Interactive interview with Rwanda Broadcasting Agency | Kigali, 5 September 2021
“ኢትዮጵያ የርዋንዳ እውነተኛ ወዳጅ ነበረች፣ አሁንም ነች ወደ ፊትም ወዳጅ ሆና ትቀጥላለች” ሲሉ የርዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ተናገሩ፡፡
ፕሬዚዳንቱ ትናንት ከአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ አገራዊ፣ ቀጣናዊ እና አጠቃላይ በአፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ለፕሬዚደንቱ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ የርዋንዳ መንግስት አቋምን የሚመለከት ነበር።
ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን በቤተ-መንግስታቸው ተቀብለው ማስተናገዳቸውን በማስታወስ በቆይታቸው በበርካታ የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ በትግራይ ክልል ችግሮች እንዳሉ ሁሉም ያውቃል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ መሃል የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉ በግልጽ መረዳት እንደሚቻል ተናግረዋል።
“ችግሩን ኢትዮጵያ በራስ አቅም ለመፍታት እና ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ፍላጎት እንዳላት እየሰራች መሆኗን አውቃለሁ” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ ጎረቤት አገሮችና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥረት እያረጉ እንደሆነ ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ አገራቸው ርዋንዳም ከነዚህ አካላት መካከል አንዷ በመሆኗ የሃሳብም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ላይ አስተዋጽኦ ለማበርከት እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
ለአገሪቱ ቀጣይነት ላለው ሰላማዊ ጉዞ ትልቅ ድርሻ ያለው ህዝቦቿ በራሳቸው አቅም በጋራ ሆነው የሚያመጡት መፍትሄ በመሆኑ አሁን ላይ ርዋንዳ ልዩ የሆነ ድጋፍ እንዳላደረገች ገልጸዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ችግር በሁለት የተለያዩ ሀገራት መካከል የተፈጠረ ችግር አይደለም” ያሉት ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፤ “ህዝቡም በጋራ የሚኖር በመሆኑ በዚህ መሃል ገብቶ ልዩነት እንዲፈጠር ማድረግ ችግሩ እንዲባባስ ከማድረግ ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም” ብለዋል፡፡
በእያንዳንዱ የአፍሪካ አገር የሚፈጸም መልካም ነገር ለመላ አፍሪካ በተለይ ለጎረቤት እና ለወዳጅ አገር መልካም ነገር እንደሚፈጥር ገልጸው፤ መልካም ያልሆነ ነገር ከተፈጠረም እንዲሁ ጉዳቱ አሉታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
- Category
- Ethiopian News