ሀይ ባይ ያጡት የኢትዮጵያ ባንክ ሹመኞች እና የምዝበራ ስራዎቻቸው

(በግል ከደረሰኝ ጥቆማ የተወሰደ ነው) – ጋዜጠኛ ኤሊያስ መሰረት

ዱሮ ዱሮ አይደለም የባንክ ባለስልጣን መሆን ተራ የባንክ ሰራተኛ መሆን እንደ ትልቅ ማዕረግ ይቆጠር ነበር። ለዛም ነበር ባንከሮች “Trust me, I am a banker” የሚሉት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከወትሮ በተለየ አብዛኛው በተለይ የኢትዮጵያ የግል ባንኮች መደበኛ የባንክ ስራ መስራትን ወደ ጎን ትተው የወንበዴዎች እና ወንጀለኞች መፈንጫ ከመሆንም አልፎ በህዝብ ገንዘብ የተመሰረቱት እና ከድሃ ማህበረሰብ በተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ባንኮች ምዝበራዎቻቸው ልክ ከማጣቱ የተነሳ ህልዉናቸውን አደጋ ላይ እስከመጣል ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

ይሄ ብቻ ሳይሆን በነዚህ ባንኮች ዉስጥ በሚደረገው ምዝበራ እና ጤናማ የንግድ ሂደትን ባልተከተለው የንግድ ሰንሰለት የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብን እያማረረ ከሚገኘው የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ዉደነት አስተዋፅኦአቸው ይህ ነው የማይባል ከፍ ያለ ነው። ለዚህ ህገወጥ እና ልክ ያጣ ድርጊታቸው ምክንያት የሆናቸው ደግሞ እጅግ ክፍት የሆነ የህግ ማዕቀፍ መኖሩ እና ባለፉት አመታት ከተቆጣጣሪ አካል (ብሔራዊ ባንክ, Finacial intelligence እና ሌሎች የመንግስት አካላት) ተገቢ ትኩረት ባለማግኘቱ ነው።

ሰሞኑን የበዛው የብሔራዊ ባንክ የመመሪያ ጋጋታም ይሄንኑ ክፍተት የተገነዘበ ይመስላል፣ ብቻ ያለፈው አልፎ የሚመጣውን ችግር ቢያስቀርልን የሚናቅ አይደለም።

ለማንኛዉም በነዚህ የግል ባንኮች ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሚሰሩት ምዝበራዎች ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል:

1. ለብዙ ሰው ለማመን በሚከብድ ደረጃ በዋናነት የ black ማርኬት ዋነኛ አዋዋዮች ወይም አገናኞች ሆነው የሚሰሩት እነዚህ ሹመኞች ተብለው የተሰየሙት የባንክ ባለስልጣናት ናቸው። ይሄም አሰራሩ እንዲህ ነው: መንግስት ኤክስፖርትን ለማበረታታት ለኤክስፖርተሮች ወደ ዉጭ ሀገር ልከው ከሚያስገኙት የዶላር መጠን ዉስጥ 30% እና በቅርብ ጊዜ ደግሞ 50% ለራሳቸው ለዕቃ አስመጭነት እንዲጠቀሙ መፍቀዱ ይታወሳል። ነገር ግን ሁሉም ላኪዎች አስመጪ ባለመሆናቸው ከሚደርሳቸው ዶላር ላይ ለተለያዩ አስመጪዎች በነዚህ የባንክ ሹመኞች አስተባባሪነት ከ black market ዋጋ ላይ በተሻለ መልኩ ያሻሽጣሉ፣ ይሄን በማድረግ ለነዚህ ሹመኞች በመልሱ ዳጎስ ያለ commission ይከፈላቸዋል። ከዚም አልፎ እንደምንሰማው ከሆነ ለአንዳንዶቹ ከዱባይ እስከ አሜሪካ ድረስ በቱጃር አስመጪዎች የመኖርያ ቤት በስጦታ መልክ ይገዛላቸዋል።

