ጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ ለደረሰው አደጋ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ ታወቀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ ለደረሰው አደጋ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ ኢሰመኮ አስታወቀ

አደጋውን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጠው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በዞኑ የደረሰው አደጋ በዜጎች ሕይወት ፣ በመኖሪያ ቤቶችና እና በስራ ቦታዎች ላይ ከፍተና ጉዳት ማድረሱን ገልቷል፡፡

የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የሚደርሱት ጥቆማዎች እና ሪፖርቶች በእጅጉ አሳሳቢ ናቸው ያለው ኮሚሽኑ በአፋጣኝ ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲደረገም አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሠለ ለተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ በተፈጥሮ አደጋ ወቅት በተለይ በሴቶች፣ በህጻናት፣ በአረጋዊያን እና በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው ጉዳት የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ከግንዛቤ ያስገባ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሀምሌ 14 ቀን በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቶች ቁጥር 260 በላይ መድረሱን እና ፍለጋው መቀጠሉን እንዲሁም የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

የፌደራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በአደጋው 400 ያህል ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉና እርዳታ እየቀረበላቸው እንደሆነ አስታውቋል።