የትግራይ ልጆችና የኦሮሞ ልጆች ልዩነት (ግርማ ካሳ)

መረጃ ቲቪን ሰብስክራይብ በማድረግ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ ትንተናዎችን፣ የኪነጥበብ ፕሮግራሞችን እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ማግኘት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

የትግራይ ልጆችና የኦሮሞ ልጆች ልዩነት (ግርማ ካሳ)

አንድ ታሪክ ልንገራችሁ። አንድ የግል መስሪያ ቤት ነው። ቦታዉንና የመስሪያ ቤቱን ስም አልጠቅስም። የመስሪያ ቤቱ ባለቤት የአንድ ወዳጄ ዘመድ ነው። የሚንቀሳቀሰው በኦሮሞ ክልል ነው። የመስሪያ ቤቱ የስራ ቋንቋም አማርኛ ነው። ከኦሮሞ ክልል ጋር የሚደረጉ የደብዳቤ ልውውጦች በላቲን ነው። መስሪያ ከክልሉ ወይም ወረዳው ደብዳቤ ሲደርሰውም ሆነ ሲልክ እያስተረጎመ ነው።

አንድ ከዩኒቨሲቲ የተመረቀ ሰው ተቀጠረ። አማርኛ ለመግባባት ያህል ይናገራል። ስራዉን ሰርቶ ሪፖርት መጻፍ ነበረበት፣ ግን ሪፖርት አያቀርብም። አለቃው ይጠራዉና ለምን ሪፖርት እንደማያደርግ ይጠይቀዋል። “ጋሼ ለምን አሁን እዚህ በቃል አልነግሮትም ? ” ይላል። “አይደለም ጊዜ ስለሌለኝ፣ ጽፈህ ዛሬዉን አቅርብልኝ” ሲል፣ ከወጣቱ ጋር መፋጠጥ ሆነ። “ጋሼ አማርኛ መጻፍ አልችልም” አለው።

Image result for ethiopia alphabet

አለቅዬው ደነገጠ። አላባረረዉም። አዘነለት። በስድስት ወር ውስጥ አማርኛ መጻፍ እንዲማር፣ እንደሚረዳው” ነገረው። መጽፍ ካልቻለ ግን፣ በስራው ላይ መቀጠል እንደማይችል፤ ቢዝነስ ስለሆነ አስቸጋሪ እንደሆነ ነገረው። እስከዚያውም” ሪፖርቱን በቃል እየነገርከኝ እኔ ለጊዜው እጽፍልሃለሁ” አለው። ከዚያ በኋላ ምን እንደሆነ አላውቅም።

ይሄ ወጣት ያጋጠመውን አይነት ችግር እንዳያጋጥማቸው ነው አማርኛ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል ከአንደኛ ክፍለ ጀምሮ እንዲሰጥ ለማድረግ አዲስ የትምርህት ፍኖተ ካርታ እነ ዶ/ር አብይ አሀምድ ያዘጋጁት። በዚህ አዲሱ ፍኖተ ካርታ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ፣ ሶማሌኛ አትማሩ አልተባለም። እንደውም እንደ አዲስ አበባና አማራ ክልል ያሉም ከ እንግሊዘኛና አማርኛ በተጨማሪ ሌላ ሶስተኛ ቋንቋም ይማሩም ይላል ፍኖተ ካርታው ያስቀምጣል።

ሕወሃት አማርኛ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርት እንዲሰጥ የሚጠይቀውን ይህን ፍኖተ ካርታ አልቀበልም ብላለች። ያንን ያለችው አማርኛ ትምህርት መሰጠቱን ተቃውማ አይደለም። የአማርኛን ጥቅም ጠንቅቃ ታውቀዋለች። ግን የዶ/ር አብይን አስተዳደር ለመቃወምና ለማሳጣት ሰበብ ሁልጊዜ ስለምትፈለግ ነው። የኦሮሞ ጽንፈኞች እነ ጃዋር፣ የነዚህን ጽንፈኞች ማስጠንቀቂያ በመፍራት የኦሮሞ ክልል መንግስት፣ እነ ሺመለስ አብዲሳ፣ ከኦሮሞ ጥቅም ጋር በጣም የሚጋጭ አስተያየት ሲሰጡ፣ “አማርኛን ከአንደኛ ክፍለ ጀምሮ መማር የለብንም” ሲሉ ህወሃትም አገኝሁ ብላ፣ ከበሮ እየመታች፣ “አዎ መማር የለብንም” እያለች ነው።

