" /> የዋጋ ንረት አዙሪት እየበረታ የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

የዋጋ ንረት አዙሪት እየበረታ የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው

ባለፉት ጥቂት ወራት የሸቀጦች የዋጋ ንረት እና አጠቃላይ የኑሮ ዋጋ መወደድ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ የብዙሃን መገናኛዎች ተደጋግመው የሚወሱ ጉዳዮች ሆነዋል።

የመንግሥት ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶችም የችግሩን አሳሳቢነት ከመቀበል በዘለለ እየተወሰዱ ናቸው የሚሏቸውን እርምጃዎች ሲናገሩ ተስተውለዋል።

ብር የሚቆጥር ሰው

በወርሃ ግንቦት 2011 ዓ.ም መገባደጃ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ በመዲናዋ በግንባታ ዕቃዎች፣ በእህል፣ በጥራጥሬ እና በአትክልት ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪዎች መከሰታቸውን ጠቅሰዋል።

እንደመፍትሄም ችግሩን አባብሰዋል ያሏቸው ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር ማምጣት፣ ፈቃደኛ ያልሆኑት ላይ ደግሞ ይህንን የሚከታተል ግብረ ኃይል በማቋቋም እርምጃ መውሰድ፣ እንዲሁም ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የአቀርቦት ሥርዓቱን ማሰተካከል የከተማዋ አስተዳደር የሚያከናውናቸው ተግባራት መሆናቸውን ገልፀው ነበር።

ይሁንና ክረምቱ ሲገባ የዋጋ ንረቱ ከመርገብ ይልቅ ከፍ ብሎ ታይቶ የዋጋ ግሽበቱ ባለሁለት አሀዝ ሆኗል። በወርሃ ነሐሴ እንዲያውም ባለፉት ስድስት ዓመታት ከታየው የዋጋ ግሽበት መጠን ከፍተኛው ተመዝግቧል።

የሸቀጦች የዋጋ ንረት ህይወታቸው ላይ ቀጥተኛ ጫና ካሳረፈባቸው የአዲስ አበባ ኗሪዎች መካከል ደገሞ የአርባ ዓመቱ ጎልማሳ ጋሹ መርከቡ አንዱ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚኖረው ጋሹ ላለፉት ከአስራ ለሚልቁ ዓመታት በሚኒባስ ታክሲ ሾፌርነት ቤተሰቡን ሲያስተዳድር ኖሯል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን “የኑሮ መወደድ ከአቅሜ በላይ ሆኖ እያንገዳደገደኝ ነው” ይላል።

“በዋጋ ላይ ያለውን ለውጥ ከቀን ወደ ቀን እያየሁት የመጣሁት ጉዳይ ነው፤ በእኔ [ህይወት] አንኳ ታክሲ ሠርቼ ብሩን ይዤ ብገባም ምንም የሚገዛው ነገር የለም” ይላል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ። “የልጆች ትምህርት ቤት፣ የእህሉ ውድነት፣ እንዲያውም ተስፋ ወደማስቆረጥ ደረጃ እየደረሰ ያለ ይመስለኛል” ይላል።

ውን ፍራቻ

ጋሹ የአራት ልጆች አባት ሲሆን ትልቋ የአስራ ሁለት ዓመት ልጁ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ሌሎቹ ሦሰት ልጆቹም በመዋዕለ ሕፃናት እና በአንደኛ ደረጃ ትምርት ቤቶች ውስጥ ይማራሉ።

ባለፉት ዓመታት ሁሉንም ልጆቹን በግል ትምህርት ቤቶች ያስተምር የነበረ ሲሆን አሁን ግን በኑሮ ውድነት ላይ በየጊዜው የሚጨምረውን የትምህርት ቤት ክፍያን መቋቋም ባለመቻሉ አንደኛውን ልጁን የመንግሥት ትምህርት ቤት፣ ሁለቱን ደግሞ በለጋሽ ድርጅቶች በሚደጎም እና በዚህም ምክንያት በአንፃራዊነት አነስተኛ ከፍያ ወደሚጠይቅ ትምህርት ቤት አስገብቷል። ለእያንዳንዳቸው በየወሩ ሦስት መቶ ብር በመደበኛት ይከፍላል።

