የጠ/ሚ ዐብይ ትልቁ ስኬት ብዙ ሰው በተስፋ እንዲኖር ማድረጋቸው ነው – ዶ/ር ዮናስ አዳዬ

[addtoany]

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአንድ አመት ውስጥ ምን አከናወኑ?

BBC Amharic

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ይማሩ በነበረበት ወቅት ዮናስ አዳዬ( ፒ ኤች ዲ) የትምህርት ክፍሉ የአካዳሚክ ዳይሬክተር ነበሩ፤ የመመረቂያ ጽሁፋቸውንም በቅርበት ተከታትለዋል፡፡

ለሶሰት ዓመታት በነበራቸው ቆይታ እያንዳንዱን ጊዜና ሰዓት በአግባቡ የመጠቀም መርህን ይከተሉ እንደነበር ያወሳሉ፡፡

“ሰዓት በማክበር አንደኛ ናቸው፤ ሁልጊዜም መጀመሪያ የሚገኙት እሳቸው ነበሩ፤ ያኔ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜ ፒ ኤች ዲ አራት ዓመት ይፈጃል፤ እርሳቸው ግን በዓለማቀፍ ደረጃ በተቀመጠው የሶስት ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ ነው ያጠናቀቁት፤ብስለታቸውን ያየሁት መጀመሪያ የጥናት መነሻ ሀሳባቸውን ሰያቀርቡ ነው፤ በእስልምናና ክርስትና ኃይማኖቶች ፍልስፍና ላይ ተመስርተው በአጋሮ አካባቢ የነበረውን ልምድ ነበር ያጠኑት፤ የመደመር ፍልስፍናን ያኔም ያንጸባርቁ ነበር ” ይላሉ፡፡

አሁን ደግሞ ዐቢይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ከመጡ ዓመት ሊደፍን የተቃረበበት ጊዜ ነው፡፡

እስካሁን ያሳለፏቸው ዓበይት ኢኮኖሚዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እያሳረፉት ባለው ተጽዕኖ ዙሪያ ዮናስ አዳዬን ጨምሮ የየዘርፉ ምሁራን ኃሳባቸውን አካፍለውናል፡፡

ፖለቲካ

በሰላምና ደህንነት ተቋም ጥናት መምህርና ተመራመማሪው ዮናስ አዳዬ(ፒ ኤች ዲ) እንደሚሉት የዐብይ ትልቁ ስኬት ብዙ ሰው በተስፋ እንዲኖር ማድረጋቸው ነው፡፡

“ያለጥፋታቸው ኃሳባቸው ስለተለየ ብቻ ጥፋተኛ፣ ወንጀለኛ፣ ነውጠኛ ተብለው የታሰሩ፣ ብሎም ለማመን የሚከብድ ግፍና መከራ ሲደርስባቸው የቆዩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከእስር እንዲፈቱ ከማድረጋቸውም በላይ ካሁን በኋላም ይህ መሰል በደል እንደማይፈጸም የሚያሳዩ ማሻሻያዎችን ለማድረግ መነሳታቸው ትልቅ መልዕክት አለው፡፡”

ዜጎቸ በጎሳቸው፤ በማንነታቸውም ሆነ በቋንቋቸው ምክንያት እንዲሰደዱ መደረጉ ስህተት መሆኑን ማመናቸው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ቦታ እንዲኖር መንገድ እንደከፈተም ይናገራሉ -ተመራማሪው፡፡

ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና ያንን የሚያግዙ ተቋማትን ለማጠናከር በሚል በብሄራዊ ምርጫ ቦርድና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሹመት አሰጣጥ ያሳዩትን ቁርጠኝነትም ማጣቀሻ ያደርጋሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎሳ ፖለቲካ ይልቅ ሃገራዊ ሲልም ክፍለ አህጉራዊ ፖለቲካ ማሰብ እንዲሚቻልም በተግባር አሳይተዋል ይላሉ፡፡

“በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውን የጠላትነት ስሜት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አስገራሚ የወዳጅነት መንፈስ መለወጣቸው ከፍተኛ ፖለቲካዊም ሆነ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘቱ የማይቀር ነው ”

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ከፊታቸው የተጋረጡና በቶሎ ሊፈቱ የሚገባቸው ትላልቅ ፈተናዎች እንዳሉ ነው የሰላምና ደህንነት ጥናት መምህሩ ዮናስ አዳዬ(ፒ ኤች ዲ) የሚናገሩት፡፡

“በየቦታው እያቆጠቆጠ ያለው የጎሳ ነውጠኝነት፣ ራሱ ኢህአዴግ ውስጥ ያለው መከፋፈል እንዲሁም በክልሎች እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለው ግልጽ ያልሆነ ግንኙነት አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልጉ የወቅቱ አንገብጋቢ ችግሮች ናቸው፡፡”

ተመራማሪው ዮናስ አዳዬ ችግሮቹን ለመቅረፍ ያግዛሉ ያሏቸውን የግል የመፍትሄ አቅጣጫዎችም አስቀምጠዋል፡፡

” ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ማምጣት በሚባለው የፖለቲካ መርህ መሰረት ፣ ከመገንጠል ይልቅ መደራደርን መሰረት ያደረገ ውይይት ማድረግ፤ ኢሕአዴግን እንደአዲስ የማዋቀሩ ሂደትም በጣም ጥሩ ጅምር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡” ብለዋል።

“እንደአዲስአበባ፣ ሃዋሳ፤ ባህርዳርና መቀለ ያሉ ትልልቅ ከተሞች በፌደራል አስተዳደር ሥር ሆነው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በነጻነት እንዲኖር ከዓመታት በፊት ታስቦ የነበረው ዕቅድ ሥራ ላይ መዋል አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡” በማለት የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀምጣሉ።

ምጣኔ ብት

ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ በኢትየጵያና በአፍሪካ ኢኮኖሚ ዙሪያ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን አካሂደዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገና ከጅምሩ ሌብነት የበዛበትን ስርዓት ለመታገል መነሳታቸው ከፍተኛ መጠን ያለውን ሃብትን ከምዝበራ በመታደግ የኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ማሳረፍ እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

‹‹ሌብነት ቀላል ከሆነ አምርቶ ከማደግ ይልቅ ሁሉም ያን አጭር መንገድ እየተከተለ በአቋራጭ ይሄዳል ፤የሚሰርቅ እንጂ የሚያምርት አይኖርም፤ ይህ ሂደት ደግሞ የሀገርን ኢኮኖሚ የማውደም አቅም ስለሚኖረው ከሌብነት ይልቅ ሰርቶ የመለወጥን ስሜት ለመፍጠር ይህ ውሳኔያቸው በጣም የሚደገፍ ነው፡፡›› ይላሉ

በከባድ ብድር አዋጭነታቸው በአግባቡ ሳይጠና በየቦታው በግዙፍ ፕሮጀክቶችና ግንባታዎች ያለቅጥ የተለጠጠው ኢኮኖሚ ‹ድንገት አዘቅት ውስጥ ሊከተን ይችላል› የሚል ስጋት ለዓመታት እንደነበራቸውና በየመድረኩ ሲናገሩ እንደነበር ያወሳሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ፡፡

በምክንያትነት የሚያሰቀምጡት ደግሞ ከጠቅላላ የሃገሪቱ ምርት 10 በመቶ የነበረው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ድርሻ በቅርቡ 20 በመቶ ደረሰ ቢባልም አብላጫውን ቦታ የያዙት የግንባታ ሥራዎች እንጂ የፋብሪካዎች መስፋፋት አለመሆኑን ነው::

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን የመጡት ሃገሪቱ በብድር ዕዳ ተዘፍቃ ግራ በተጋባችበት ወቅት በመሆኑ ካሁን በኋላ በከፍተኛ ብድር እየተለጠጡ የሚሰሩ ነገሮችን ለማቆም ወሰኑ፤ ከእርሳቸው በፊት የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ደግሞ አዋጭነታቸው በአግባቡ ሳይጠና በሌብነት ዕቅድ ውስጥ ገብተው፤ ባልተቀናጀም የሥራ አካሄድ የሚመሩ ስለነበሩ ገና ተገንብተው እንኳን ሳይጠናቀቁ የመክፈያ ጊዜያቸው ይመጣ ነበር፡፡ ስለዚህ ብድሩን በረጅም ጊዜ ለመክፈል የማግባባት ሥራ ሰርተው ተቀባይነት አግኝተዋል›› ይላሉ።

እንደ ባለሙያው ኢትዮጵያ በየዓመቱ 17 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የሚያወጣ ምርት ስታስገባ ወደ ውጪ ከምትልከው የምታገኘው ገቢ ግን 3 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

ይህን ክፍተት መሙላት በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ሳቢያ የውጭ ምንዛሬ የመጠባበቂያ ክምችቷ ብዙ ጊዜ የተመናመነ ነው፡፡

” ዐቢይ ሲመጡም የነበራት መጠባበቂያ ከአንድ ወር በላይ ምርት ማስገባት የማትችልበት፤ ከዚያ እየቀነሰ በሄደ ቁጥር ደግሞ እንደመድሃኒት፤ ነዳጅ ያሉ አቅርቦቶችን አደጋ ውስጥ የሚከት በመሆኑ ቢያንስ የሁለት ወራት ክምችት አስገኝተዋል፡፡ ”

