ፕ/ር መረራ፣ ዶ/ር ደሳለኝ፣ አቶ የሺዋስ፣ ፕ/ር በየነ፣ አቶ አንዶምና አቶ ቶሌራ ስለመጭው ምርጫ ይናገራሉ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


BBC Amharic : በዚህ ዓመት ለማካሄድ የታቀደው አጠቃላይ ምርጫ ስምንት ወራት ያህል ነው የቀሩት። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ ምርጫው እንደሚካሄድ በተደጋጋሚ ቢያረጋግጡም፤ በዚህ ወቅት ግን ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ፓርቲዎች በውድድሩ እንደሚሳተፍ ወገን የሚያደርጉት የጎላ እንቅስቃሴ አይስተዋልም። ምን እየጠበቁ ይሆን?

ፕ/ር መረራ፣ ዶ/ር ደሳለኝ፣ አቶ የሺዋስ፣ ፕ/ር በየነ፣ አቶ አንዶምና አቶ ቶሌራ

ምርጫውን ከማካሄድ የተሻለ አማራጭ ያለ አይመስለኝም” ፕ/ር መረራ ጉዲና

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና አገሪቱ ባልተረጋጋችበት ሁኔታ ምርጫ መካሄድ የለበትም የሚሉ ሰዎችን መረዳት ይከብደኛል ይላሉ።

እንዲያውም አገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ በመሆኗ ምንም ዓይነት ይሁን ምን ምርጫ አካሂዶ ወደ ህዝብ መቅረብ እንደሚያስፈልግ ያምናሉ።

አገሪቷን ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ውስጥ የከተተው ኢህአዴግ ራሱ ሆኖ እያለ ይሄንኑ ኢህአዴግ ለምርጫ ሁኔታዎችን ያመቻች ብሎ መጠበቅ ቀልድ ነው ይላሉ።

“ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆነም አልሆነ፣ በፈለግነው መንገድ ሄደ አልሄደም ምርጫውን ከማካሄድ የተሻለ አማራጭ ያለ አይመስለኝም” ሲሉም ይደመድማሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ኢህአዴግ መሄድ እንዳለበት እየሄደ አይደለም፤ ሰላምና መረጋጋትም እንደሚጠበቀው እየመጣ ባለመሆኑ ምርጫውን አካሄዶ ወደ አንድ አቅጣጫ መሄድ አስፈላጊ ነው።

የምርጫ መዋቅሩንም በፍጥነት መዘርጋት ይቻላል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። በተቃራኒው ይህ ካልሆነ ምርጫ መካሄድ የለበት ወይም ወደ ምርጫ አንገባም ማለት አገሪቱን የከፋ ነገር ውስጥ ይከታታል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይገልፃሉ።

ነገሮች ካልተስተካከሉ ወደ ምርጫ በመግባት ምን ይገኛል?

“ምርጫውን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ወደ ሆነ ነገር መውሰድ ይሻላል። ከሁለት መጥፎ አማራጮች ህዝቡን ይዞ ወደ ምርጫ፣ ሰላምና መረጋጋት መግባቱ ይመረጣል” የሚል መልስ የሰጡት ፕ/ር መረራ ሌሎች ጥያቄዎች እንዳላቸው ይጠቅሳሉ።

ከእነዚህም መካከል በአዲሱ የምርጫ ህግ መሰረት እንደ አዲስ አስር ሺህ የአባላት ፊርማ ሰብስቡ መባላቸውን በመቃወም ለምርጫ ቦርድ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

ለዚህም አባሎች ስለሌሏቸው ሳይሆን የአስር ሺህ ሰዎች ፊርማ ማሰባሰብ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ሊጠይቃቸው እንደሚችል በማንሳት “ተወዳዳሪዎች አንድ ሺህ፣ ሁለት ሺህ ፊርማ ይሰብሰቡ የሚለውን እኮ ከነመለስና በረከት ጋር ሰፊ ድርድር አድርገን እንዲነሳ አድርገናል። ለምን መልሰው እንደሚያመጡብን አላውቅም” ይላሉ።

