ጣና ሐይቅንና ሌሎችንም የውሀ አካላት ከጥፋት ይታደጋል የተባለ ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

ጣና ሐይቅንና ሌሎችንም የውሀ አካላት ከጥፋት ይታደጋል የተባለ ኤጀንሲ እንደሚቋቋም የአማራ ክልል አስታወቀ። የክልሉ የአካባቢ የደን እና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን የኤጀንሲው ዋና ተግባር የውሐ አካላትን ከጥፋት ማዳን ብቻ ይሆናል ብሏል።

ኤጀንሲው የሚቋቋመው የአማራ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ጥቅምት 2011 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ነው። የኤጀንሲው ማቋቋሚያ አዋጁ በክልሉ “ዝክረ ህግ” ጋዜጣ ፀድቆ ሰሞኑን መውጣቱን እና መስሪያ ቤቱን ለማቋቋም የሚያስችል ኮሚቴ መዋቀሩንም የአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እሸቴ ተናግረዋል።

ጣና ሐይቅ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ እንቦጭ በተባለ አረም በመወረሩ በሐይቁ ህልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡ አረሙን ለመከላከል በአገር ውስጥ ከሚገኙ ባለሀብቶችና ሌሎች ተቋማት ወደ 50 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን አቶ ጋሻው መናገራቸውን DW ዘግቧል።