" /> መከላከያ ሰራዊት የአይ ኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ! | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

መከላከያ ሰራዊት የአይ ኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ!

መከላከያ ሰራዊት የአይ ኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገለፀ!
EPA : የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሞኑን የተወሰኑ የአይኤስ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ያልተያዙትም በጥብቅ ክትትል ውስጥ መሆናቸውን የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ጀነራል ብርሀኑ ጁላ አስታወቁ፡፡
ሰራዊቱ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሀገርና ሕዝብን ከአደጋ ለመጠበቅ እየሰራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ጀነራሉ እንዳስታወቁት፤ አይ ኤስ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ለመንቀሳቀስ በተደጋጋሚ ጥረት አድርጎ ቢመክንበትም በአገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የመለመላቸው፣ ስልጠና የወሰዱና የተጠመቁ ሰዎች እንዳሉ መንግስት በሚገባ እንደሚያውቅ ተናግረዋል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት የአይኤስ አባላት ምን እያደረጉ እንዳሉ፣ የት የት ቦታ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ፣ ከእነማን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው፣ በከተሞች ውስጥ ያሉት ሰዎቻቸው እነማን እንደሆኑ፣ ምን እየሰሩ እንዳሉ፣ እቅዳቸው ምን እንደሆነና ሌሎች መግለጽ የማያስፈልጉ ጉዳዮችም እጅግ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው ነው››ብለዋል ጀነራሉ፡፡
‹‹ሀገራችንንና ሕዝባችንን ከየትኛውም አደጋ ለመጠበቅና ለመከላከል ባለብን አደራና ከባድ ኃላፊነት የተነሳ ቀን ከሌት አንተኛም›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ኢታማጆሩ፤ ‹‹ሰራዊቱ እረፍት የሚባል ነገር አያውቅም፤ ያረፍንበት ጊዜም የለም›› ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ እንደ ጀነራሉ ማብራሪያ፤ አንዳንድ ጊዜ የሆነ ሰው እንደተገኘ ሄዶ መያዝና መቆጣጠር ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም ለአንድ ሰው ተብሎ ብዙ ነገር እንዳይታጣና እንዳያመልጥ በማድረግ በጥንቃቄና በሕግ አግባብ መቆጣጠር ስለሚቻል ሁኔታው አስቸጋሪ አይሆንም፡፡
አይ ኤስ ኢትዮጵያ ገብቻለሁ የሚለው በሕዝቡ ውስጥ ሽብር ለመልቀቅ በማሰብ የተጠቀመበት የሥነልቦና ጦርነት (ሳይኮሎጂካል ዋርፌር) ነው ያሉት ጀነራሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ የሚፈራና የሚደናገጥ አይደለም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ የአይ ኤስ ኦፕሬሽን አካሂዳለሁ የሚል አቅም እንደሌለው ገልፀዋል፡፡

የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV