ቦረና ውስጥ የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ ነው። የትኛውም ሚዲያ ሆነ የመንግስት ባለስልጣን ስለ ጉዳዩ ሲናገርና መፍትሄ ለመስጠት ሲንቀሳቀስ አላየሁም። በተለይ ላለፉት ሦስት ቀናት ከአከባቢው በደረሰኝ መረጃ በሞያሌ ከተማና አከባቢው እየሆነ ያለው ነገር በጣም አሰቃቂ ነው። በአከባቢው የሚኖሩ ሰዎች በስልክና በፌስቡክ “ኧረ ስዩም ስለ ቦረና ምነው ዝም አልክ?” እያሉ ይጠይቁኛል። ከእነዚህ ውስጥ ለብዙ አመት የማውቀውን ወዳጄን “እስኪ በአከባቢው ስለ ተከሰተው ግጭት የሚያሳይ ፎቶ ወይም ቪዲዮ ላክልኝ?” ብዬ ጠየቅኩት። ይህ ወዳጄ በአንድ ግዜ ከአስር የሚበልጡ የፎቶ ምስሎች ላከልኝ። በሞያሌ አከባቢ በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተገደሉና የቆሰሉ ሰዎችን ምስል ከአንድ ደቂቃ በላይ መመልከት አልቻልኩም። እኔ ለመመልከት የከበደኝ ነገር የአከባቢው ነዋሪዎች በእውን እየሆኑት ነው።
በዚህ መልኩ በጥይት እየተገደለ ላለ ሕዝብ ስለ ፍቅርና ይቅርታ መናገር በሰው ሕይወት እንደ መቀለድ ነው። የቦረና አከባቢ ነዋሪዎች በየቀኑ በጥይት እየተገደሉ ነው። ነዋሪዎቹ በጥይት ሲገደሉ የመከላከያ ሰራዊት ዳር ቆሞ እየተመለከተ ነው። ይሄ ነገር መቆም አለበት! ጠ/ሚ አብይ ሆነ ኦቦ ለማ መገርሳ በቦረና እየደረሰ ያለውን ግድያ ማስቆም አለባቸው። ግድያውን ሳያስቆሙና ገዳዮችን ለፍርድ ሳያቀርቡ ለቦረና ሕዝብ ስለ ይቅርታና ፍቅር፣ ስለ ሰላምና ዴሞክራሲ መናገር አይችሉም። ማንም ሆነ ምንም ነገር ከሕይወት አይበልጥም። የሰው ልጅ ሕይወት ምርጫና አማራጭ የለውም። ሕይወት በፍቅርና ይቅርታ የሚገኝ ነገር አይደለም።
ፅሁፍ ስዩም ተሾመ …. ምስል ከሀምዛ ቦረና