የጃዋርን ሀሳብ ስቀሉት! – የቦረናው ሙክታር አደም ለኦሮሞ ጽንፈኞች ይናገራል

(ሙክታሮቪች ኦስማኖቭ)
የኦሮሞ ወጣቶች ሆይ ጃዋርን ስቀሉት።
አዎ! እሱን ትታችሁ፣ ሀሳብና የገነባውን ተክለስብዕና ስቀሉት። ሀሳቡን ስቀሉት!
ይህን ለምን እንደምል በጥሞና አድምጡኝ።

*****
የጃዋር መንገድ የጤነኛ ፖለቲካ መንገድ አይደለም። የፖለቲካን መካረር ጉዳይ በቋንቋ ጭንብል ማቅረብ ስህተት ነው። የፖለቲካ ጉዳይ በፖለቲካ መንገድ፣ ሰጥቶ በመቀበል፣ በመደማመጥ እና የጥቅም ግጭትን ወግ ባለው፣ ስርአት በተበጀተለት፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ “እነሱ የኛን ካልተማሩ እኛም የነሱን አንማርም የሚለው ብሂል ጉዳዬ ከአማርኛ ጋር ሳይሆን ከህዝብ ጋር መሆኑን የሚያሳይና ለመግባባትም መፍትሄ የማያመጣ የእልህ ፖለቲካ ነው። የፖለቲካ ጉዳይን በትምህርት ጭንብል ማቅረብ ትክክል አይደለም። መደረግም ካለበት ወይይቱ ለልጅ ከአፍ መፍቻ በተጨማሪ ሌላ ቋንቋ ማስተማር ማንነቱን ያስለውጠዋል ወይ ብሎ ጥያቄውን በዚህ መንገድ ፍሬም በማድረግ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ለሀገርና ለትውልድ የሚጠቅም የሀሳብ ሙግት ማድረግ ነው። የጥላቻና የእልህ መንገድ፣ የመንግስትን እጅ መጠምዘዝ ለሁላችንመ የማይበጅ በመሆኑ ተክለስብእናውን በመቅበር በእራስ ማሰብን መለማመድ በማስፈለጉ:

የጃዋርነ ሀሳብ ስቀሉት!

ስለቋንቋና ባህልና የልጆች ትምህርት ጃዋር ከሚናገረው ባሻገር ማንበብ፣ ማሰናሰል እና ግራቀኝ ማየት ያስፈልጋል።
+
በዚህ በኩል እኔ ኢንተርኔት ውስጥ መልከት ባደረግኩት መሰረት:—
• ልጆች እስከ አስራ ሰባት ቋንቋ በአንድ ላይ በአንድ ወቅት መማር የሚችሉ መሆኑን
• ተጨማሪ ቋንቋ በልጅነታቸው የሚችሉ ልጆች ችግር የመፍታት፣ አካባቢን የመረዳት፣ ነገሮችን በተለያዩ አቅጣጫዎች የመመልከት፣ በቡድን የመስራት፣ የመተባበር፣ ከሰው የመግባባት እና ሌሎች ችሎታዎችን ለማዳበር እንደሚጠቅማቸው
• የብዙ ቋንቋ ባለቤት መሆን ከነባርና አንድ ሰው ከበቀለበት ባህል የማያፈናቅል መሆኑን። ልጆች ባህላቸውን እና ማንነታቸውን እንዳይዘነጉ በልጆች ላይ መሰራት ያለበት የእራስን እሴት አጉልቶ በማውጣት፣ በህፃናት መፅሃፍ፣ በካርቱን፣ በተረትና ትውፊት ማድረግ እንጂ ሌላን ቋንቋ እንዳያውቁ በማገድ አይደለም። የኦሮሞ ማንነት የምስራቅ አፍሪካ ባህልና ቋንቋን የሚሸፍን፣ በምንም መንገድ ከመስፋፋት ሊታገድ የማይችል የደረጀ ማንነት ነው። ፅንፈኞች ፍርሃት በመንዛት ቅዠት ይፈጥራሉ እንጂ የኦሮሞን ማንነት ምንም አይነት ምድራዊ ሀይል ሊያጠፋው ቀርቶ ሊያደበዝዘው አይችልም። ትልቁን ብሄር እንደ ህዳጣን (minority) በመመልከት ስጋት መፍጠር የብሄርተኞች ዘዴ እንጂ እውነታቢስ የቀን ህልም ነው።
ስለዚህ የጃዋርን ሀሳብ ስቀሉት!

