በጄኔራል አሳምነው ፅጌ የተመራ ክልላዊ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ መደረጉን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስታወቀ (DW)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ የተመራ ክልላዊ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ መደረጉን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አስታወቀ። የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራው መክሸፉን የክልሉ ገዢ ፓርቲ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በአማራ ቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጠው መግለጫ ማሳወቁን ጀርመን ራዲዮ (DW) ዘገበ።

በተጨማሪም፣ በባህር ዳር የሚገኘው ጀርመን ራዲዮ ጋዜጠኛ የሚከተለውን ዘግቧል። የፌደራል የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ በተደረገባት የባሕር ዳር ከተማ ተሰማሩ። የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት መኮድ ተብሎ ከሚጠራው የጦር ሰፈር ወደ ከተማዋ የዘለቁ ወታደሮች የጸጥታ ቁጥጥር እያደረጉ ናቸው።
ከመንፈቅለ መንግሥት ሙከራው ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ባሕር ዳር ከምሽቱ 12 ከ30 ጀምሮ ቢያንስ ለግማሽ ሰዓት የዘለቀ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የከተማዋ ነሪዎች እንደሚሉት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልሉ ምክር ቤት እና የርዕሰ-መስተዳድሩ ፅህፈት ቤት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የተኩስ ድምፅ ተሰምቷል።

አንድ የከተማዋ ነዋሪ “ተኩስ የጀመረው ፖሊስ ኮሚሽን አካባቢ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ከፖሊስ ኮሚሽን ፅህፈት ቤት አቅራቢያ የነበሩት እኚሁ የዐይን እማኝ “የቀላል እና የከባድ መሳሪያ ተኩስ” መስማታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በክልሉ ልዩ ኃይል አዲስ እና ነባር አባላት መካከል ቀደም ሲል ግርግር እንደነበር መስማታቸውንም ገልጸዋል።