መንግሥት በዓለም ባንክ የተሰጠውን መርዘኛ መድኃኒት ወደ ሕዝብ እየረጨ ነው

መንግሥት በዓለም ባንክ የተሰጠውን መርዘኛ መድኃኒት ወደ ሕዝብ እየረጨ ነው – (ያሬድ ኀይለመስቀል)

የኢትዮጵያ ማክሮም ሆነ ማይክሮ ኢኮኖሚ መሠረታዊ ችግር እየሆኑ ከመጡ መሰናክሎች መካከል የውጭ ምንዛሪ እጥረት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ለሚስተዋለው የዋጋ ንረት መሠረታዊ ምክንያት እየሆነ ያለው ይኸው የውጪ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ ዛሬ በባንክና በትይዩ (ጥቁር) ገበያው ላይ ያለው የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት ከ10 ብር በላይ በሆነ ልዩነት ሰፍቷል፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት መንግሥት ከቀን ወደ ቀን የዶላርን የመግዛት አቅም እያዳከመ መምጣቱና ባንኮች በበቂ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪን ለተጠቃሚዎች ማቅረብ አለመቻላቸው ነው፡፡

መንግሥት በዓለም ባንክ የተሰጠውን መርዘኛ መድኃኒት ወደ ሕዝብ እየረጨ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ከዚህ ቀደም ባደረጉት አንድ ጥናት 2 በመቶ ብር ከዶላር አንጻር የመግዛት አቅሙ ሲወድቅ በ1 በመቶ የዋጋ ንረት መጠን እንደሚያድግ አረጋግጠዋል፡፡ ቀደም ሲል 29 ብር የነበረው የውጭ ምንዛሪ መጠን በየቀኑ እንዲጨምር ተደረጎ ዛሬ 40 ብር ደርሷል፡፡ ጭማሪው መች እንደሚያቆም እስካሁምን ድረስ መንግሥት በግልጽ መናገር አልፈለገም፡፡ ይህ መሆኑ ነገም ይጨምራል በሚል እሳቤ እና በባንክ ቤቶች ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተደማምሮ የትይዩ ገበያው ተመን አንድ ዶላር ከ50 ብር በላይ እየተሸጠ ይገኛል፡፡

መንግሥት በዶላር ተመን ላይ እየሠራ ያለው ሥራ ራስ ላይ ተኩሶ ራስን ከማጥፋት የተለየ አይደለም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ተመኑ እያደገ በመጣ ቁጥር የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ሸጠን 20 ቢሊዮን የምንገዛ አገር ነን፡፡ የዶላር ተመኑ በመጨመሩ ምክንያት ቀድሞ በ20 ቢሊዮን ብር የምንገዛውን ምርት ዛሬ 30 ቢሊዮን ብር በላይ ሊያስወጣን ይችላል፡፡ ቀድሞ ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ የነበረብን እዳችን አሁን የውጭ ምንዛሪ ተመን ጭማሪ በመደረጉ ምክንያት በብር ልኬት ከፍ እያለ ነው፡፡ ከፍተኛ እዳ ያለባት ኢትዮጵያ በምታወጣቸው ፖሊሲዎች እዳዋን ወደ ማይደረስበት ጣራ ከፍ እያደረገቸው ነው፡፡ ይህ በቀጣይነት ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የፍጆታ ምርት እጥረት መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡

ጫናው በዚሁ ከቀጠለ የዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት በጀታችሁ ትክክል አይደለም፡፡ የብድር ጫናችሁ በጣም ከፍተኛ ሆኗል መክፈል ስለማትችሉ፤ አዲስ ብድር መውሰድ አትችሉም፤ የጀመራችሁትን ትላልቅ ፕሮጀክቶች አቁሙ፤ ግድቡን አሁኑኑ አቁሙት ወዘተ… ይሉናል፡፡ ደህንነታችንን በራሳችን ላይ የማዘዝ ሥልጣናችንን ለሌላ ወገን አሳልፈን እየሰጠን ነው፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት መንግሥት የውጭ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትን ጣልቃ ገብነት እምቢ በማለት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማምጣት ችሏል፡፡ አሁን ላይ ግን የውጭ ተቋማትን በማመን (በማምለክ) ችግራችን ይፈታል ብሎ የሚያምን የኢኮኖሚ ሥርዓት ፈጥረናል፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከአንድ ዓመት እና ሁለት ዓመት በኋላ በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ቀውስ የሚያመጡ የፖሊሲ መድኃኒት እየዋጥን ነው፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት እንኳን በዓለም ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ ሳይጨምር በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ጊዜ በድምሩ 5 ብር 90 ሳንቲም የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ይኼ የቀውሱ መጀመሪያ አንድ ምልክት ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ የትራንስፖርት የዋጋ ታሪፍ ጭማሪ አደርጓል፡፡ ትራንስፖርት ሲጨምር የሸቀጦች ዋጋ በእጥፍ ይጨምራል፡፡

እኛ የገንዘባችንን የመግዛት አቅም የምንጥልበት ጊዜ አሁን አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ የሚወሰነው አገሪቱ የተትረፈረፈ ምርት አምርታ ምርቱን የሚገዛን ሲጣፉ ገዥን ለማሰብ በሚደረግ ጥረት ነው፡፡ እኛ እንኳን ለውጭ ገበያ የምናቀርበው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የምንጠቀመው በቂ ምርት የለንም፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የዶላርን በብር የመግዛት አቅም ማዳካም ፋይዳው ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ ማስተካከያው መቼ እንደሚቆምም ግልጽ አይደለም፡፡ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ እንደ ኬንያ አንድ ዶላር 100 ብር እንደማይገባ ማረጋገጫ የለንም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በዚህ ልክ ግልጸኝነት የለውም፡፡ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች ከመወሰናቸው አስቀድሞ ምክክር እና ክርክር ሊደረግበት ይገባል፡፡

መንግሥት አሁንም ውሳኔውን ቆም ብሎ በገበያው እየፈጠረ ካለው ነገር ጋር አስተያይቶ ራሱን ቢገመግም መልካም፡፡ ከተመን ለውጥ ጋር ያለውን ጨዋታ ለጊዜውም ቆም አድርጎ የአገር ውስጥ ምርት የሚያድግበትን ዕድል መፍጠር አለበት፡፡ ከውጭ ንግድ በተጨማሪ መንግሥት በሕግ ዝግ የሆኑ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገዶችን ዳግም መክፈት አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

(ያሬድ ኀይለመስቀል) – ሲራራ – Sirara