የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችን ቤቶች በኃይል አፈረሰ
መንግስት የባልደራስ አመራሮች ቢገኙም ተፈናቃዮችን እንዳያነጋግሩና ፈረሳው እንዳይቀረፅ ፖሊስ ከልክሏል
(ኢትዮጲስ፤ አዲስ አበባ 30/8/2012)
በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ከኢትዮጵያ ፖስታ ቤት ጀርባ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን መንግስት ከትናንት ለሊት ጀምሮ እስከ ዛሬ ማለዳ ድረስ በኃይል አፍርሷቸዋል። ቤቶቹ በሚፈርሱበት ጊዜ ከነዋሪዎች አቤቱታ የደረሰው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ዛሬ ጧት በቦታው ቢገኝም አመራሮቹ ወደ ውስጥ እንዳይይዘልቁ ፖሊስ ከልክሏል። ተፈናቃዮችንም ማነጋገር እንዳይችሉ አግዷል። በቤት ፈረሳው ላይ የተገኙትን የፓርቲው ሊቀ መንበር እስክንድር ነጋ እና የአደረጃጀት ጉዳዮች ሓላፊውን አቶ ስንታየሁ ቸኮልንም አግቶ አቆይቷል። በቤቶች ፈረሳው እንቅስቃሴ ላይ የክፍለከተማው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተገኙ ሲሆን ክስተቱ በምስልና በድምፅ እንዳይቀረፅ ፖሊስ ከልክሏል።
ቤቶቹ የፈረሱባቸው ነዋሪዎች ከ55 በላይ የሚሆኑ አባወራዎችና እማወራዎች ናቸው። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ያሉ የቤተሰብ አባላትና ተከራዮች ሲጨመሩ የተፈናቃዮችን ቁጥር ከፍተኛ እንደሚያደርገው ይገመታል። ቤቶቹ የፈረሱባቸው ተለዋጭ ቦታ ሳይሰጣቸው በድንገት መሆኑን የተናገሩት ተፈናቃዮቹ የኮሮና ተህዋሲ ወረርሽኝ አለምን እያስቸገረ ባለበት ወቅት የት እንደሚጠለሉ መቸገራቸውን ገልፀዋል። በረመዳን ፆም ላይ መሆናቸውን የገለፁት የእስልምና እምነት ተከታይ ተፈናቃዮችም ለተደራራቢ እንግልት መዳረጋቸውን አብራርተዋል። ከተፈናቃይ እናቶች ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ ዛሬ አመሻሽ የምናቀርብ ይሆናል።
#የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የቤት ፈረሳ #ኢትዮጲስ #Addis Ababa dwellers home deconstruction #Ethiopis
- Category
- Ethiopian News