ወጣቱ ያለፉት አባቶችን የዓላማ ጽናት በማሰብ አገሪቱን በተለያየ መንገድ ከሚፈታተኑ ችግሮች ለመከላከል ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

ENA : ተተኪው ትውልድ ጀግኖች አርበኞች የከፈሉትን መስዋእትነት በማሰብና የእነርሱን ፈለግ በመከተል አገሩን ሊጎዳ ከሚችል ችግር ለመከላከል ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ ጀግኖች አባት አርበኞችና ቤተሰቦቻቸው አሳሰቡ።

“አዲስ አበባ ቤቴ፤ኢትዮጵያዊነት ኩራቴ” – Photo BBC Amharic

የአሁኑ ትውልድ ይህንን የጀግኖች አባቶችን ገድል በተለያየ አገራዊ መስክ እንዴት ማስቀጠል አለበት? በሚለው ሀሳብ ዙሪያ ዛሬ የተከበረው ብሔራዊ የኩራት ቀንን የታደሙ አባት አርበኞችና ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት የዛሬዋን ኢትዮጵያ ለማቆየት የጀግኖች አርበኞች ሚና ትልቅ ነው፤ የዛሬው ትውልድም ይህንን ተጠብቆ የቆየ ክብር በተለያየ መስክ በማስፋት ለማስቀጠል ተግቶ መሥራት አለበት።

ወጣቱ ያለፉት አባቶችን የዓላማ ጽናት በማሰብ አገሪቱን በተለያየ መንገድ ከሚፈታተኑ ችግሮች ለመከላከል ጠንክሮ መነሳሳት እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።

ትውልዱ የኢትዮጵያ አንድነትና ብሄራዊ ክብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ የአገሪቱ ሰላምም እንዲረጋገጥ ዘብ መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል።

አባት አርበኛ ዋና ሳጅን ስዩም ኪዳኑ አለምን እያስደመመች ክብሯን፣ ህልውናዋን ያስጠበቀችን ሀገርን ወጣቶች እንደሚጠብቁ አደረራ ብለዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያዊነትን ከሚያጎድፉ እኩይ ተግባራት ራሱን በመጠበቅ አገሩንም በመልካም ስም ማስጠራት አለበትም ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ።

ለዚህም ቤተሰብ ስለኢትዮጵያ ታሪክና የአባት አርበኞች ገድል ለልጆቹ በማስተማር ልጆች ለአገራቸው ያላቸው ፍቅር የላቀ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታልም ሲሉ መክረዋል።

የአባት አርበኛ ልጅ ወይዘሮ የሺዋ ቅድስአድማስ በበኩሏ አገሩን በመተሳሰብና በፍቅር ሊጠብቅ ይገባል ነው ያለችው ፡፡

ከጳግሜ 1 ቀን 2011 ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በኢትዮጵያ ሰላም፣ ብሄራዊ አንድነት፣ ብልፅግና፣ አገራዊ ኩራት፣ ዴሞክራሲንና ፍትህን በመላው ዜጎች በማስረፅ ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበትን ሁኔታ ለማጠናከር የሚያግዙ ኩነቶች በመካሄድ ላይ ናቸው።

በዛሬው እለትም በዜጎች ዘንድ ብሄራዊ ኩራት እንዲመጣ፣ በዚህም በአገሪቱ የሚካሄዱት የሰላምና የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ የሚያግዝ ሞራላዊ አቅም ለመፍጠር ሲባል ብሄራዊ የኩራት ቀን ተከብሯል።

በተለይም በአዲስ አበባ “አዲስ አበባ ቤቴ፤ኢትዮጵያዊነት ኩራቴ” በሚል መሪ ቃል ነው በመስቀል አደባባይ በተሰናዳ ደማቅ ስነ-ስርዓት ብሄራዊ የኩራት ቀን የተከበረው።