የመንግሥት ሰራተኞች በምርጫ የሚወዳደሩ ከሆነ ስራ ይለቃሉ የሚለው የአዋጁን አንቀፅ ደግሞ “እጅግ ነውር ነው” ሲሉ ይገልፁታል።

“ምርጫ ቦርድን እስከ መክሰስ ልንሄድ እንችላለን” ፕ/ርበየነ ጴጥሮስ

የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሆኑት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ምርጫው በ2012 ዓ.ም ቢካሄድ የጊዜ ጥያቄ እንደሌለባቸው ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ይልቁንም ለእነሱ ትልቁ ችግር የፖለቲካ ሜዳው ለምርጫ ውድድር የተመቻቸ አለመሆኑ ነው።

“በተጨባጭ እንደምናውቀው አምስት የምርጫ ቦርድ አባላት ከመሾማቸው በስተቀር ህዝብ ድምፅ እስከሚሰጥባቸው የታችኞቹ ማዕከሎች ድረስ ያለው የምርጫ ቦርድ መዋቅር ያው የድሮው ኢህአዴጋዊ ነው” ይላሉ።

“ምርጫ የሚያስፈጽመው እኮ ከአዲስ አበባው ወደታች የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ የምርጫ ጣቢያ እየተባለ በመቶ ሺህዎች የሚመለመሉ ምርጫ አስፈፃሚዎች እስካሁንም የኢህአዴግ ካድሬዎች ናቸው። እዚህ [አዲስ አበባ ላይ] ጎፈሬ ቢያበጥሩ የሚመጣ ለውጥ የለም” ይላሉ።

ፕ/ር በየነ ለዚህ ድምዳሜያቸው እንደማስረጃ የሚጠቅሱት የተሳተፉባቸውን ያለፉት አምስት ምርጫዎችን ነው።

“መሬት ላይ ያለውን እውነት እናውቀዋለን። ምን ማስረጃ ያስፈልገዋል” በማለት ከጥቂት ቀናት በፊት ግን ለክልል ምርጫ አስፈፃሚ የሚሆኑ ሰዎችን ጠቁሙ የሚል ደብዳቤ እንደደረሳቸው ይናገራሉ። “ምናልባትም ይህ አንድ አዎንታዊ እርምጃ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

ስለዚህም እሳቸው ችግር የሚሏቸውን ነገሮች ለማስተካከል መንግሥት ከተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ባለድርሻዎች ጋር ካልሰራ ስለ ምርጫ ማሰብ የዋህነት ነው ሲሉ ይደመድማሉ።

እንደ ችግር የሚያነሱት ሌላው ነገር ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ያፀደቀው አዲሱ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የሥነ ምግባር አዋጅን ነው።

“ከዚህ በፊት ከእነ አቶ መለስና አቶ በረከት ጋር ተደራድረን ያመጣነውን፤ ምርጫ ውስጥ ገብቶ መሳተፍ ቀላል እንዲሆን ማድረግን በተመለከተ ይህኛው ለውጥ አመጣሁ የሚለው አካል ወደ ኋላ መልሶታል” ሲሉ ፕ/ር መረራ ያሉትን ያጠናክራሉ።

ፓርቲዎች እገሌ እገሌ የእኔ ተወዳዳሪ ነው ብለው እጩዎቻቸውን ያቀረቡበትን የ1997 ዓ.ም ምርጫን በማስታወስ፤ አዲሱ ህግ አንድ ተወዳዳሪ እጩ ለመሆን ቢያንስ ሁለት ሺህ ፊርማ ያሰባስብ ማለቱን ይኮንናሉ ፕ/ር በየነ።

“የድሮው አንድ ሺህ ፊርማ ይል ነበር አሁን ሁለት ሺህ አድርገው መልሰውታል።”

በአዲሱ አዋጅ መሰረት ባለፉት ሁለት አስርታት በምርጫ ውስጥ የተሳተፈ እንደእሳቸው አይነት ፓርቲ “እንደ አዲስ አስር ሺህ የአባል ፊርማ እንዲሰበስብ መጠየቁ ትክክል አደለም” በማለት ምርጫ ቦርድን እየጠየቁ መሆኑን ገልፀዋል።

“ይህ እስከ ፍርድ ቤትም ሊወስደን፤ ምርጫ ቦርድን ልንከስ እንችላለን። ጠበቃም እያነጋገርን ነው”ይላሉ።

ምርጫ ቦርድን መክሰስ አዋጪ መንገድ ይሆናል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ፕ/ር በየነ “የበፊቱ ሥርዓት ተሻሽሏል፤ አዲስ አሰራር ነው ያለው ይሉ የለ?” በማለት እርምጃው ለውጡን ለመፈተሽም እንደሚጠቅም ይገልጻሉ።