አስቡት ፣ ኢሕአዴግ ስልጣን ሲይዝ፣ ከአስር አመታት በላይ፣ እንደነ አዳማ ካሉ አካባቢዎች ውጭ ፣ በሁሉም የኦሮሞ ክልል ፣ የነፍጠኛ ቋንቋ ተብሎ፣ አማርኛ እንዳይሰጥ ተደርጎ ነበር። እነ አዳማም ሕዝቡ አምጾ ነው የተፈቀደው። ወለጋ፣ አርሲ፣ ሃረርጌ፣ ቦረና …አማርኛ የሚባል ነገር አልነበረም። በኋላ ፣ “አይ ማሻሻል አለብን” ብለው ከአምስተኛ ነው ከስድስተኛ፣ በሳምንት ሁለት ክፍለ ጊዜ ብቻ እንዲሰጥ አደረጉ። ስለዚህ የኦሮሞ ልጆች የግል ትምህርት ቤቶች ካልተማሩ በቀር፣ አማርኛ መጻፍና ማንበብ አይችሉም።

በኦሮሞ ክልል በዚህ መልኩ የኦሮሞ ልጆች ወደ ኋላ እንዲቀሩ ሲደረግ፣ በትግራይ ግን ሕወሃት ኦፊሴላዊ በሆነ መንገድ፣ ከሶስተኛ ክፍለ ጀምሮ ላለፉት 28 አመታት አማርኛን በትግራይ ስታስተምር ነበር። ኦፊሴላዊ አይደለም እንጂ፣ እንደውም ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ነበር አማርኛ ታስተምር የነበረው ማለት ይችላል። ለምን ብትሉ ትግሪኛ ከተማሩ፣ የትግሪኛ ፊደል፣ ሀ ሁ ሂ ሃ ሄ ህ ሆ …ስለሆነ፣ የአማርኛ ፊደል ተማሩ እንደማለት ስለሆነ።

አማርኛ የፌዴራል መንግስት፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደር፣ የደቡብ ፣ የጋምቤላ፣ የቢኔሻንጉልና የአማራ ክልሎች የስራ ቋንቋ ነው። በኦሮሞ ክልል በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያና በሸዋ፣ የግል መስሪያ ቤቶች የስራ ቋንቋ ነው። ከሰማኒያ በላይ የኢትይጵያ ኢኮኖሚ የሚንቀስቀሰው በአዲስ አበባ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሸዋ ነው፤ አብዛኛው ነዋሪ ሕብረ ብሄራዊና አማርኛ ተናጋሪ በሆነበት ቦታ።

የትግራይ ልጆች ከትግሪኛ በተጨማሪ አቀላጥፈው አማርኛ ማንበብና መጻፍ ስለሚችሉ እንደ ኦሮሞ ልጆች ወደ ኋላ አልቀሩም።

እንግዲህ የተወሰነ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብለው፣ የነርሱን ልጆች ፣ አዲስ አበባ እንደ ሊሴ ገብረማሪያም፣ ቅዱስ ዮሴፍ፣ ናዝሬት ስኩል፣ አሜሪካ ሚሽን ..የመሳሰሉ የግል ት/ቤቶች፣ አማርኛን ብቻ አይደለም፣ እንግሊዘኛን፣ ፈረንሳይኛን..ያወቁ ዘንድ እያስተማሩ፣ በድሃው የኦሮሞ ልጅ ሕይወት ላይ ቁማር የሚጫወቱ፣ የኦሮሞ ጽንፈኛ ፖለቲከኞችን ተንኮል የኦሮሞ ልጆች አውቀውና ተረድተው አንቀረው ካልተፉፏቸው የሚጎዱት እነርሱ ናቸው።

የኦሮሞ ልጆች አማርኛ ባለመማራቸው ትግሬው፣ ወይን አማራውም፣ ወይም ጉራጌው..አይጎዳም። ሕወሃቶች በሚሉት አይታለሉ። ትግሬዎቹ በደንብ ነው አማርኛን የሚማሩት። ሶማሌና አፋር ክልልም ፍኖተ ካርታዉም በደስታ ነው የተቀበሉ።የሚጎዱት ደግሜ እላለሁ እነርሱ ናቸው።

ማን እንዳለው አላውቅም አንድ ትክክለኛ አባባል ላስቀምጥና ላቁም። አማርኛን ለኦሮሞ ልጆች አለማስተማር ዶዶላ የተወለዱ፣ ዶዶላ አድገው፣ ዶዶላ ኖረው፣ እዚያው ዶዶላ እንዲኖሩ ማድረግ ነው። ወድ ሌላ ቦታ ሄደው ሕይወታቸው እንዳይሻሻል ማገድ ነው።