አንደኛዋን ልጁን ብቻ በግል ትምህርት ቤት መማሯን እንድትቀጥል አድርጓል።

ለብቸኛዋ የግል ትምህርት ቤት ተማሪ ልጁ መደበኛ ክፍያ ብቻ በዓመት ከአስር ሺህ ብር በላይ ያወጣል።

ይህም የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ፣ የአልባሳት፣ የምግብ ወጪዎች ሲደመሩበት “ናላን የሚያዞር” ሆኗል ይላል ጋሹ። በዚህ ላይ የቤት ኪራይ ወጪ ይታከልበታል። “ህይወታችንን ለማቆየት እየሰራን ነው እንጅ እየኖርን ነው ብዬ አላወራውም።”

አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ መጪውን ጊዜ ይበልጥ እንዲፈራው እንዳደረገው ይናገራል ጋሹ፤ “ወደፊት እንዴት እንደማስተምራቸው ራሱ ግራ ገብት እያለኝ ነው” በማለት።

ተስፋው ከዕለት ወደ ዕለት እንዲሟጠጥ አንድ ምክንያት የሆነው እርሱን ለመሰሉ ከኑሮ ጋር እልህ አስጨራሽ ግብግብ ለገጠሙ ሰዎች በፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ብዙም ትኩረት እየተሰጠ አይደለም ብሎ ማመኑ ነው።

የፖለቲካ ልሂቃኑ “በብሔርም ጉዳይ፣ በምንም ጉዳይ የራሳቸውን ለማመቻቸት እንጂ የድሃውን [ጉዳይ] አንስቶ ልብህን [የሚነካ] ነገር ሲናገሩ እኔ እስካሁን ሰምቼም አላውቅም። የራሳቸውን ጉዳይ ከማስፈፀም በስተቀር ውስጥህን የሚነካ ነገር፣ ስለኑሮህ፣ ስለሽንኩርት የሚያወራ የለም” ይላል።

ከጋሹ አስተያየት ጋር በሚስማማ መልኩ አጠቃላይ ምርጫ በሚከናወንበት ዓመት በፖለቲካዊ መድረኮች ላይ የዋጋ ንረት የሚገባውን ያህል ስፍራ ይዞ ያለመታየቱ እንደሚገርማቸው የሚያስረዱት የምጣኔ ሃብት የፖሊሲ ተንታኝ የሆኑት አሚን አብደላ ናቸው።

“ምርጫ ኖረም አልኖረም፤ የማንኛውም አገር መንግሥት ፈተና የሚሆኑ ሁለት የማክሮኤኮኖሚ አመላካቾች አሉ፤ የሥራ አጥነት እና የዋጋ ንረት።”

በፖለቲካው መልክዐ ምድር ገኖ ያለው መንግሥታዊው ሥርዓት “የፌዴራል ይሁን አይሁን የሚል ዓይነት እንጅ የሥራ አጥነት እና የዋጋ ንረት ላይ ብዙም የፖለቲካ ልሂቃን ሲጨቃጨቁ አይቼ አላውቅም” ባይ ናቸው ተንታኙ።

ለአንድ አገር መረጋጋት እና የምጣኔ ሃብት ዕድገት ወሳኝ ናቸው የሚሏቸው እነዚህ ጉዳዮች ብዙም ያለመነሳታቸው “ዋናው ነገር የተዘነጋ ይመስለኛል” አስብሏቸዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ውሰጥ የሚታዩ ሰዎችና የምግብ ምርቶች
በምግብ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ መጨመር

የምርት-አቅርቦት ሰንሰለት ችግር

የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ተንታኙ አሚን አብደላ እንደሚሉት አጠቃላይ የዋጋ ንረት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ ይላሉ።

በተሰናበተው 2011 ዓ.ም የሐምሌ ወር የዋጋ ግሽበቱ ከ15 በመቶ በላይ ደርሶ እንደነበረ የሚያስታውሱት አሚን በወርሃ ነሐሴ ደግሞ ይህ ቁጥር ወደ 18 በመቶ ከፍ ብሎ እንደነበርም ይጠቅሳሉ።