ፓርቲዎች አስር ሺህ ፊርማ አሰባስበው ይመዝገቡ ማለት ጊዜ የሚጠይቅና ፓርቲዎች ላይ የገንዘብ ጫና የሚፈጥር እንደሆነም ያስረዳሉ።

“በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል አብን እንደሽብርተኛ እየተቆጠረ ነው” ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ በገቧቸው የለውጥ ቃሎች ተስፋን ሰንቀው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ ሜዳው ላይ በሚመለከቷቸው ነገሮች ቀጣዩ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ይሆናል የሚል እምነታቸው መሸርሸሩን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ይናገራሉ።

“ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙ ጥፋቶችን አልፏል” የሚሉት ዶ/ር ደሳለኝ በተለይም ከሰኔ 15ቱ ሁኔታ በኋላ የፖለቲካ ምህዳሩ እየጠበበና እየተዘጋ ነው ይላሉ።

በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ክልሎች መንቀሳቀስ አዳጋች እየሆነባቸው መሆኑን በመጥቀስ “አብን በኦዲፒና ቤጉዴፓ የዞን አስተዳዳሪዎችና በወረዳ ካድሬዎች እንደ ሽብርተኛ ፓርቲ እየታየ ነው” ሲሉም የገጠማቸውን ይናገራሉ።

“ወለንጪቲ ቦሰት የሚባል ወረዳ ከሁለት ወር በፊት የፓርቲው ጽ/ቤት በጥይት ተደብድቧል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከአምስት መቶ በላይ የሚደርሱ አባላት፣ በተለያየ ደረጃ ያሉ አመራሮችና ደጋፊዎቻችን ኦሮሚያ ላይ ታስረው ነበር” ብለዋል።

ጉዳዩንም በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስቴርና ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እንዲሁም ለምርጫ ቦርድ ጭምር ሪፖርት ማድረጋቸውንም ይናግራሉ ዶ/ር ደሳለኝ ።

በችግሩ ላይ ለመወያየትና መፍትሄ ለመፈልግ የኦዲፒ የፓርቲ ጉዳይ ሃላፊ አቶ አለሙ ስሜን አናግረው እንደነበር፤ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ለማነጋገር ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራም አለመሳካቱን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ቀላል ከሚባሉ አጋጣሚዎች በስተቀር ያለችግር በነፃነት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ከዚህ ባሻገር ግን እስርና አፈና ትልቅ እንቅፋት እንደሆነባቸው፤ የፓርቲያቸው ሕዝብ ግንኙነት እንዲሁም የጽህፈት ቤት ሃላፊና የሌሎችም እስር ለዚህ ምስክር መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በቀጣይ ምርጫ እየቀረበና ሰፊ የቅስቀሳ ሥራዎችን መስራት ሲጀምሩ ደግሞ የመንግሥት እጅ ይበልጥ ይከብድብናል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ይገልፃሉ።

አዲሱን የምርጫ አዋጅ በሚመለከት በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ አንደ ፓርቲ አስር ሺህ፤ በተወዳዳሪ ሁለት ሺህ ፊርማ ማሰባሰብን እንደ ችግር የሚያዩ ፓርቲዎች ቢኖሩም አብን በዚህ ረገድ ምንም ችግር እንደሌለበት ዶ/ር ደሳለኝ ያስረግጣሉ።

ዶ/ር ደሳለኝ የሚያስፈልገው የፊርማ ቁጥር ላይ ባይሆንም እዚሁ ጉዳይ ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ግን አለ።

“በፓርቲዎችና በአርቃቂ ቡድኑ መካከል ስምምነት ተደርሶበት የነበረው ቁጥር አራት ሺህ የሚል ሆኖ ሳለ ማን እንደቀየረው አይታወቅም” የሚሉት ዶ/ር ደሳለኝ ረቂቁ መጨረሻ ላይ ለፓርቲዎች ውይይት አስር ሺህ ሆኖ መምጣቱን ያስታውሳሉ።

