በሶማሌ ክልል በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው። የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 26፤ 2012 ባወጡት ዕለታዊ መግለጫቸው በክልሉ ዋና ከተማ ጅግጅጋ ባለ የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ባለፈው 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገ ምርመራ ሶስት ተጨማሪ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን አስታውቀዋል። ከ20 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እነዚህ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ከፑንትላንድ የተመለሱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የሶማሊያ ራስ ገዝ አስተዳደር ከሆነችው ፑንትላንድ ወደ ሀገራቸው በተመለሱ ኢትዮጵያውያን ላይ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱ ሲረጋገጥ የዛሬዎቹን ጨምሮ ለስምንተኛ ጊዜ ነው። በምስራቅ ኢትዮጵያ ያለውን የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ለመፈተሽ ባለፈው ሳምንት ወደ ሶማሌ ክልል ተጉዘው የነበሩት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢዎች ከፑንትላንድ እና ሶማሊያ በኩል የሚመጡ ስደተኞችን አስመልክቶ ለክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ ጥያቄ አቅርበዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ “የሶማሊያ ሁኔታ ያስፈራናል” የሚሉት አቶ ሙስጠፌ ክልላቸው ለበሽታው ያለው ተጋላጭነት “አሳሳቢ” እንደሆነ ባለፈው ሐሙስ ሚያዝያ 22፤ 2012 ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጡት ልዩ ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። “በአንዳንድ ቦታዎች እየደረሰን ያለው መረጃ ትልቅ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሊመለሱ ይችላሉ የሚል ነው። ስለዚህ ከዚህ አንጻር፤ የሶማሌ ክልል ከሌሎቹ አካባቢዎች በተለየ ደረጃ፤ አሳሳቢ አካባቢ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም hotspot ሊሆን ይችላል” ሲሉ ያለውን ስጋት ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
- Category
- Ethiopian News