የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከትምህርት ማገዱን አስታወቀ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሰባ ሰባት ተማሪዎችን ከትምህርት ማገዱን አስታወቀ

የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ዛሬ ባካሄደው ጉባዔ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዳይኖር በተደራጀ ሁኔታ ተማሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ፣ በቡድን ተደራጅተው በማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት የማድረስ የማስፈራራት እና የማሸማቀቅ ተግባር ሲፈፅሙ የተደረሰባቸው እንዲሁም የብሔር ግጭት የሚቀሰቅሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ንግግሮችን በማጉላት በተማሪዎች መካከል ስጋት እንዲፈጠር በአጠቃላይ በተቋሙ ህገ ወጥ የሆኑ ተግባራትን በማከናወን ተሳትፈዋል የተባሉ ሁለት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት መታገዳቸውን አስታውቋል።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በተጨማሪ 75 የሚሆኑ ተማሪዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት እንዲታገዱ ውሳኔ ማሳለፉም ተገልፃል። በተጨማሪም ሁለት መምህራን ተማሪዎችን በማስኮብለል ድርጊት ላይ ተሳትፈው በመገኘታቸው የደሞዝ ቅጣትና የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደረሳቸው መደረጉን አስታውቋል።

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች በሚነሳ ግጭት ሳቢያ ለወራት ሲስተጓጎል ከቆየው መደበኛ ትምህርት ባሻገር በትናንትናው እለት በቴክኖሎጂ ካምፓስ አካባቢ ኹከት ተከስቷል ፤ ይህንኑ ተከትሎ የኹከቱ ተሳታፊ ተማሪዎች እሳት መለኮሳቸውን እና በስፍራው ቆመው የነበሩ ሁለት ሞተር ሳይክሎች መቃጠላቸውን ፣ አንድ የዩኒቨርሲቲው ተሽከርካሪ መስታወት መሰባበሩን እንዲሁም የንግድ ባንክ ንብረት የሆነ የገንዘብ መክፈያ (ATM) ማሽን መሰባበሩን ተገልፃል፡፡

በአካባቢው የነበሩ የዩኒቨርሲቲው ፀጥታ ኃይሎች ድርጊቱን መከላከላቸውንና ተሳታፊ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ታውቋል። በዩኒቨርሲቲው ሰላምን ከማደፍረስ ጋር በተያያዘ በማኔጅመንቱ ከተወሰደው እርምጃ የዲሲፕሊን እርምጃ በተጨማሪ የወንጀል ድርጊት የፈፀሙ ተማሪዎች በህግ እንደሚጠየቁ ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል፡፡