ይህም ቁጥር በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የታየው ትልቁ አሃዝ ነው።

ለቁጥሩ ከፍ ማለት የምግብ ዋጋ፣ በተለይም የእህል ሰብል ዋጋ ንረት ምክንያት መሆኑን የስታትስቲክስ መረጃዎች ያመላክታሉ።

በዚህ ረገድ በአንዳንድ ትርፍ አምራች በሆኑ አካባቢዎች የነበረው የፀጥታ ሁኔታ፣ የመጓጓዣ አገልግሎት እንደልብ ያለመገኘት እና ከዚህም ጋር በተያያዘ ምርትን በተፈለገው ደረጃ ማቅረብ ያለመቻል ለችግሩ ምክንያት ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ተንታኙ አሚን ያነሳሉ።

እየናረ ያለውን የዋጋ ንረት ለማቃለል ሁለት የመፍትሄ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ የሚሉት ባለሙያው፤ “አንደኛው በአቅርቦት በኩል ሌላኛው ደግሞ በፍላጎት በኩል ያሉ ናቸው” እንደአሚን ገለፃ።

“ከፍላጎት አንፃር የመንግሥት ወጪ የቀነሰበት ሁኔታ አለ። ያለፉትን ዓመታት ዓይነት እድገት ስለሌለ፤ ምጣኔ ሃብቱ ውስጥ የሚለቀቀው የገንዘብ መጠን ቀነስ ያለ ይመስላል። ይሁንና በአቅርቦት በኩል እምብዛም ለውጥ ያለ አይመስልም” ሲሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል አቶ አሚን።

የምርቶች በተገቢው መጠን አለመገኘት ለዋጋ መወደድ በአንዳንድ ሰዎች እንደምክንያት ተደጋግሞ የሚነሳ ሲሆን፤ ባለሙያውም በምርት እና በአቅርቦት መካከል ያለው ሰንሰለት ችግር እንደሚስተዋልበት ይናገራሉ።

“ገበሬው አምርቶ ለምርቱ የሚያገኘው ዋጋ እና ከተማ ላይ መጥቶ የሚሸጥበት ዋጋ በጣም ከፍተኛ ልዩነት አለው። ገበሬው ከአንድ ኪሎ ሙዝ እያገኘ ያለው ገቢ እና አንድ ኪሎ ሙዝ ከተማ ውስጥ እየተሽጠበት ያለው ዋጋ ልዩነት አለው።

“በዚህ መካከል ያለው የአገልግሎት፣ የደላላ፣ የመጓጓዣ፣ የቦታ ኪራይ እና የመሳሰሉት ወጪዎች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወሰዱ ናቸው። ይህ የገበያ ሰንሰለት ሥርዓት እሰካልያዘ ድረስ፤ የምርቶች ዋጋ ከፍ እንዲል ማድረጉ አይቀሬ ነው” ለአሚን።

ከውጭ የሚመጣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የንግድ ውድድርን ማሳለጥ እንዲሁም የሸማቾችን ጥበቃ ማጠናከር ይገባል የሚሉት ባለሞያው፤ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን የሚያስመጡ ተቋማት እና ግለሰቦች በየተሰማሩበት ዘርፍ ጥቂት መሆናቸው ዋጋው ላይ ከሚገባው በላይ ጫና እንዲፈጠር መንገዱን ይጠርጋል ባይ ናቸው አቶ አሚን።

ከውጭ የሚመጣ የዋጋ ንረት በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምከንያትም ሊከሰት ቢችልም በእኛ አገር እየተስተዋለ ያለው እውነታ ግን በውጭ ምንዛሬው እጥረት መጠን ያህል መኖር ከሚገባው በላይ ጭማሪ ነው፤ ሲሉ የዋጋው ጭማሪ አሳሳቢ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ባለሞያው አቶ አሚን አብደላ ለፖለቲካዊ ጉዳዮች እየተሰጠ ካለው ጋር የሚመጣጠን አትኩሮት የዋጋ ንረትን ለመሳሰሉ ምጣኔ ሃብታዊ ተግዳሮቶች መቸር አለበት ባይ ናቸው።

በዚህ አስተያየታቸው ጋሹም የሚስማማ ይመስላል፤ “ይሄ ሁሉ እየታየ ቸል የሚባለው እስከመቼ እንደሆነ አይገባኝም።”


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV