Professor Mesfin Woldemariam’s poem about death. Issued Meskrem 1967
ሞት ማለት
ተንጋሎ መተኛት ፣አለመንቀሳቀስ ፣
ፍፁም የእንቅልፍ ዓለም ፍፁም የሕይወት ቀውስ ፣
አለመደሰት ነው ፤ ተከፍቶ አለማልቀስ ፣
የሬሳ እኩልነት ፣ እርኩስ የለ ቅዱስ ፣
በኅብረት መበስበስ ፣ በየቀኑ መፍረስ ፣
ሞት አለመስማት ነው ፤ ጆሮ ዳባ ልበስ ፣
ክርስቶስ ሲሰቀል ፣ሲፈታ በርናባስ ።
ሞት ማለት :-
አለመናገር ነው ጭው ያለ ዝምታ፣
የመቃብር ሰላም የሬሳ ጸጥታ ፣
ደሀ በሰሌኑ ሳጥን ገብቶ ጌታ ፣
የውሸት ልዩነት ተጋድሞ በተርታ ፣
አይመሽ ወይ አይነጋ ፣ጠዋት የለው ማታ ።
ሐዘን የለ ለቅሶ ፣ደስታ ፣ ፈገግታ ፣
ዘፈኑና ለቅሶው የምስጥ ሹክሹክታ ።
ሞት ማለት:-
አይረገዝበት ፣ አይወለድበት ፣
የመቃብር ዓለም ፣ጭንጋፍ ፣የጭንጋፍ ቤት
የሰው ልጅ አንደበት ትል የሚሆንበት ፣
ውሸትና እውነት በማይበርድ ፍትወት የተሳሰሩበት ፣
የድብቅብቅ ዓለም ምስጢር የበዛበት ፣
ሁሉም በየጉድጓድ የተሸሸገበት።
ሞት ማለት:-
አለመነቃነቅ ፣አለመነቃነቅ ፣
እንደ ድንጋይ መድረቅ ፣ደርቆ መወላለቅ ፣
ክብርና ውርደትን ለይቶ አለማወቅ ፣
አዘቅት ውስጥ ተኝቶ በክፋት መጥለቅለቅ ፣
በተዋኅዶ መልክ ጠላትና ወዳጅ አብሮ ሲደባለቅ ፣
ድፍርሱ ከጠራው ባሕርዩ ሲደበቅ፣
የሩቁ ሲጠጋ የቅርቡ ሲራራቅ ፣
ሞት አምሮት ሲጠፋ በልጦ ለመመረቅ።
ሞት ማለት :-
ሞት አለመስጋት ነው የግዴለሽ ዓለም ፣
ድንጋይ ተሸክሞ በውሃ ላይ መቆም ፣
ጤንነት የለበት፣ አያጠቃው ሕመም ፣
ትዝታ የለበት ፣ አይታይበት ሕልም ፣
ቡቃያው አያሸት ፣ፍሬው አይለመልም ።
ዝናብ አይዘንብበት ድርቀት ነው ዘላለም ።
ማንም አይጎዳ ማንም አይጠቀም ።
ሞት ማለት :-
አዕምሮ ፈራርሶ፣
ኅሊና በስብሶ፣
ሰውነት ረክሶ ፣
እንደግም ፣ እንደጥምብ ፣
የጭልፊቶች ምግብ ፣
የሞት ሞት ይኸ ነው ፤
ትንሳኤ የሌለወ ።
(እንጉርጉሮ -ከመስፍን ወልደማርያም ገጽ 31-32 መስከረም 1967 ዓ. ም)
- Category
- Ethiopian News