በፖለቲካ ስጋት እንኳ ቢኖር ጉዳዩ መያዝ ያለበት በነጃዋር መንገድ በእልህ ሳይሆን በብልጠት የነገ ውጤትን በመሳል ሰጥቶ በመቀበል የበሰለ ዊን—ዊን መንገድ ነው። ስለዚህ ትክክለኛው አካሄድ ሌላውን የሃገሪቱን ህዝብ በዲፕሎማሲ ማሳመንና ድጋፍ ማግኘት፣ በክልላቸው 2ኛ ቋንቋ አድርገው እንዲያተምሩ ማሳመን፣ ከዚያ ቀጥሎ የቋንቋ ፖሊሲ እንዲሻሻል ማድረግና በመጨረሻም የህገ-መንግስት ማሻሻያ ማድረግ ነው። ከዚያ ውጪ የጋሽ በቄም ሆነ የጀዋር አካሄድ ውጥረት ከማንገስና ሌላው ህብረተሰብ እልህ ውስጥ እንዲገቡና ለቋንቋን ጥላቻ እንዲያሳድሩ ከማድረግ ውጪ ምንም ጠብ የሚል ለውጥ አያመጣም።

ስለዚህ የጃዋርን ሀሳብ ስቀሉት!
+

ኦሮሞ የአማራ ወንድሙን ጥቅም በፍፁም መርሳት የለበትም። አራት ኪሎ ለመግባት የአማራ ወዳጅነት ምን ያህል እንደጠቀመ መረሳት የለበትም። የደመቀና የገዱ እርዳታና መደጋገፍ ባይኖር ኖሮ ዶክተር አብይ ድል ያደርግ ነበር? አማራን ማስከፋትም በተቃራኒው ተረጋግቶ ሀገር ለመምራት ያስቸግራል። እርግጥ አንዳንድ ፅንፈኞች ብዙ የሚያስከፋ ነገር ይላሉ። እነሱን ሳይሆን ገዱ በባህርዳር “እናንተ አማርኛም ኦሮምኛም ትችላላችሁ፣ እኛ አማርኛ ብቻ ነው የምንችለው። ኦሮምኛ ባለመቻላችን ምን ያህል እንደጎደለን ብታውቁት፣ ብንችል ምን ያህል እንደምንደሰት ብታውቁት፣ በአማራ ክልል ኦሮምኛ እንደተጨማሪ ቋንቋ ለመስጠት ስራ እንጀምራለን ነው ያሉት።