2. በብዛት በዚህ ድርጊት ዉስጥ የሚሳተፉት ፕሬዝደንቶች፣ የብድር እና የዉጭ ንግድ ምክትል ፕሬዝደንቶች እና እስከ ዳይሬክተሮች የሚገኙት ናቸው። የእነዚህ ሹመኞች ምዝበራቸው በዉጭ ምንዛሬ ብቻ ቢቆም ጥሩ ነበር፣ ነገር ግን የተለያየ የህግ ክፍተትን ተጠቅመው ከድሀ የተሰበሰበውን ብር በቢሊየኖች የሚቆጠር መጠን በብድር መልክ የአንድ ግለሰብ ሀብት እና የንግድ አቅም ከሚችለው በላይ እንደፈለጉ ከ collateral free/clean base በሆነ እና የብሔራዊ ባንክ ሕግ ከሚፈቅደው ዉጭ ሲሰጡ ይስተዋላል። ይሄን በማድረጋቸው አንድ አንድ ተበዳሪዎች የወሰዱትን ብድር ጠቅላላ የአንድን ባንክ total capital እስከመድረስ የሚሄዱም አሉ። ይሄን ሁሉ ሲያደርጉ ባንኮቹ ቦርድ ወይም ተቆጣጣሪ አካል የላቸውም ወይ ልትሉ ትችላላችሁ፣ ግን እነዚ ሹመኞች እጃቸው በጣም እረጅም ከመሆኑ የተነሳ በየእርከኑ የሚገኝ የትኛዉንም አካል በጥቅማ ጥቅም እጅ የመጠምዘዝ ስራ ይሰራሉ ምክንያቱም ብር በነሱ እጅ ስለሆነ በስጦታ መልክ እንደውም አነስ ባለ ወለድ በብድር መልክ ሰዎችን አፍ የሚያስዙበት ከመኪና እስከ ቤት ድረስ ይጨብጣሉ። በስራቸው የማይተባበሩ ወይም እንቅፋት ይሆናሉ ብለው ያሰቡትን አካል ደግሞ በፈለጉበት ጊዜ ያባርራሉ፣ ወይም ያስፈራራሉ ወይም ከፊታቸው ዘወር ያስደርጋሉ። በተጨማሪ፣ አንዱ አካል አንዱን እንዳይጠይቅ (Check and balance እንዳይኖር) ለማድገረግ ከቦርድ እስከ ክፍል መሪዎች ከ10 ሚልዮን ብር እስከ 200 ሚልዮን ብር የሚደርስ የንግድ ብድር (commercial loan) ይሰጣጣሉ። በዚህ ሁሉ ግዜ ግን ታች ላሉ ሰራተኞቻቸው በዓመት አንዴ እንኳን ስልጠና ሳያሰጡ የቦርድ እና የባንክ አመራሩ በዓመት ከ 3-4 ጊዜ ተሰብስቦ ወደ ዉጭ ሀገር ሄዶ ለሳምንታት ተዝናንቶ ይመለሳል፣ ገንዘብ አባከንክ የሚላቸው ሰው የለም።

3. እነዚህ ሀብታሞች በዚህ መልክ በሚያፈሩት ሀብት ሀገራቸው ውስጥ ቢሰሩበት ጥሩ ነበር፣ አብዛኞቻቸው ግን ወደ ዱባይ እና ወደ ሌሎች ሀገራት ሀብታቸውን በኤክስፖርት ስም ተጠቅመው የሀገር ሃብትን በገፍ ሲያሸሹ ይስተዋላሉ። በዚህ ድርጊት ዉስጥም የነዚህ የባንክ ባለስልጣናት ሚና ከፍ ያለ ነው። በዚህ ህገወጥ ምዝበራ ዉስጥ የሚሳተፉት ሁሉም ባንኮች ላይሆኑ ቢችሉም በሚያሳዝን መልኩ ግን ከዉጭ ጤናማ እና ብዙ ስም ያተረፉት የግል ባንኮች ዉስጣቸው ቢፈተሽ ከላይ ለመጥቀስ የሞከርኩት ችግሮች በመጠኑም ቢሆን የማይመለከታቸው ምናልባት ጥቂት ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪ አሁን በምናየው ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም የኢትዮጵያ የግል ባንኮች ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ጤናማ የሆነ የባንክ ስራ ይሰራሉ ማለት እጅግ ያዳግታል፣ ምክንያቱም አብዛኞቻቸው ከጤናማ ፉክክርም አልፎ ደንበኞችን ለመሳብ/ለመነጣጠቅ በሚል ጥላ ስር ሆኖ ያልተገባውን ጥቅምን ትላልቅ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ለሆኑ የድርጅቶች ስራ አስኪያጆች እና ሌሎች ሰራተኞቻቸው የመኪና እና የቤት ቁልፍ በስጦታ መልክ (ከባንክ ወጪ አድርገው) እስከ መስጠት የደረሱም አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለደንበኞቻቸው ከሚፈቅዱት ብድር እና ዋስትና (guaratee)፣ commision ተደራድሮ ሲወስዱም ይስተወላል። ከዚ የተነሳ የአንዳንድ ደንበኞች ብድር ተበላሽቶ ሳይከፈሉ ሲቀሩ የተበላሸ ብድር (NPL) ዉስጥ ይመደባል። ከዚ ጋር ተያይዞ አንድ የተለመደ ቀልድ አለ ይባላል፣ የብድር ባለሙያዎች ብድር መክፈያ ጊዜ ለተበዳሪዎች ብድር ክፈሉ ሲሉዋቸው “ግማሹ እናንተ አለቃ ጋር ነው የቀረው፣ ከየት አምጥቼ እከፍላለው” ይላሉ።
4. በዚህ የህዝብ እና የሀገር ሀብት ምዝበራ ዉስጥ በቀዳሚነት የሚሳተፉት እና ሲሳተፉ የከረሙ ግለሰቦች ወይም ባንኮች ስም መጥቀስ አስፈላጊ ስላልሆነ እሱን ለሚመለከተው አካል ትቼ ለጥቆማ ያህል በቅርቡ አንዱ ባንክ በዚህ ምዝበራ ወስጥ በመሳተፍ የባንኩን ስራ በእጅጉ ጎድተውታል በሚል ከዉስጥ በበረታበት ጫና አንዱ ባንክ የንግድ አገልግሎት እና የትላልቅ ደንበኞች ክፍል ምክትል ፕሬዚደንት የነበረውን ግለሰብ ያለ ምንም የሕግ ተጠያቂነት ማሰናበቱን መጥቀስ ይቻላል። ጋዜጠኛ ኤሊያስ መሰረት