የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮች በተለያዩ የመንግሥት ሥራ ሃላፊነት ላይ መሾማቸው ለዴሞክራሲው መጎልበት ጥሩ ሚና አለው።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


  • የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ወደ ሹመት መምጣት ለዴሞክራሲ ዕድገት ጠቃሚ ነው – ዶክተር ዳንኤል በቀለ
  • የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በሙያቸውና በክህሎታቸው ለቦታው የሚመጥኑ መሆናቸው ተረጋግጦ የሚሾሙ ከሆነ የሚበረታታ ተግባር ነው – የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነጋ
(ኢፕድ) –  የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ወደ መንግሥት ሥልጣን በሹመት መምጣት ሊበረታታ የሚገባው እና ለዴሞክራሲያዊ ዕድገት ጠቃሜታ ያለው መሆኑ ተገለፀ። በሀገር ጉዳይ በአንድነት ተጋግዞ መሥራት እንደሚቻል ማሳያ ምሳሌ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተሹመው መሥራት መጀመራቸውን ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሰጡት አስተያየት የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮችን በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በአመራርነት እንዲሠሩ መደረጉ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና አሳታፊነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ነጋ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሾሙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በሙያቸውና በክህሎታቸው ለቦታው የሚመጥኑ መሆናቸው ተረጋግጦ የሚሾሙ ከሆነ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል። ባልተለመደ መልኩ ለተቃዋሚዎች ዕድል የመስጠት ጅማሮው የሚበረታታና አሳታፊ የሚደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚሾሙት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሥራውን መምራት አቅም አላቸው ወይ የሚለው ሊጤን የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ለቦታው የሚመጥኑ ሆነው ከተገኙ መመደባቸው አስፈላጊም ተገቢም ነው የሚሉት አቶ በቀለ፤ የሹመቱ ዕድል መሰጠቱ ተገቢና ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው። መሠረታዊ ችግራችን ከሚሾመው ሰው ሳይሆን የሚሾመው ሰው ሥራውን በብቃት ይመራዋል ወይ ብሎ መጠየቅ ላይ ሊያተኩር ይገባል። እነደ ሀገር ማንኛው የሥራ ሹመት ወይም ሃላፊነት ሲሰጥ የግለሰቡ የሙያ ብቃትና ችሎታ መሠረት ተደርጎ ብቻ መሆን አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በነበረው የፖለቲካ ልምድ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በመንግሥት ሹመት የመስጠት ልምድ እንዳልነበረና አሁን ላይ የተጀመረው አሳታፊነት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ መጠናከር ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት መሆኑን ገልፀዋል።
የተቃዋሚ ፖለቲካ አመራሮች በተለያዩ የመንግሥት ሥራ ሃላፊነት ላይ መሾማቸው ለዴሞክራሲው መጎልበት ጥሩ ሚና አለው። መንግሥትን የሚቃወሙና የተለያየ የሀሳብ ልዩነት ያላቸው ብቁና ቦታውን የሚመጥኑ ሰዎች የተለያዩ ተቋማት ውስጥ በሃላፊነት መሾማቸው በፓርቲዎች መካከል በጋራ የመሥራት ልምድ ሊያጠነክርና ተቀራርበው በተለያዩ ጉዳዮች አገራዊ ጉዳዩ ላይ እንዲግባቡ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግስት ለተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ይህንን መሰል እድል መስጠቱ በጣም የሚያስደስት እርምጃ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ዳንኤል፤ ተግባሩ በሀገር ጉዳይ ላይ በአንድነት ተጋግዞ መሥራት እንደሚቻል በምሳሌነት መጥቀስ እንደሚቻልም ማሳያ ነው።
ሹመቶቹ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብቶች መረጋገጥ አይነተኛ ሚና እንዳላቸው የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ሹመቱ በራሱ የፖለቲካ ተሳትፎ መብት መሆኑንና በልዩነት ውስጥ የሚፈጠሩ የተለያዩ ሰብዓዊ ቀውሶችም ከመከሰታቸው በፊት ተቀራርቦ ለመነጋገርና ለመግባባት በር የሚከፍት መሆኑን ያስረዳሉ። የሰዎች መብት እንዲጣስ የሚያደርገው የከረረ የፖለቲካ አስተሳሰብ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ዳንኤል ይህንን ለማርገብ ትልቅ አስተዋፅዖ የሚኖረው መሆኑን ይገልፃሉ።
በቅርቡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ዶክተር አረጋዊ በርሄ በመንግሥት የተለያዩ ተቋማት ላይ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ተሹመው መሥራት መጀመራቸው የሚበረታታና አስደሳች መሆኑን ገልፀው፤ እሳቸው የተሰጣቸው ሃላፊነት በትክክልና በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸው መግለፃቸው ይታወሳል።