እነዚህን እና የማውቃቸው፣ እኔ በመቻሌ እነሱ ባለመቻላቸው የሚቆጩ ሚሊየኖችን እንጂ የፌስቡክን ፅንፈኛ አትስሙት። የአሊቢራን ሙዚቃ በፍቅር የሚሰሙ፣የሚሰሙ፣ ትርጉሙን ለማወቅ የሚንሰፈሰፉ ብዙ ልጆች ከሁሉ ብሄር አሉ። ቋንቋውን ለነሱ ለማድረስ ስሩ። ዲክሽነሪ በስፋት ፃፉ። ኦሮምኛን በቀላል መንገድ አስተምሩ በቪድዮ፣ በቴሌቭዥን በሬዲዮ አስተምሩ። በየክልሉ ፈንድ ኢንሴንቲቭ በመስጠት በየክልሉ እንዲሰጥ ስሩ። መፅሃፍ ወደ ኦሮምኛ ተርጉሙ። እነ ፍቅር እስከመቃብር እነ ትኩሳትን የባዓሉ ግርማን ኦሮማይ ተርጉሙ። ህዝብ አቀራርቡ። አስታውሳለሁ በልጅነቴ ቅዳሜ “ደንጋ” የተሰኘው ዘጠኝ ሰዓት የቲቪ መዝናኛ በሁሉ ብሄር ተወዳጅ ነበር። ይሄ መንገድ አልፊ መንገድ ነው። ለትውልድ የሚያስብ ብቻ የሚሰራው ነው። ብሄርተኞች ለብሄራቸው የሚሳሱ ከሆነ መንገዱ ይሄ ነው። መጠላለፍ ለደህነት፣ ስደት፣ በሽታ፣ ረሀብና ውርደት ነው የሚዳርገን። ተያይዞ መበልፀግ፣ አልያም ተጠላልፎ መውደቅ ነው። የመውደቁ ነገርን ከሶሪያ መማር፣ ከየመን፣ ከሊብያ፣ ከደቡብ ሱዳን ካልተማርን እንዴት የተማሩ ሰዎች እንባላለን። ቅንነት ካለ መንገድ አለ-If there is a will there is a way! በመያያዝ በመጠላለፍ በጃዋር መንገድ የት መድረስ እንደሚቻል ማሰብ ያስፈልጋልና

የጃዋርን ሀሳብ ስቀሉት!

++++
መንግስት ሀቅሙ አለኝ ካለ እንኳን አማረኛን ከ70% በላይ የሀገራችን ህዝብ የሚናገረውን፣ የፌደራል የስራ ቋንቋ ሁኖ ለአመታት ያገለገለውን፣ ለአመታት በስነፅሁፍ፣ በታሪክ፣ በፍልስፍና በጥንታዊ ሀገር በቀል እውቀቶች የተሰነዱበት ቀርቶ ሁሉንም የኢትዮጵያ ቋንቋ ማሳደግ መንከባከብ አለበት። ኦሮሚኛም ማደግ አለበት። ሶማሊኛም፣ አፋሪኛም ማደግ አለበት። ሆኖም የነዚህ እድገት አማርኛን ከመጥላት መነሳት የለበትም። አማርኛ የአማራ ብቻ ሀብት አይደለም። የሁሉ ሀብት ነው። ፀጋዬ ገ መድህን ቀዌሳ እና ስብሃት ገብረእግዛብሄርን ሳናነሳ የአማርኛን ስነፅሁፍ ማንሳት እንችላለን። ወደድንም ጠላንም ተቀበልነውም አልተቀበልነውም ታሪካችን፣ ድላችን ሽንፈታችን የተከተበበትን፣ እትየለሌ ሀገር በቀል ጥናቶች የተከተቡበት በአማርኛ ነው።

የጭቆና ታሪካችንም በግዕዝና አማርኛ ነው የተሰነደው። እነዚህን የጋራ ሀብት አለመማር በትውልድ ላይ ወንጀል መፈፀም ነው። ነውር ነው። ቋንቋን ከፖለቲካ መቀላቀል የለብንም። የቋንቋ ተቋም ከፍተን በምስራቅ ያሉትን ወንድሞቻችን ሱማሌኛ፣ በደቡብ ያሉትን ሲዳመኛ፣ በምእራብ ያሉትን ደግሞ ጉምዘኛ ማስተማር አለብን:: ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። ለምን በግል የፖለቲካ አቋማችን ህፃናት ላይ እንፈርዳለን። አፋን ኦሮሞን ለማሳደግ እኮ የግድ ሌላን መራቅ አያስፈልግም። ሲጀመር አማረኛና አማራ ይለያያሉ። ኦሮሞና አፋን ኦሮሞ አንድ ሊሆኑ ይችላሉ። ተጋሩና ትግረኛ አንድ ሊሆኑ ይችላሉ። አማረኛ ግን የሁላችን የኢትዮጵያውያን ነው። አማረኛን ለአማራ ብቻ መስጠት ተገቦ አይደለም። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊነት ለአማራ ብቻ ይሰጥ ነበረ። ይህ ስህተት መሆኑን ብዙ ሰው ያምናል። በኢትዮጵያ በመልካሙም በመጥፎውም ሁላችንም አለንበት። ከቃላት ማዋጣት ጀምሮ በስነ ፅሁፍ ቋንቋውን ያሳደገውን ህዝባችንና የስነ ጥበብ ባለሙያዎቻችንን ማሳነስ ነው። ልክ የአደዋ በአልን ለአንድ ህዝብ አጎናፅፈን የወንድም እህቶቻችንን ደም ደመ ከልብ ስናደርገው እንደኖርነው አሁንም ሌላ አዙሪት ውስጥ ሊከቱን ነው። አማርኛ የሁሉ ኢትዮጵያዊ ሀብት ነው። እስኪ ኦሮሞው ጥላሁን ገሰሰን፣ ጉራጌው ማህሙድ አህመድን፣ጉራጌው ቴዲ አፍሮን ሳታስብ የአማረኛ ሙዚቃን እሰቡት? ኦሮሞውን ሎሬት ፀጋየ ገ/መድህንን ትግሬውን ፈላስፋ ስበሃት ገ/እግዜአብሄርን ሳታስብ የአማረኛን ስነአፅሁፍ አስቡ።

