በኢትዮጵያ የሚሰሩ አገር በቀል የሰብዐዊ መብት ድርጅቶች መሪዎች ከሃገር ተሰደዱ

“የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ለሰላም” የተሰኘው አገር በቀል ድርጅት፣ የመብቶችና ዴሞከራሲ ዕድገት ማዕከል መስራችና አመራር አጥናፍ ብርሃኔ፣ የስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ኤደን ፍሰሃና ተተኪያቸው መሠረት ዓሊ እንዲኹም የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋ፣ የጸጥታ አካላት በአካልና በስልክ ባደረሱባቸው “ዛቻ”፣ “ወከባ” እና “ማስፈራሪያ” በተለያዩ ጊዜያት ከአገር መሰደዳቸውን ከደረሱት አቤቱታዎች መረዳቱን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ፣ በሲቪል ማኅበራትና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ላይ የሚደርሱ ጫናዎች እና እገዳዎች “የሲቪል ማኅበረሰቡን ምኅዳር የሚያጠቡ”፣ በማኅበራቱ ላይ “ፍራቻን የሚፍጠሩ” እና የነቃ ተሳትፏቸውን “እጅግ የሚያኮስሱ” ናቸው በማለት ተችቷል። በቅርቡ “የመብቶችና ዴሞከራሲ ዕድገት ማዕከል”፣ “ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ” እና “የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች” በተባሉ ማኅበራት ላይ የተጣለው እገዳም፣ “በነጻነት የመደራጀት”፣ “የመሰብሰብ” እና “ሐሳብን የመግለጽ መብትን የሚጎዳ” እና “የመንግሥትን ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስጠበቅ ግዴታን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ” እንደኾነ ድርጅትቱ አውስቷል። ድርጅቱ፣ መንግሥት በሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ላይ የሚወስዳቸው ርምጃዎች ሕጋዊ አሠራሮችን የተከተሉ መኾናቸውን ማረጋገጥ እንዳለበትም አሳስቧል።