“ዉሻዉ አብዮታዊ መስመር ይዟል! በግ መሆኑንም አምኗል” – (ታዬ ደንደዓ)

“ዉሻዉ አብዮታዊ መስመር ይዟል!
በግ መሆኑንም አምኗል” – (ታዬ ደንደዓ)

መቸም ቀን ሄዶ ቀን ይመጣል። የህዳር 21/2012 እሁድም ታሪካዊ ቀን ሆኖ አልፏል። የህወሀት ነገር ደግሞ ሁሌ ይገርማል። አንዳንዴ ፕሮፓጋንዳዉ ተፈጥሮን እስከ መቀየር ይደርሳል። ከሁሉ በላይ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲደሰኩር የነበረዉን ጉዳይ መልሶ ይክዳል። ከአስር ዓመታት በፊት ጀምሮ በየጉባኤዉ ” የኢህአዴግ መዋሀድ እና የአጋሮች መደመር ከልክ በላይ ዘግይቷል” ብሎ ሲናዘዝ ከራርሟል። ዛሬ ደግሞ “ዉህደቱ ከብርሃን ጉዞ በላይ ፈጥኗል” ሲል ይሰማል። ይህ በምን ሎጂክ ሊሆን ይችላል? ለነገሩ ህወሀት ቤት ሎጂክ መች ይሰራል? ከፈለገ ዉሻን አሳምኖ “በግ ነኝ” እንዲል ያደርጋል። ሰዉ ገሎ ከቀበረ በኋላም ይፈልጋል!


በቃሊቲ እስረኞች አንድ ቀልድ ነበራቸዉ። ቀልዱ አብዮታዊ ታጋዮችን ይመለከታል። በ1980ዎቹ አጋማሽ አንድ ታጋይ በግ ለመግዛት ከካምፕ ወደ ገበያ ይሄዳል። መንገድ ላይ ወፈር ያለ ዉሻን ያገኛል። ወዲያዉ ተኩሶ ይገልና ተሸክሞ ወደ ካምፑ ይመለሳል። ጓዶቹ ሲያዩት ገረማቸዉና “ያመጣሄዉ በግ ዉሻ ይመስላል” ይሉታል። እሱም ዘና ብሎ ” አዎ መጀመሪያ በግ ነበር። አሁን ግን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተጠምቆ በግ መሆኑን አምኗል” ሲል ይመልሳል። እነሱም ታጋዩን አምነዉ ህደቱ ቀጠለ ይባላል። የዉህደቱ መዘግየትና መፍጠንም በዚያዉ ይለካል።


ከምንም በላይ ህወሀት መደመርን ይጠላል። ምክንያቱም መደመር የኢትዮጵያዊያንን እዉቀት፣ ገንዘብ እና ልምድ አሰባስቦ ወደ አቅም ይለዉጣል። ይህ ደግሞ ለህወሀት ህልዉና ከፍተኛ አደጋ ይፈጥራል። የህይወቱ ምሰሶ ክፍፍል መሆኑን ሁሉም ይገነዘባል። የመንኮታኮቱ ምክንያትም “እሳትና ጭድ” ሳይታሰብ በድንገት መደመራቸዉ እንደሆነ ጌች አንድ ወቅት ተናግሯል። የቀድሞ ጓዳችን ህኸሀት በብሔር፣ በሀይማኖት፣ በአከባቢ እና በተገኘዉ ቀዳዳ ሁሉ ኢትዮጵያውያንን ከፋፍሎ እያጋጬና እያጋዳደለ በህዝብና በሀገር ኪሳራ እያተረፈ ኖሯል። ዘና ብሎ ውስኪ ሲጠጣ ድንገት “መደመር” ሲመጣበት እንዴት ትላንት ያለዉን ሊያስታዉስ ይችልላ? ደግሞ በእርጅና ምክንያት መርሳትም ይኖራል።


በሌላ በኩል “ሆድ ሲያዉቅ ዶሮ ማታ” ይበላል። ህወሀት ሁሌም ብልጣብልጥ ሆኖ ለማታለል ይሞክራል። “አሁን ሀገር በአንገብጋቢ ችግሮች ስለተያዘች ውህደቱ ከምርጫዉ በኋላ ይሁን” ይላል። ራሱ በተማሪዎች፣ በብሔሮች እና በሀይማኖቶች መሀከል እሳት ለኩሶ “መጀመሪያ ስለሰላም እናዉራ” ሲል ይጠይቃል። ለመሆኑ ችግሩን በፈጠረዉ ከፋፋይ እሳቤና አወቃቀር ችግሩን መፍታት እንዴት ይቻላል? በህዝቡ ዘንድ የተጠላ ፕሮግራም፣ ስምና ምልክት ተይዞስ እንዴት ምርጫ ይታሰባል? ስሌቱ ይገባናል። ውህደቱ በዘገየ እና ቀዉሱ በቀጠለ ቁጥር ህዝቡ ከለውጥ ሀይሉ ተስፋ ይቆርጣል። በሰላም ወጥቶ መግባት ሲያቅተዉ ያለፈዉን ስርዓት ይናፍቃል። ያኔ ህወሀት አፈር ልሶ በመነሳት ወደ መንበሩ ይመለሳል። ይህም ዘመናዊ የፐለቲካ ዘዴ ይባላል።


ብልፅግና ፓርቲ እንዳይወለድ ህወሀት ብዙ ለፍቷል። “አሀዳዊ ስርዓት እየመጣ ነዉ” በማለት አሰልቺ ፕሮፓጋንዳ ነዝቷል። ጥቂቶችን ቀጥሮ ብዙዎችን አደናግሯል። ሰላም ለማደፍረስ ገንዘብ መድቦ ግጭት በመቀስቀስ ህይወት እና ንብረት እንዲጠፋ አድርጓል። ቅጥረኞች እና አላዋቂዎችም በወጥመዱ ተጠልፈዉ በሰፊዉ አግዘዉታል። ሆኗም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምናባዊ ጉልበት አሁን ላይ ክፉኛ ተዳክሟል።

ዉሻን አሳምኖ ወደ በግ ሲቀይር የነበረዉ “ጠንካራ” ሎጂኩ ዛሬ ስለራሱም በትክክል መናገር ተስኖታል። እንግድህ ጊዜዉ ነዉ! በመጨረሻም እሳቤዉ ተሸንፎ ጥብቆዉ ተቀዷል! አሁን መደመርን መርሁ አድርጎ በእዉነት እና በእዉቀት ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማማ ለመዉሰድ እነሆ ብልፅግና ፓርቲ ተወልዷል። “እንኳን በሰላም መጣህ! መልካም ልደት! እደግ ተመንደግ! ለሀገር መከታ ሁን!” ብለናል። ያሉንን መልካም እሴቶች አጎልብተን፣ ስህተቶቻችንን አርመን፣ ህብረብሔራዊ አንድነታችንን አጠናክረን በነፃነት፣ በእኩልነት እና በወንድማማችነት መንፈስ የበለፀገች እና የተከበረች ኢትዮጵያን እንገነባለን! አሜን!

አሁን አብዮታዊ ጭምብል ወልቋል!
በግዴታ ማመን ቀርቷል!
የሀሳብ ነፃነት ሰፍኗል!
እዉነትም እዉነት ሆኗል!