“ደሞዝ ሳይከፈለን ሶስት ወር አለፈን”- በወላይታ ዞን የሚገኙ ሰራተኞች

  • “ደሞዝ ሳይከፈለን ሶስት ወር አለፈን”- በወላይታ ዞን የሚገኙ ሰራተኞች
  • “ከዚህ ወር ጀምሮ ክፍያ መፈፀም እንጀምራለን” የዞኑ አስተዳዳሪ ለመሠረት ሚድያ

(መሠረት ሚድያ)- በወላይታ ዞን ውስጥ ላለፉት ሦስት ወራት ደመወዝ ባለመከፈሉ ምክንያት በርካታ ዜጎች በከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ለመሠረት ሚድያ መረጃ አቅርበዋል።

“እኔንና ባለቤቴን ጨምሮ እንዲሁም ሦስት ልጆቼ በከባድ ችግር ውስጥ ነን” ብሎ ያለበትን ሁኔታ የገለፀው አንድ በዞኑ የሚገኝ ሰራተኛ የለት ተለት ኑሮ በእጅጉ እንደከበደው ያስረዳል።

“በዚህ የኑሮ ውድነት ምን እንሁን? የቤት ኪራይ መክፈል አቅቶን ውጡ እየተባልን ነው” ያለው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ተማፅኗል።

በዚህ ዙርያ መሠረት ሚድያ ከቀናት በፊት የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙትን አቶ ጴጥሮስ ወልደማርያምን አነጋግሯል።

ችግሩ አዲስ ሳይሆን ከአመታት በፊት ሲንከባለል የመጣ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ጴጥሮስ በአዲስ አወቃቀር ዞኑ ከ3 ከተማ እና 12 የገጠር ወረዳ ወደ 23 የገጠር ወረዳ ማደጉ አንዱ ምክንያት ነው ይላሉ።

“ከዚህም በተጨማሪ በእነዚህ 23 የገጠር ወረዳዎች ላይ ከመጠን ያለፈ የሰራተኛ ቅጥር ነበር። የሰራተኛው ቁጥር ከ23 ሺህ ገደማ ወደ 65 ሺህ አድጎ ነበር” ያሉት የዞኑ ሀላፊ የበጀት ማነስም ሌላው ምክንያት ነው ይላሉ።

“ደሞዝ መክፈል አለመቻል ብቻ ሳይሆን የልማት ስራም በሚፈለገው ልክ እየተሰራ አይደለም። ከዚህ ጋር ተያያዞ በ 2016 ወጪ የመቀነስ ስራ ለመስራት ተሞክሯል። የሚገርመው ግን የአሁኑን ብቻ ሳይሆን የመጪውን 2017 በጀት የጨረሰ ወረዳ አለ” ብለው አስረድተዋል።

ይህ እንዳለ ሆኖ የወላይታ ዞን እየተገባደደ ያለውን የነሐሴ ወር ሙሉ ደሞዝ ለመክፈል ፔይሮል እየተሰራ መሆኑን አስታውቀው ይህም በቅርብ ቀናት ይፈፀማል ብለዋል።

ያልተከፈለው የሶስት ወር ደሞዝን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ጴጥሮስ “እሱ ከመዋቅር ጋር ገቢ የማሰባሰብ ርብርብ ተደርጎ የሚከፈል ይሆናል” ብለዋል።

ደሞዝ የመክፈል ችግሩ ከከተሞች ይልቅ በተለይ በገጠር ወረዳዎች ላይ የከፋ እንደሆነ የዞኑ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

“ወደፊት ገቢ ማሰባሰብ ላይ አቅማችንን አሟጠን መጠቀም አለን ብለን እቅድ ይዘናል፣ ወጪ መቀነስም እንደዛው። በተጨማሪም በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተቀጠሩ፣ መደብ ሳይኖር የተቀጠሩ እና ከመደቡ በላይ ደሞዝ የሚከፈላቸው ላይ የእርምት ስራ ይሰራል” ብለው መረጃ ሰጥተውናል።