ካለስምምነት የተበተነው በህዳሴው ግድብ ላይ ያተኮረው ውይይት ነገ በአሜሪካ ይካሄዳል፡፡


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

በህዳሴው ግድብ ላይ ያተኮረው የሶስትዮሽ ውይይት ነገ በአሜሪካ ይካሄዳል፡፡ ለዚህም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ትናንት ወደ ዲሲ አምርቷል፡፡ያለ ስምምነት የተጠናቀቀውን ይህንኑ የቴክኒክ ውይይት በተመለከተ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአቋም መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም የዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በወንዙ የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን የማስከበር፣ እንዲሁም የመጪውን ትውልድ የመጠቀም መብት የማረጋገጥ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቋል፡፡

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳጋቸው ከዚህ ቀደም በተደረሰው ስምምነት መሰረት እኤአ ጃንዋሪ 13 ቀን 2020 የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዋሽንግተን ከተማ በሚያካሂዱት ውይይት ላይ ለመሳተፍ ጥር 2 ቀን 2012 ዓም ማምሻውን ወደ አሜሪካ አቅንተዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የታላቁ የህዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ በተመለከተ ሲያካሂዱት የቆየው የቴክኒክ ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ የሚሰጠው ትርጉም፣ ግብፅ ግድቡ ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም የሚል ካልሆነም ግድቡ በተገቢ ዓመታት ውስጥ በውኃ እንዳይሞላ ፍላጎት እንዳላት ነው ሲሉ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ሲካሄዱ በቆዩት የቴክኒክ ውይይቶች ያልተነካና ያልተመነዘረ የቴክኒክ ችግር እንዳልነበረ፣ በዚህም በሦስቱም ወገኖች በተለይም በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የነበረው የቴክኒክ ልዩነት በጣም ከመጥበቡ የተነሳ ለመስማማት የሚያስችል ደረጃ ላይ ተደርሶ እንደነበር አስረድተዋል። ነገር ግን ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቻሉንና በግብፅ ወገን ውሳኔ ለመስጠት የሚችለው አካል በዚህ ድርድር ውስጥ አለመኖሩን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

‹‹በዚህ መንገድ መስማማት ካልተቻለ ግድቡ ለኢትዮጵያ አያስፈልጋትም የሚል አመለካከት ግብፆች እንዳላቸው ነው ለእኛ የሚገባን፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ግድቡ በተገቢዎቹ ዓመታት ውስጥ እንዳይሞላ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን በቴክኒክ ድርድሩ ስምምነት የተደረሰባቸውንና ልዩነት የታየባቸውን ጉዳዮች በመለየት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት እንደሚያቀርብ፣ የሦስቱ አገሮች መሪዎች የበኩላቸውን ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚሰጡበት እምነታቸው መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይና የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንትና የአሜሪካ ትሬዥሪ ኃላፊ እስካሁን በነበረው የቴክኒክ ውይይትና ምክክር ውጤት ላይ በአሜሪካ እንደሚወያዩም ገልጸዋል።

ያለ ስምምነት የተጠናቀቀውን ይህንኑ የቴክኒክ ውይይት በተመለከተ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአቋም መግለጫ ኢትዮጵያ በናይል (ዓባይ) ወንዝ ላይ ለተፈረሙና አባል ላልሆነችባቸው የቅኝ ግዛትና ድኅረ ቅኝ ግዛት ኢፍትሐዊና አግላይ፣ እንዲሁም ለናይል ወንዝ 77 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለምታበረክተው ኢትዮጵያ ዜሮ ድርሻ ለሚሰጡ ‹‹ውሎች›› ዕውቅና እንድትሰጥ የሚደረጉ ሙከራዎችን እንደማትቀበል አስታውቋል፡፡

ነገር ግን ከተፋሰሱ አገሮች ጋር በሚደረግ ውይይት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትብብርና የጋራ ልማት ምሳሌ እንዲሆን በወንድማማችነት፣ በቅን ልቦናና በመተባበር መንፈስ ለመሥራት ኢትዮጵያ ጥረቷን እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አክሏል፡፡

ምንጭ ፦የተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች (Govt Media and Reporter) የተሰበሰበ