ግብፅ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር መሰረት የህዝቦቿን ጥቅም ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷን ገልፀች።

ግብፅ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር መሰረት የህዝቦቿን ጥቅም ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷን ገልፀች።

ግብፅ ይህንን የገለፀችው ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ሰሞኑን የአምስተኛ ዓመት የግድቡ ሙሌት መጠናቀቁን መግለፃቸውን ተከትሎ ነው።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ትናንት እሁድ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት (UNSC) በላኩት ደብዳቤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በግድቡ ሙሌት ላይ የሰጡትን አስተያየት ግብፅ “ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጓን” ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የማጠናቀቅ ሂደት፣ አብደላቲ እንዳሉት ከአለም አቀፍ ህግጋት የመርሆችን ጋር የሚጋጭ እንዲሁም በጎርጎሪያኑ 2015 ዓ/ም የኢትዮጵያ ፣የግብፅ እና የሱዳን የሶስትዮሽ ስምምነት የሚጥስ ነው።
የኢትዮጵያ የተናጠል አካሄድም የወንዙን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይ የግብጽ እና የሱዳንን ጥቅሞች በእጅጉ ይጎዳል ብለዋል።

አብደላቲ አክለውም ግብፅ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር መሰረት የህዝቦቿን ጥቅም ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷን ገልፀዋል።

በጎርጎሪያኑ በ2011 ዓ/ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ግንባታው የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ከ5,000 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት የሚያስችል ሲሆን፤ግብፅ እና ሱዳን ግድቡ ሲጠናቀቅ የውሃ ፍሰቱን በመቀነስ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል በሚል ስጋታቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል በጎርጎሪያኑ 2015 ዓ/ም የሶስትዮሽ ስምምነት ቢደረግም በግድቡ አሞላል እና በመተዳደሪያ ደንቦቹ ላይ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻለም።