በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በር ላይ በርካታ ሐሰተኛ የቢጫ ወባ ካርዶች በጠራራ ጸሐይ ይቸበችባሉ።

የሐሰተኛ (ፎርጅድ) የቢጫ ወባ ካርድ ነገር – BBC

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በር ላይ በርካታ ሐሰተኛ የቢጫ ወባ ካርዶች በጠራራ ጸሐይ ይቸበችባሉ። ሰዎች ክትባቱን ከመውሰድ ይልቅ ካርዱን ገዝተው መሄድ ይቀላቸዋል። ይህን ሁኔታ ለመግታት ጥፋተኞችን ሕግ ፊት የማቅረብ ሥራ ስንሠራ ቆይተናል ይላሉ ዶ/ር በየነ።

“ሐሰተኛ ባለማኅተም ካርዶቹ ከሆስፒታሉ የሚወጡ ናቸው ወይ? በሚል ሲጠየቁም “የለም ሙሉ በሙሉ ውጭ ተመሳስለው የሚሠሩ ናቸው” ብለዋል።

ዶ/ር በየነ ጨምረው ይህንን ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ «ባር-ኮድ» ማንበብ የሚችል ዲጂታል ካርድ በመዘጋጀት ላይ እንደሆነ ነግረውናል። ይህ ካርድ በኮምፒውተር መረጋገጥ የሚችል የራሱ መለያ ቁጥር ስለሚኖረው በዚህ ዓመት መጨረሻ ቢጫ ካርዱን ይተካል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህ የሚረዱ መሣሪያዎች ግዢ ተጠናቆ ከቴሌ የቪፒኤን ፍቃድ እየተጠበቀ ነው።

ይህ ዲጂታል ካርድ ተግባራዊ ሲሆን በተጭበረበረ ቢጫ ወባ ካርድ ከአገር የሚወጡ ዜጎችን በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚቻልም ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢጫ ወባ ክትባትን በርካታ ኤምባሲዎች ለተጓዦች በግዴታነት ያስቀምጣሉ። ኢትዮጵያም ይህንኑ ተግባራዊ የምታደርግባቸው ጎብኚዎች በርካታ ናቸው።

ለመሆኑ ከአገር የሚወጡ ተጓዦች በሙሉ ቢጫ ወባ ክትባትን ለመከተብ ይገደዳሉ?

አንዳንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሳምንታት ምንጭ ጠቅሰው እንደዘገቡት ከሆነ ማንኛውም በቦሌ ከአገር የሚወጣ ዜጋና ወደ ከየትም አገር ወደ አገር ቤት የሚገባ ጎብኚ የቢጫ ወባ ክትባት መውሰዱን ያሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት መያዝ እንዳለበትና ይህም ግዴታ ሊደረግ እንደሆነ ዘግበዋል።

ይህ ምን ያህል እውነት ነው በሚል ዶ/ር በየነ ሞገስ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ም/ዋና ዳይሬክተርን ጠይቀናቸው ነበር።

እርሳቸው እንደሚሉት ይህ በመገናኛ ብዙኃኑ የተሰራጨው መረጃ በመጠኑ የተፋለሰ ነው። በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ የሰጡንን ማብራሪያ በአጭሩ እናቅርብላችሁ።

Image result for yellow fever cards

ማን ይከተብ፣ ማን አይከተብ የሚወስነው ማን ነው?

ይህን የመወሰን ሥልጣን የአገሮች እንጂ የማንም አይደለም። የዓለም ጤና ድርጅት ሚና ጠቅላላ ሕጎች መመሪያና ደንቦችን የማዘጋጀትና የመከታተል እንዲሁም የማማከር ሲሆን መዳረሻ አገራት ግን ግዴታን ይጥላሉ።

ቢጫ ወባ ክትባት ሁሉም መንገደኞች እንዲይዙ ቢመከርም አስገዳጅነቱ እንደሚጓዙባቸው አገሮች ደንብና ግዴታ እንጂ ሁሉም ሰው ሲወጣና ሲገባ ይከተብ የሚል መመሪያ የለም።

ክትባቱ የት ይሰጣል?

በአዲስ አበባ ብቸኛው የክትባት መስጫ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲሆን አሁን ግን በቦሌ አየር መንገድ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት መጀመሩን ተከትሎ በአየር መንገድ ውስጥም ክትባት መስጫ ማእከል ለማዘጋጀት መሰናዶ አለ። ከጥቁር አንበሳ ሌላ አንድ የግል ሆስፒታልም ክትባት ለመስጠት ፍቃድ ወስዷል ብለዋል ዶ/ር በየነ።

ወረርሽ ተከስቶ ያውቃል?

በአገር ውስጥ ቢጫ ወባ የያገረሽበታል የሚባለው ቦታ በደቡብ ክልል በተለይም ደቡብ ኦሞና አካባቢው ነው። ኾኖም ወረርሽኙ አልፎ አልፎም ቢሆን መከሰቱ አልቀረም። ለአብነት ባለፈው መስከረም አካባቢ በወላይታ ወረርሽኝ መከሰቱ መዘገቡ ይታወሳል።

ቢጫ ወባ ገዳይ ነው?

ቢጫ ወባ ገዳይ ነው። ነገር ግን ክትባቱ እጅግ አስተማማኝ ነው። በሽታው የተያዘ ሰው ምልክት ሳይኖረው ለሞት የሚያበቃ ሁኔታ ሊገጥመው ይችላል። ሁሉንም የተያዘ ሰው ግን ይገድላል ማለት አይደለም። የበሽታው ምልክቶች ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ መዛል፣ ከፍ ያለ ትኩሳትና የጡንቻ ህመም ናቸው።

በሕይወታችን ስንት ጊዜ ነው መከተብ ያለብን?

አንድ ጊዜ መከተብ ለዕድሜ ልክ ያገለግላል። ሆኖም የአንዳንድ ሰዎች በሽታ የመከላከል መጠን ዝቅ ያለ ስለሚሆን በየ 10 እና 15 ዓመቱ በድጋሚ መከተብ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። አንድ ሰው በቢጫ ወባ ተይዞ ካገገመ በኋላም በድጋሚ የመያዝ ዕድሉ የመነመነ የመነመነ የሚሆነውም ለዚሁ ነው።

ክትባቱ በዘመቻ ለምን አይሰጥም?

የኢትዮጵያ መንግሥት በፈረንጆች በ2020 (ከአንድ ዓመት በኋላ) የቢጫ ወባ ክትባትን በመደበኛነት በዘመቻ (Routine Vaccination) መልክ መስጠት ይጀምራል። ይህንንም ለማሳካት ከወዲሁ ዝግጅት ተደርጓል።

የካርድ ዋጋ ለምን 22 ብር ሆነ?

ይህ ዋጋ የዛሬ 20 እና 30 ዓመት የወጣ ተመን ነው። አንዳንድ ሰዎች የብሩ ማነስ ክትባቱ የውሸት ነው ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል ይላሉ ዶ/ር በየነ። ለመድኃኒቱ የሚወጣው ገንዘብ ግን ከዚህ በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ነው። ይህን ዝቅተኛ ተመን የመከለስ ሐሳብ እንዳለም ዶ/ር በየነ ተናግረዋል።

የቢጫ ወባ ክትባትን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ በዓመት ከ70ሺ የሚልቁ ሰዎች ይከተባሉ።

BBC Amharic