ስለዚህ የጃዋርን ሀሳብ ስቀሉት!

+++

ጃዋር ፖለቲካን የሚረዳበት መንገድን ማሰብ ያስፈልጋል። የህዝብ ለህዝብ ያደርገዋል። እነዚህ ሰዎች ይላል፣ ባዕዳን ይላል፣ ጠላቶቻችን ይላል። ፖለቲካ በዚህ መንገድ አይቃኝም። ወጥተህ ደም እንድታፈስ ግፋ ይልሃል። ልጆቻቸው አበቋንቋቸው አያስተምሩም፣ ኦሮምኛ አማራ ክልል እስካልተሰጠ ይላል። ገዱ እኮ በቁጭት መማር አለብን ብሎ ነበር። እሱ ይሄን ረስቶ አይደለም። ደም ለማፍሰስ ነው። ከራሳቸው ወይ ከዘመዳቸው ደም ግን ጠብታ አይፈስም። እሱ ህዝቡን ከመውደድ የሚጠላ ያስመስልበታል። ያልጠላኧውን ሕዝብ ፀብ ለምን ትፈልግለታለህ ? ለውጥ ካመጣህ በሃላ ለምን ሌላ ዙር ፀብ ትፈልጋለህ? ለምን? እንጮሃለን ይሉሃል እንጂ በጩኧትህ ሰዓት ከነቤተሰባቸው ሀገር ውስጥ የሉም። እንሞታለን ይሉሃል እንጂ ሙቀቱ ሲቀየር ድራሻቸው ጠፍቷል። እንቆስላለን ይሉሃል እንጂ አይመቱልህም። አንተና ቤተሰብህን በማራቆትና ስጋት በመፍጠር አዳኛቸው እንደሆኑ ለማሳመን ነው። ይህ የብሄርተኝነት አስተሳሰብ ነው። ልትጠፋ ነው፣ አለቀልህ እያሉ ማስፈራራት። በዚህ ሁሉ ውስጥ፣ ተበላህ እያሉ ሌላ ሕይወትህ ላይ እንዳታተኩር ቸንክረው ይይዙሃል። የኢኮኖሚ፣ የፆታ፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የስራ ሁኔታ አያሳስባቸውም። በነጠላ ችግር ላይ ሰቅዘው አምጣ አምጣ እያሉ ከኪስህ ኪሳቸውን ይሞላሉ። አንተ ጀግኖቻችን ትላለህ። ለነሱ ግን የገንዘብ ምንጫቸው ነህ። «ለኛ ብለው» ትላለህ እነሱ ግን ለራሳቸው ብለው ከሆነ ቆይቷል!