በተጨማሪም የመንግሥት ሰራተኞች ለምርጫ እጩ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ሥራቸውን መልቀቅ አለባቸው የሚለውን የአዋጁን አንቀጽ አብን ይቃወመዋል።

ገዢው ፓርቲ በምርጫው ጊዜ ሊያሳይ የሚችለው ባሕሪ ላይ ስጋት ያላቸው ዶ/ር ደሳለኝ “ባለፉት ዓመታት የህዝብን ድምፅ ሲሰርቅ የኖረው ገዥው ፓርቲ አሁንስ ከዚህ አመሉ ምን ያህል ይፀዳል የሚል ጥያቄና ስጋት አለብን። ለውጦች ቢኖሩም፤ ትናንትም፣ ዛሬም ነገም ምርጫ ውስጥ ለውድድር የሚገባው ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግ ደግሞ መሰረታዊ በሚባል ሁኔታ ባህሪው ተቀይሯል ብለን አናስብም።” ይላሉ።

አብን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የጊዜ ጥያቄ የለበትም። አሁን ባለው ሁኔታም ለምርጫ በሙሉ አቅሙ እየሰራ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ደሳለኝ ከቻሉ አሸንፎ ለብቻው የክልልና የፌደራል መቀመጫዎችን መያዝን፤ ይህ ካልሆነም አብላጫ ወንበሮችን አግኝቶ ከሌሎች ጋር ጥምር መንግሥት መመስረትን እንደሚያስቡ ያስረዳሉ።

“ሚሊሽያም ሚዲያም ያላቸው ፓርቲዎች አሉ” አቶ የሺዋስ አሰፋ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ “የጊዜ ጥያቄ የለብንም ነገር ግን መታየት ያለባቸው ብለን ለመንግሥት ያቀረብናቸው ጉዳዮች አሉ” ይላሉ።

ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት እና ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበቂ ሁኔታ ዝግጁ ናቸው ወይ? የሚለው አሁንም ጥያቄያቸው እንደሆነ በመጥቀስ፤ ከዚህ ባሻገር ደግሞ በገዢ ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚው በኩል በምርጫ ቢሸነፉ አሜን ብለው የማይቀበሉ ፓርቲዎች ይኖራሉ የሚል ስጋትም እንዳላቸው ይናገራሉ።

“የራሳቸው ሚሊሺያና ሚዲያም ያላቸው ፓርቲዎች አሉ። ገንዘብም አላቸው ምርጫውን ቢሸነፉ ስልጣን የማስረከብ አዝማሚያ አይታይባቸውም” በማለት ልማደኞች ናቸው ያሏቸው የገዥው ፓርቲ አባላትን በስም ይጠቅሳሉ። በሌላ በኩል ኢዜማ በምርጫ ቢሸነፍ ውጤቱን የመቀበል ችግር እንደሌለበት ይናገራሉ።

በፓርቲና በተወዳዳሪዎች መሰባሰብ አለበት ስለሚባለው የፊርማ ብዛትን በተመለከተ ኢዜማ ከሌሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለየ መልኩ ሃሳቡን እንደሚደግፈውና “ሁለትም ሦስትም እየሆኑ ፓርቲ ነን ማለትን ቅርፅ መያዝ አስፈላጊ ነው። አስር ሺህ ፊርማ እንዲያውም ያንሳል ” ይላሉ አቶ የሺዋስ።

ኢዜማ ከምርጫው የሚጠብቀው “በፖለቲካ ሜዳው ያለው የተዥጎረገረ ሃሳብ ፓርላማ እንዲገባ። ምርጫው የዲሞክራሲ መሰረትን የሚጥል እንዲሆን እንፈልጋለን። ትኩረታችንም ውጤቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ሂደቱም ነው፤ የኛ ትኩረትእንፈልጋለን” ሲሉ ያጠቃልላሉ።

“ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እናሂዳለን ተብሎ የተገባው ቃል መፈፀም አለበት” አቶ ቶሌራ አደባ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ በአዲሱ የምርጫ ህግ ሳይሆን በቀደመው ለመመዝገብ የተጠየቁትን ነገሮች በሙሉ አሟልተው የምርጫ ቦርድን ምላሽ በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ምንም እንኳ የጊዜ እጥረት ውጥረት ሊያስከትል ቢችልም በተቀመጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ተንቀሳቅሰው በምርጫ እንደሚያሸንፉ እምነት አላቸው።