የውጭ ኢንቨስትመንትንም አዲስ ዕይታ ፈጥረውታል፤ ልማት ማለት ለባሃብቶች ቦታ እንዲያለሙ ከመስጠት በዘለለ ሰዉንም ማልማት እንደሆነ ለማሳየት እንደቻሉ ይገልፃሉ፡፡

እንደማሳያም ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ነገር ግን ነዋሪዎችን እንደማያፈናቅል የተነገረለትን የለገሃሩን ፕሮጀክት ከሚጠቅሷቸው አንዱ ናቸው፡፡

በፕሮጀክቱ ኢትዮጵያም የ27 በመቶ ድርሻ መውሰዷ ስለውጭ ኢንቨስትመንት የነበረውን አመለካከት መዋቅራዊ በሆነ መንገድ እንደሚለውጥ እምነት አላቸው፡፡

” ድክመት “

ዓለማቀፍ ተቋማትም ሆነ የውጭ ሃገራት ለብድር ሲጠየቁ ከዓለም ባንክና ከዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር በትብብር የሚሰራ መርሃግብር መኖሩን እንደሚጠይቁ ነው የኢኮኖሚክስ መምህሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ የሚገልጹት

እነርሱ ደግሞ የመንግሥትን ግዙፍ ኩባንዎች ወደግል ማዞርን እንደቅድመ ሁኔታም እንደግዴታም ያስቀምጣሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩ የልማት ድርጅቶችን ለግል ኩባንያዎች ክፍት እንዲሆን መወሰናቸው ከዚህ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ቢናገሩም ከዚያ መቅደም የነበረባቸው መደላድሎች ነበሩ ይላሉ፡፡

‹‹የውጭ ኦኮኖሚ በዋናነት በግል ዘርፍ የሚመራ ነው ፤ እኛ ጋር ግን የተጠናከረ አይደለም ፤ ስለዚህ መጀመሪያ መንግሥት ራሱ ከሃገር ውስጥ የግል ተቋማት ጋር በጥምረት መስራት አለበት፤ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ወደ ግል የሚዛወሩበት መሰረታዊ መርህ ፍትሃዊ የውድድር ሜዳን ፈጥሮ የተሳለጠ አካሄድ ማበጀት ስለሆነ ፍትሃዊነቱን የሚዳኝ አካል መቋቋም አለበት ካለበለዚያ ከመንግስት የበላይነት(ሞኖፖሊ) ወደ ግለሰቦች የበላይነት( ሞኖፖሊ) ነው የሚሄደው፤ የግለሰብ ኢኮኖሚ ደግሞ በየትኛውም ዓለም ተጠያቂ አያደርግም፡፡›› የሚሉት ባለሙያው

አክለውም ‹‹ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮምን ብንወስድ ገዢው ድርጅት አገልግሎቱን የሚሰጠው በብር ስለሆነ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱንም ቢሆን ለአጭር ጊዜ እንጂ በዘላቂነት አይቀርፈውም፡፡የኢትዮጵያ አየር መንገድም ቢሆን አሁን በመቶኛ የሚያገኘው ትርፍ ከአሜሪካ ሰባት ግንባር ቀደም አየር መንገዶችም በላይ ነው›› ይላሉ፡፡

ፕሮፌሰሩ የዐቢይና የመንግሥታቸው መሰረታዊ ድክመት ነው የሚሉት ደግሞ በህግና በፖለቲካው ዘርፉ ያደረጓቸውን ዓይነት ማሻሻያዎችም ሆነ ምክረ ሃሳቦችን በኢኮኖሚው አለማካሄዳቸውን ነው፡፡

” ኢኮኖሚውን ተቋማዊ በሆነ መንገድ ለማደራጃት ነጻ የሆኑ ባለሙያዎችን ሰብስበው የኢኮኖሚው ፍኖተ ካርታ እንዴት መሆን አለበት ብለው አላማከሩም፤ዕቅዱን የሚነድፈውና የሚያስፈጽመው ባለሞያው እንዲሆን የምጣኔ ሃብት ጉዳይ የአማካሪ ቡድን መቋቋም አለበት፤ የእስካሁኑን አፈጻጸም ቢባል የሚለካው በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማሳካት ከተያዘው እቅድ አንጻር እንደመሆኑ እርሳቸውን ከዚህ አንጻር ለመግምገም የሚያስችል የሰማነው ዕቅድ የለም፡፡” በማለት ይገልፃሉ

እናም ሥልጣን ላይ ከመጡ እጭር ጊዜ ቢሆንም ስራ አጥነትን ለመቀነስ፤ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግና ብዙ ጉልበት የሚፈልጉ የተፈበረኩ ምርቶችን በማምጣት ብዙሃኑን ተጠቃሚ ያደረገ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ለኢኮኖሚው ካለፈው የተሻለ ጊዜ እንዲሠጡ ይመክራሉ፡፡