰራች ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሐር ትልን ለማስለመድ የምትሰራዋ ዶ/ር ሰገነት በምግብም ረገድ ነፍሳት አማራጭ እንደሚሆኑ ታስባለች።

በአፍሪካ፣ ኤስያ፣ ላቲን አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ ሁለት ሚሊዮን ህዝብ ነፍሳት እንደሚበላ፤ እንደ ጀርመን ያሉ ያደጉ ሀገራትም ለሕዝባቸው ይህንኑ ለማስለመድ እየሰሩ መሆኑን ትጠቁማለች።

አሁን የምትሰራበት መስሪያ ቤት ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል አንዱ ይህንን ማስተዋወቅ እና ምግብ ይዘቱንና ጥቅሙን መተንተን ነው። “የሚጎዱ እንዲሁም የሚጠቅሙ ነፍሳት አሉ። ሁለቱንም አመጣጥነን መኖር እንችላለን” ትላለች።

የዩኒቨርስቲ መምህርቷ ሞዴል፡ “ውበት ባመኑበት ነገር ጠንክሮ መሥራት ነው”

ሌላው የምርምር ስራዋ የሚያተኩረው የከብት መኖ ላይ ነው። ደቡብ አሜሪካ እያለች ትሰራ የነበረው እዚህ ላይ ነው። ይህ የምርምር ስራዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ገበሬዎችን ተጠቃሚ ማድረጉንም ትናገራለች።

“የበርካታ ገበሬ ሕይወት ተሻሽሏል። ከላሞቻቸው የሚያገኙት የወተት ምርት ጨምሯል ይህንንም በማየቴ ደስተኛ ነኝ” ትላለች።

ይህንን የከብት መኖ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሆኖ በአመት ለ20 ሺህ ገበሬ ለመድረስ እቅድ አላት።

በቀሪው ህይወቴ ገበሬውን መርዳት እፈልጋለሁ የምትለው ዶ/ር ሰገነት በመስሪያ ቤቷ ከአፍሪካ እና ከአፍሪካ ውጭ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመስራት የሚመጡትን ተመራማሪዎች ማገዝ ማሳደግ ትፈልጋለች።

የሕይወትሽ ደስታ

ለዶክተር ሰገነት ጊዜዋን ማሳለፍ የሚያስደስታት ከቤሰተቧ ጋር ነው። “ባለቤቴ አይሰራም አሁን ታሟል። … ደስ የሚለኝ እሱን መንከባከብ እና ልጄን ለስኬት ማብቃት ነው” ትላለች።

ሌላ ደስ የሚላት ጎበዝ የሆኑ እና ዕድል ያጡ ሰዎችን ዕድል ሰጥቶ ማብቃት ነው። የራሷን ህይወት መለስ ብላ በማስታወስና ባትማር ምን ልትሆን እንደምትችል በማጤን ግለሰቦችም ሆኑ መንግስት ትምህርት ላይ ማተኮር አለበት ትላለች።

በመጨረሻም ከተለያዩ አካላት ገንዘብ በማሰባሰብ የተወለደችበት አካባቢ የገበሬዎች ማሰልጠኛ ብትከፍትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ብትሰራ ምኞቷ ነው።