ስለዚህ የጃዋርን ሀሳብ ስቀሉት!
+

የሰሞኑን የቋንቋ ነገር ብቻ አንሳ። ካጠሩልህ አጥር እንዳትሻገር ስለሚፈሩ አይሆንም ይሉሃል። ምንድነው ችግሩ ብትል በውል አይነግሩህም። ችግሩ ከቅንፋቸው እንዳትወጣ ነው። ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝማችን ይሉሃል እንጂ፣ የሚጨነቁት የገቢ ምንጫቸው ከመሆን እንዳታመልጥ ነው። በትምህርታቸው ሰቃይ የሚባሉት ፊንላዶችን ሂድና እይ። ስንት ተጨማሪ ቋንቋዎች እንደሚማሩ አየት አየት አድርግ። ከመጠቀም አልፈው፣ ትምህርት ማለት እንዲህ ነው ተባለላቸው እንጂ ማንነታቸውን አላጡም። ሲጀምር ማንነት ቋንቋ ብቻ አይደለም። ግን ቋንቋው ላይ ካልተቸነገርክ ወደ ሌላ ነገር ታነጣጥራለህ ብለው ስለሚሰጉ ቀድመው ይጋርዱሃል። ጉዳዩ ቋንቋውን እየለመዱ ሌሎቹንም ቋንቋዎች ወደዚህ ደረጃ ማምጣት መሆን ሲገባው አትድረሱብን አንደርስባችሁም ይባላል። ለምን ብለህ ጠይቅ! አንተን ለመድፈን ነው። ለመድፈቅ ነው። የእነሱ ባሪያ ለማድረግ ነው። ጥያቄያቸው ከዚህ በፊት ቃል እንደተገባው በአማራ ክልልም ኦሮምኛ ይሰጥ እኛም ጋር ከታች ጀምሮ አማርኛ ይሰጥ አይሉህም። ጭንቀታቸው ቋንቋ አይደለማ! ኦሮምኛው አደገ አላደገ አይደለም ጉዳያቸው። ተቀባይነታቸው እንዳያንስ፣ ኪሳቸው እንዳይጎድል ነው። ሌሎች ቋንቋዎችን አውቀህ እየተዋሃድክ ተነጥለህ ዝመት ስትባል አለመገኘትህ ነው የሚያሰጋቸው። ቋንቋ ካወቅክ ተናጋሪውን ታውቃለህ። ተናጋሪውን ካወቅክ ባህሉን፣ ስነልቦናውን ታውቃለህ፣ አስተሳሰቡን ታውቃለህ፣ ችግሩ ችግርህ እንደሆነ ታውቃለህ። የአንድ ሀገር ልጆች መሆናችሁን ታውቃለህ። አባቶቻቹህ ለአንድ ሀገር ባንድ ጉድጓድ መቀበራቸውን ታውቃለሁ። ይህን ካወቅክ የእራስህ ባለቤት ትሆናለህ። የራስህ ባለቤት ከሆንክ አትታዘዝም፣ ካልታዘዝክ አይመቻቸውም። ነፃ ከሆንክ ይከስራሉ።

ስለዚህ የጃዋርን ሀሳብ ስቀሉት!
+

ጃዋር መሀመድ ከኦሮሚያ አልፎ በመላ ሀገሪቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን የቻለው ከኦሮምኛ በተጨማሪ አማርኛን አቀላጥፎ መናገር በመቻሉ ነው። በእርግጥ ጃዋር እንግሊዘኛ መናገር የሚችል ቢሆንም ቋንቋው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ፋይዳ ቢስ ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥ ኦሮምኛ ብቻ ተናጋሪ መሆን በራሱ ችግር የለውም። ነገር ግን ኦሮምኛ ብቻ ተናጋሪ መሆን ተፅዕኖ የመፍጠር አቅምን ኦሮሚያ ውስጥ ብቻ እንደ መገደብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ አማራ ክልልን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች የመስራት እድልን ማጥበብ ነው። በሌሎች የሀገሪቱ አከባቢዎች በኦሮምኛ እግባባለሁ ብሎ ለማለት አሁን አማርኛን ማስተማር ከባድ የሆነውን ያህል ፈታኝ ነው። በመሠረቱ ኦሮምኛ የፌደራል ቋንቋ ይሁን ማለት መብት ነው። ሆኖም ግን “ኦሮሚያ ውስጥ የሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች አማርኛ መማር የለባቸውም” ማለት ክፋት እንጂ ፖለቲካ አይደለምና

የጃዋርን ሀሳብ ስቀሉት!