ለዚህም ከሰላምና መረጋጋት አንፃር ሁኔታዎች አስቸጋሪ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች የምርጫ ዝግጅት እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ እንደሆነም ይጠቁማሉ።

በዚህ ሂደት ውስጥ ስለገጠሟቸው ችግሮችም ሲያነሱ “አንዳንድ ክልሎች ላይ ለመንቀሳቀስ አላስፈላጊ ቁጥጥሮች አሉ። ሌሎች ላይ ደግሞ የፀጥታ ችግር አለ። የተዘጉብን ጽ/ቤቶች አሉ፤ ሰዎች የኦነግ ደጋፊዎች ናችሁ እየተባሉ ይታሰራሉ” በማለት እነዚህ ነገሮችን መንግሥት ሊያስተካክል ግድ ነው ይላሉ።

ከዚህ ውጪ ግን በምርጫው የሚገኝን ውጤት ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን “ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እናከሂዳለን ተብሎ የተገባው ቃል መፈፀም አለበት እንላለን። እኛ ግን በምርጫው የምንፈራው ምንም ነገር የለም። ማሸነፍንም መሸነፍንም እንቀበላለን” ሲሉ ይናገራሉ።

“ህወትን ለስልጣኑ ስለምናሰጋው ነው ድብደባ፣ እስር እና ዛቻ እያደረሰብን ያለው” አቶ አንዶም ገብረ

ትግራይ ውስጥ ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው የአረና አባል የሆኑት አቶ አንዶም ገብረ ሥላሴ ቀጣዩን ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ በመንግሥት በኩል እንቅፋት የሆኑ ነገሮች አሉ ይላል።

“በተለይም በትግራይ የፖለቲካ ምህዳሩ በጣም አስቸጋሪ ነው። የአረና አባላት ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ ንብረታቸው ይቀማል የሚዲያ ተጠቃሚነትም የለም። በአጠቃላይ በአገሪቱ የሚስተዋለው አለመረጋጋትና በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያለው ሽኩቻም ለምርጫው አስቸጋሪ ነው” ይላሉ የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዶም ገ/ሥላሤ።

ቢሆንም ግን ፓርቲያቸው አሁንም ለምርጫው ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠው በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ “የቆየና የተደራጀ ፓርቲ ስለሆነ በትግራይና በአዲስ አበባ ለመወዳደር አስፈላጊ ዝግጅቶችን እያደረገ ነው።”ሲሉም ያክላሉ።

እንደ ሌሎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ሁሉ አቶ አንዶምም የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትን ለማረጋገጥ የተሰራው ሥራ ገና ወደ ታች አለመውረዱን ያነሳሉ።

በአዲሱ የምርጫ አዋጅ መሰረት የመንግሥት ሰራተኞች በምርጫ ለመወዳደር እጩ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ሥራቸውን ይልቀቁ መባሉን አረናም ይቃወመዋል።

በፓርቲ ደረጃ አስር ሺህ የአባላት ፊርማ ማሰባሰብን በተመለከተ ሲናገሩ “እንደ አረና በርካታ ዓመታትን ሲታገል ለቆየ ፓርቲ ይህ ችግር ሊሆን አይችልም” ሲሉ ይህን እንደማይቃወሙት አቶ አንዶም ይናገራሉ።

ከአንዳንድ ወገኖች አረና ትግራይ ውስጥ ድጋፉን እያጣ መሆኑን በሚመለከት የሚባለውን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ አንዶም “ይህ ቢሆን ኖሮ አረና ህወሓትን አያሰጋውም ነበር። ህወሓትን ለስልጣኑ ስለምናሰጋው ነው ድብደባ፣ እስርና ዛቻ እያደረሰብን ያለው” ሲሉ ይመልሳሉ።

አቶ አንዶም የሚያሳስባቸው የክልሉ ገዢ ፓርቲ የሆነው ህወሓት በመጪው ምርጫ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለውን ድምጽ ቢያጣ ስልጣን አይሰጥ ይሆናል የሚለው ሳይሆን “በመጀመሪያ ምርጫውን በትክክል ያካሂደዋል ወይ?” የሚለው ነው።