ቀኑ ድሎችን የምናወሳበት ብቻ ሳይሆን ፈተናዎችን ተገንዝበን ችግሮችን ለመፍታት የምንዘጋጅበት ነው – ጠ/ሚ ዶክተር አብይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ስናከብር ድሎችን የምናወሳበት ብቻ ሳይሆን ፈተናዎችን ተገንዝበን ችግሮችን ለመፍታት የምንዘጋጅበት መሆኑን ገለጹ፡፡

Image may contain: 13 people, people smiling, people sitting

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተከበረው ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ላይ ነው።

ያለቤተሰብ ሀገር መገንባት አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሴቶች በቤተሰብ ሀላፊነት ውስጥ ያላቸው ሚና የማይተካ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ጠንካራ ሴቶች እንደሚያስፈልጉ በመግለጽ እናቶች ደምን፣ ጉልበትን፣ እውቀትን ሀብትን በማጋራት በአርዓያነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡

ከመጉረስ ማጉረስ፣ ከመግፋት ማቀፍ፣ ከመቀማት ማካፈል ውስጣዊ ደስታ የሚያጎናጽፍና ህሊናዊ እርካታ እንደሚሰጥም ከእናቶች መረዳት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ሴቶች ባሎቻቸውን ልጆቻቸውን አጥተው ኢትዮጵያን ለዚህ ትውልድ ማቆየታቸውን በመጥቀስም፥ አሁን ላይ ሰውሰራሽ ግጭቶችን በመከላከልና የሀገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ሴቶች ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ጀግንነት በችግር ጊዜ እውነታን ይዞ መቆም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮችን በመከላከል በኩል ሰፊ ስራዎች እንደሚጠበቁም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም ሴቶች መተሳሰብን፣ አንድነትን እና በጋራ መኖርን ታሳቢ ያደረጉ ስራወች ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሰላም ወዳጆችና የአንድነት ፈላጊዎች ዝምታ ከዚህ በተቃራኒ የቆሙ የጥቂቶች ድምጽ ጎልቶ እንዲሰማ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

ትውልዱ ድልን በመጋራት ሽንፈትን ከመሸሽ አባዜ መውጣት እንዳለበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለዚህም የሴቶች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደደሚገባ አሳስበዋል ሲል የዘገበው ኤፍ ቢሲ ነው።