ጃዋር ታሪክን የማያገናዝብ ነው። 1983 ሌንጮና ጓደኞቹ አማርኛ አንናገርም ሲሉ መለስ ዜናዊ እየተረተበት፣ እያሳመነበት፣ ቅኔ እየተቀኘበት ገዛን፣ ጨፍድዶ ገዛን፣ የኦሮሞን ወጣት ገደለ፣ አሰረ፣ አሳደደ። እስርቤቱን በኦሮምኛ ተናጋሪ ሞላው። የኦሮሞ ልጆች ዛሬም ፖለቲካቸውን ለሌሎች ህዝቦች የሚያደርሱበትን መንገድ እሱ ጃዋር እየተቀኘበት፣ እያብራራው ነገርግን ለኦሮሞ ቀጣይ ትውልድ ንፉግ ሆነ። ምቀኝነት ነው። እሱ ዝና እና እውቅና ያገኘበትን መልቲሊንጓል ለሌሎች ነፈገ። እሱን ከማንነቱ ካላፈናቀለው ሌላውን እንዴት ያፈናቅላል? ብሎ መጠየቅ አለበት የኦሮሞ ወጣት። የስራ እድሉን እንዳያበዛ፣ ተዘዋውሮ እንዳይነግድ፣ በመንደሩ እንዲወሰን፣ ከሌሎች ጋር እንዳያወራ፣ ታሪኩን እንዳይመረምር ፣ በኢትዮጵያ ሀገሩ ላይ ከወገኖቹ ጋር እንዳይግባባ ስለሚፈልግ ነው። አማርኛን በማወቁ የተጎዳ የለም፣ የተጠቀመ ቢሆን እንጂ። ጃዋር ለምን በቋንቋና ባህል፣ በማንነትና ቋንቋ የበቃ እውቀት ሳይኖረው መንግስት በሞያቸው ጣሪያ የነኩ ሙህራን ያጠኑትን ወደ ፖለቲካ ተግበር መንዝሮት ያጦዘዋል? ይህ እልህ መጋባት ለኦሮሞ ይበጃል? ለተማሪ ይበጃል? ለሀገር ይበጃል? ገና በሽግግሩ እንዲህ ያለ ምርጫው በኦሮሞ ፓርቲ አሸናፊነት መንግስት ሲመሰረት ምን ሊል ይችላል ብሎ ሌላው ህዝብ አይጠራጠርም? ፖለቲካ በስክነትና ብስለት በኢሊቶች መግባባትና በሀላፊነት በተሞላበት አውድ እንጂ ኪቦርድ ላይ ተሁኖ በዛቻ ይሆናል? ይሆናል ወይ!? ከስሜት ወጥታችሁ በራሳችሁ አስባችሁ፣ ለህዝባች መጪ እጣፈንታ በማሰብ በስክነት ካሰባችሁ:

ጃዋርን አትሰቅሉትም!
ሀሳቡን ትሰቅላላችሁ!
ተክለስብእናውን ትሰቅላላችሁ!
በራሳችሁ ቆማችሁ እውነትን ከሀሰት ለመለት ትችላላችሁ!
(ማሳሰቢያ: የጃዋርን ስም ልጥራ እንጂ ይህ ለሁሉ ፅንፈኛ ብሄርተኛ የታሰበ ፅሁፍ ነው። ሀሳቡም ከክፋት ሳይሆን ለሀገር ከማሰብና ከመጨነቅ የመጣ ነው። ፋይዳ ቢስ ከሆነ ባላየ እለፉት። የሚጠቅም ነገር ካለው#ሼር ያድርጉት)